ኤርትራውያን በካንሰር ለሚሰቃይ ግለሰብ በ24 ሰዓታት ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር አሰባሰቡ

ዮናስ ከቤተሰብ አባላቱ ጋር

የፎቶው ባለመብት, HENPAS ENTERTAINMENT

በውጭ አገራት የሚኖሩ ኤርትራውያን እና ትውልደ ኤርትራውያን ዲያስፖራዎች በሕመም ለሚሳቃይ አንድ ኤርትራዊ ግለሰብ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን የካናዳ ዶላር በላይ አሰባሰቡ።

በኤርትራ ነዋሪ የሆነው እና የስድስት ልጆች አባት የሆነው ዮናስ ፀጋይ፤ ባለፈው አንድ ዓመት ሆድኪን ሊምፎማ በተባለ የደም ካንሰር አይነት ሲሰቃይ ቆይቷል።

'ዮናስ ፀጋይን እና ቤተሰቡን ይርዱ' በሚል በተከፈተው የጎፈንድሚ አካውንት በ24 ሰዓታት ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የካናዳ ዶላር ማሰባሰብ ተችሏል።

ለዮናስ የተሰባሰበው መዋጮ ማክሰኞ ጥር 09 ከሰዓት ላይ 637 ሺህ የካናዳ ዶላር (ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ) ደርሷል።

በጎፈንድሚ ገጽ ላይ ተያይዞ በወጣው የእርዳታ ተማጽኖ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ፤ ዮናስ ፀጋይ በደም ካንሰር ምክንያት ከፍተኛ ሕመም ውስጥ እንደሚገኝ እና ሰዎች ለሕክምና ወጪ መዋጮ እንዲያደርጉለት ሲማጸን ይታያል።

በስድስት ልጆቹ ተከቦ የሚታየው ዮናስ፤ በሕመሙ ምክንያት ሰውነቱ አብጦ እና እጆቹን በኃይል ሲያሽ ይታያል።

ለዮናስ የቀረበው የእርዳታ አድርጉ ጥሪ በርካታ ምላሾችን በማግኘት በጎፈንዲሚ ገጽ ላይ ቀዳሚ ደረጃን ይዟል።

ዮናስ በኤርትራ ወደ ጤና ተቋማት ቢሄድም ለተጨማሪ ሕክምና ከአገር ውጭ መጓዝ እንዳለበት ተነግሮታል።

በድህነት ውስጥ የሚኖረው ዮናስ የሕክምና ወጪውን መሸፈን አለመቻሉን በመግለጽ አንድ የዩቲዩብ ገጽ የስድስት ልጆቹ አባት የሆነው ግለሰብ ያለበት ሁኔታ ለሌሎች አጋርቷል።

ዮናስን ለማገዝ የጎፈንድሚ ገጽ በተከፈተ በመጀመሪያዎቹ 12 ሰዓታት ውስጥ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኤርትራውያን ከ350 ሺህ የካናዳ ዶላር በላይ በማዋጣት ፈጣን ምላሽ ሰጥተዋል።

የእርዳታ ገንዘብ አሰባሳቢዎች መካከል አንዱ የሆነው ዮሴፍ ወርቄ እንዲህ በፍጥነት በርካቶችን ያሳተፈ መዋጮ አጋጥሞት እንደማያውቅ ለቢቢሲ ትግርኛ ክፍል ተናግሯል።

አስተባባሪው እንደሚለው በሕመም የሚሰቃየው የዮናስ ተማጽእኖ የበርካታ ሰዎችን ልብ ተነክቷል።

እንድ የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አግልግሎት (ኤንኤችኤስ) ድረ-ገጽ ከሆነ ዮናስ የሚሰቃይበት ሆድኪን ሊምፎማ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ከነጭ የደም ሴል ጋር የተገናኘ የደም ካንስር አይነት ነው።

ተቋሙ እንደሚለው ከሆነ ይህ የካንሰር ሕመም በጨረር ሕክምና (በኬሞቴራፒ) እንዲሁም በራዲዮቴራፒ ሕክምና ሊድን ይችላል።