የጉሮሮ ካንሰር ለምን የአርሲ እና የባሌ አካባቢ ማህኅረሰብን በተለየ ያጠቃል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጉሮሮ ካንሰር፣ ገዳይ ከሆኑ የካንሰር ዓይነቶች መካከል አንዱ ነው። በተለያዩ የዓለማችን አገራት በጉሮሮ ካንሰር የሚጠቁ ሰዎች ቢኖሩም ከሌሎች በተለየ ግን ስርጭቱ ሰፋ ብሎ የሚታይባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።
እነዚህ አገራትም በምሥራቅ እና በደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በእስያ የሚገኙ አገራት ናቸው።
ኢትዮጵያም የጉሮሮ ካንሰር በስፋት ከሚስተዋልባቸው አገራት መካከል ትገኛለች።
ምንም እንኳ እርግጠኛው የጉሮሮ ካንሰር መነሻ ምክንያቶች እነዚህ ናቸው ተብሎ ባይበየኑም፣ በበርካታ አገራት የአልኮል መጠጥን የሚያዘወትሩ፣ በሲጋራ ሱስ የተጠመዱ ሰዎች በጉሮሮ ካንሰር እንደሚጠቁ ጥናቶች ያሳያሉ።
በተጨማሪም የሚፋጁ ምግቦች እና መጠጦችን የሚያዘወትሩ ለጉሮሮ ካንሰር የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ መሆኑን እነዚህ ጥናቶች ጠቁመዋል።

ካንሰር ምንድን ነው?
ካንሰር ሰውነታችን ውስጥ ያሉ ሴሎች ያለ አግባብ ሲበዙ የሚፈጠር በሽታ ነው። ይህ ያለ አግባብ የሴሎች መባዛት፣ ሰውነት ላይ እብጠት ይፈጥራል። ይህ እባጭም በጊዜ ሂደት እያደገ የሚሄድ ነው።
ዶ/ር ጂልቻ ድሪባ የካንሰር ስፔሻሊስት እና በበሽታው ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን በመስራት ላይ ይገኛሉ።
"ካንሰር ከተፈጠረበት የአካላችን ክፍል በመነሳት እየተስፋፋ የሚሄድ ሲሆን፣ የሰውነታችንን ምግብም ይሻማል። በዚህ ሂደትም በሙሉ ሰውነታችን ላይ በመስፋፋት ሕይወትን እስከ ማሳለፍ ይደርሳል" ይላሉ ዶ/ር ጂልቻ።
ስለጉሮሮ ካንሰርም ሲያብራሩ በኢትዮጵያ ከሌሎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች በተለየ በአርሲ እና በባሌ ተስፋፍቶ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
እርሳቸውም የባሌ እና የአርሲን ማኅበረሰብን በስፋት እየጎዳ የሚገኘውን ይህንን የጎሮሮ ካንሰር ላይ አራት ጥናቶችን ይፋ አድርገዋል።

የአርሲን እና የባሌን ማኅበረሰብን ለምን?
ይህ የካንሰር ዓይነት የጉሮሮ ቱቦን የሚያጠቃ ሲሆን 'የጎሮሮ ካንሰር' በመባል ይታወቃል።
ኢትዮጵያ ውስጥም በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ላይ ይስተዋላል።
"በአገር ደረጃ በዚህ የካንሰር ዓይነት ተይዘው በብዛት ወደ ሆስፒታል የሚመጡ ሰዎች በተለይ ከባሌ እና ከአርሲ አካባቢ ነው። እኔም በዚህ ጉዳይ ላይ ለዓመታት ጥናት ሳደርግ ቆይቻለሁ። ምሥራቅ ሸዋ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ቡታጅራ እና ስልጤ አካባቢዎችም እንደ አርሲ እና ባሌ ባይሆንም ይህ በሽታ ከሚታይባቸው አካባቢዎች መካከል ናቸው።"
ይህ የካንሰር ዓይነት ለምን በእነዚህ ሁለት አካባቢዎች በስፋት ይከሰታል?
እንደ ዶ/ር ጂልቻ ጥናት ከሆነ ዋናው ምክንያት በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩት ማኅበረሰቦች አዘውትረው ከሚመገቡት ምግብ ጋር የሚያያዝ ነው።
"ለዚህ የካንሰር ዓይነት ጥናቶች እንደምክንያት የሚጠቅሱት ሁለት ነገሮች አሉ። እነርሱም አልኮል እና ትኩስ [የሚፋጁ] ምግቦችን መመገብ ናቸው። በአርሲ እና በባሌ አካባቢ ደግሞ አልኮል ብዙም የማይዘወተር ነገር ነው። ስለዚህ ምክንያቱ ሊሆን የሚችለው የሚመገቡት ምግብ ነው ማለት ነው" ይላሉ።
ልክ በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ሰዎች እንጀራ በየዕለቱ እንደሚመገቡት ሁሉ በባሌ እና በአርሲ ማኅበረሰብ ባህላዊ ምግብ የሆነው ገንፎ የዚህ ካንሰር መነሻ መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች እንዳሉ ዶ/ር ጂልቻ ይናገራሉ።

"የእነዚህ አካባቢ ነዋሪዎች በብዛት ገንፎ ይመገባሉ። ገንፎ ደግሞ በባህሪውም በባህልም ትኩሱን ነው የሚበላው። ይህ ደግሞ በጊዜ ሂደት ለዚህ የካንሰር ዓይነት እንድንጋለጥ ያደርጋል ማለት ነው" በማለት ስለዚህም እንደመፍትሄ ሰዎች ይህንን ምግብ ሲመገቡ አቀዝቅዘው እንዲበሉ ባለሙያው ይመክራሉ።
በተጨማሪም በአመጋገብ ልማድ ምክንያት ለዚህ የጤና ችግር ተጋላጭ የሆኑ አካባቢ ነዋሪዎችን የአመጋገብ ሥርዓትን መቀየር አስፈላጊ መሆኑንም ዶ/ር ጂልቻ ጠቅሰዋል።
ባለሙያው ቁርስ፣ ምሳ እና እራት ገንፎ በየዕለቱ መመገብ ለጉሮሮ ቱቦ ካንሰር የመጋለጥ እድልን እነደሚያሰፋ ይገልጻሉ።
ይህ የጉሮሮ ቱቦ ካንሰር ምን ያህል አስከፊ ነው?
ዶ/ር ጂልቻ እንደሚሉት ይህ የካንሰር ዓይነት ከሌሎች የካንሰር ዓይነቶች አንጻር ለማከም የሚያስቸግር እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሕይወትን ሊያሳጣ የሚችል ነው።
"አሁን አሁን ብዙ የካንሰር ዓይነቶችን ማዳን እየተቻለ ነው። የጎሮሮ ቱቦ ካንሰር ግን በጣም አስከፊ ነው። አንዴ ከያዘ ተመልሶ የዳነን ሰው ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው" ይላሉ።
"በየጎሮሮ አካባቢ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ እንኳ በጣም አስቸጋሪ ነው። በቱቦ አካባቢ ያሉት ሌሎች የሰውነታችን አካላት በጣም ወሳኝ ናቸው። ልባችን የሚገኘው በዚያ አቅራቢያ ነው። ሳንባችንም እንደዚሁ። ከዚያ በተጨማሪ ትልቁ የደም ቧንቧ፣ አኦርታ የሚባለውም የሚገኘው በዚሁ አካባቢ ነው። ስለዚህ ይህ ካንሰር ከያዘ ቶሎ ወደ እነዚህ የአካል ክፍሎች ይስፋፋል ማለት ነው" በማለት የሚያስከትልውን ውስብስብ ችግር ይገልጻሉ።
ስለዚህ ይህ የካንሰር ዓይነት አንዴ ከያዘን ረዥም ጊዜ ሳይሰጥ በወራት ጊዜ ውስጥ ሊገድል ይችላል ይላሉ።
የዚህ ካንሰር ዓይነት ምልክቶች ምን ምንድን ናቸው?
በዚህ ካንሰር ዓይነት የተያዘ አንድ ታማሚ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያየው ምልክት የደረት ማቃጠል ነው።
ይኹን እንጂ ብዙ ሰዎች ይህ ምልክት የቀላል ሕመሞች ምልክት አድርገው ስለሚያስቡ ወደ ሆስፒታል ከመሄድ ይልቅ፣ አቅልለው በመመልከት የጨጓራ መድኃኒት እንደሚወስዱ በጥናታቸው ማረጋጋጣቸውን ይናገራሉ።
"በዚህ የካንሰር ዓይነት የተያዘ ሰው ደረቱ አካባቢ የማቃጠል ስሜት ከመሰማት ባሻገር፣ በሂደት ምግብ መዋጥ ሊያስቸግረው ይችላል። መጀመሪያ ላይ ጠጣር ምግቦችን ከዚያ ደግሞ ፈሳሽ፣ መጨረሻ ላይ ምራቁን ጭምር መዋጥ ይቸገራል። ከዚያም ክብደቱ በጣም ይቀንሳል" ይላሉ።


















