ከ50 በላይ የካንሰር አይነቶችን ቀድሞ የሚለይ የደም ምርመራ ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምንም አይነት የካንሰር ህምም ምልክቶች ከመታየታቸው በፊት በሚደረግ ቀላል የደም ምርመራ ከ50 በላይ የካንሰር አይነቶችን መለየት እንደተቻለ ተመራማሪዎች አሳወቁ።
በዚህም በሰውነት ውስጥ የሚከሰቱ ካንሰር አምጪ ሴሎችን በመጀመሪያ ደረጃ ላይ እያሉ ለመለየት ያስችላል።
ባለሙያዎቹ እንደሚሉትም ይህ ምርመራ ካንሰርን በወቅቱ ለማከም ከፍ ሲልም ለማዳን ተስፋን እንደፈጠረ አመላክተዋል።
በሥራው ላይ የተሳተፈው ቡድን እንደጠቆመው በምርመራው የተገኙት ካንሰርን አመልካች ውጤቶች ውስጥ ከ99 በመቶ የሚበልጡት ትክክለኛ መሆናቸው ተመልክቷል። ነገር ግን ውጤቱ ስህተት እንዳይኖረው ማረጋገጥ ያስፈልገዋል ተብሏል።
ሐኪሞች ምርመራውን በህሙማን ላይ እየሞከሩት ሲሆን ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልገው በካንሰር ህክምና ላይ የሚያተኩረው መጽሔት ገልጿል።
ምርመራው ከካንሰር አምጪ ህዋሳት በመውጣት በደም ስሮች ውስጥ የሚገኝንና በዘረ መል ውስጥ የሚከሰትን ኬሚካላዊ ለውጥ የሚዳስስ ነው።
ከተለያዩ የህክምና ምርምር ተቋማት የተወጣጡት አጥኚዎች ካንሰር ያለባቸውና የሌለባቸው ከ4 ሺህ የሚበልጡ የህሙማን ናሙናዎችን በመውሰድ ሙከራ አድርገዋል።
በዚህ የሙከራ ምርመራ ወቅትም የአንጀት፣ የሳንባና የማህጸን ካንሰርን ጨምሮ ከ50 የሚበልጡ የካንሰር አይነቶች ተካተዋል።
ሙከራው ከተደረገባቸው ናሙናዎች ውስጥ 96 በመቶው የሚሆኑት ላይ የተገኘው የመርመራ ውጤት በትክክል ያለባቸውን የካንሰር አይነት የመለከተ እንደሆነም ተገልጸወል።















