ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ዋንጫ ስትሰናበት ቡርኪና ፋሶ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈች

የኢትዮጵያ ተጫዋች ሱራፌልና የቡርኪናፋሶው አዳማ ጉይራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያ ትላንት ምሽት በተደረገው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታ ከቡርኪና ፋሶ ተፋልማ አቻ ብትወጣም ከአፍሪካ ዋንጫ ተሰናብታለች።

ሲሪል ባያላ በ25ኛው ደቂቃ ከመሃል ሜዳ የተሻማለትን ኳስ የተክለማርያም ሻንቆን ከመረቡ መራቅ ተመልክቶ በአናቱ አሳልፎ የመጀመሪያውን ጎል አስቆጥሯል።

ከእረፍት በኋላ ስቲቭ ያጎ ኳስ በእጁ በመንካቱ ለኢትዮጵያ ፍፁም ቅጣት ምት ዳኛው ሰጥተዋል።

ይህንን ፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ጌታነህ ከበደ በማስቆጠር ጨዋታ አንድ አቻ እንዲሆን አስችሏል።

ነገር ግን ይህ ውጤት ከምድቡ ምንም ጨዋታ ላላሸነፈችው ኢትዮጵያ በቂ አልነበረም። በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ከውድድሩ የመጀመሪያዋ ተሰናባች ስትሆን ቡርኪና ፋሶ ሁለተኛ ሆና ወደ ቀጣይ ዙር አልፋለች።

ቡርኪና ፋሶ በሚመጣው እሑድ በዙር 16 ከምድብ ሲ ሞሮኮን፣ ጋናን አሊያም ጋቦንን የምትገጥም ይሆናል።

ቡርኪናቤዎችና ኬፕ ቨርድ ምድቡን በእኩል 4 ነጥብና በተመሳሳይ የጎል ልዩነት ቢያጠናቅቁም እርስ በርስ ተገናኝተው ቡርኪና በማሸነፏ ነው ሁለተኛ ሆና ወደ ቀጣይ ዙር ያለፈችው።

ካሜሮን ሶስተኛ ከወጣችው ኬፕ ቨርድ ጋር አቻ ተለያይታ የምድቡ አውራ ሆና አልፋለች።

ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ምን ነበር?

ዋሊያዎቹ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ከሒሳባዊ ቀመር ባለፈ ተዓምር ያስፈልጋቸዋል የሚሉ አስተያየቶች ሲደመጡ ነበር።

ኢትዮጵያ ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ ተስፋዋ እንዲለመልም ትላንት በካሜሩኗ ባፎሳማ የተካሄደውን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባት ነበር።

በኮቪድ 19 ምክንያት ያለፈውን ጨዋታ ያልተጫወተው የአስተን ቪላው በርትራንድ ትራኦሬ ወደ ሜዳ ቢመለስም ቡርኪና በጨዋታው ይህን ያህል አስፈሪ ቡድን አልነበረችም።

ቁጥር አንድ የቡርኪና ፋሶ ግብ ጠባቂ የነበረው ሄርቬ ኮፊ በኮቪድ መያዙን ተከትሎ በምትኩ የገባው ፋሪድ ጌታነህና አጋሮቹ የሞከሯቸውን ኳሶች ሲያከሽፍ ታይቷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ጌታነህ ከበደ ወደ ጎል የሰደዳቸውን ሁለት ጎል ሊሆን የሚችሉ ኳሶች እንዲሁም የዳዋ ሆቴሳን ሙከራ በማዳን ተጠባባቂው ግብ ጠባቂ ኃላፊነቱን ተወጥቷል።

የቡርኪናው ሆሳኔ ባንዴ ያገኛትን ወርቃማ ዕድል አግኝቶ ባይጠቀምም ባያላ የኢትዮጵያ ተከላካዮችንና የግብ ጠባቂውን ስህተት ተጠቅሞ የመጀመሪያዋን ጎል አስቆጥሯል።

ኢትዮጵያ የአቻነቷን ጎል ያገነኘችው በሁለተኛው አጋማሽ ዳኛው አጋዥ የተንቀሳቃሽ ምስል ዳኛ [ቪኤአር] ተመልክተው የፍፁም ቅጣት ምት ከሰጡ በኋላ ነው።

ጌታነህ ከበደ የፍፁም ቅጣት ምቷን አስቆጥሮ በ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ሁለተኛዋን ጎል ለዋሊያዎቹ አስመዝግቧል።

ተጨማሪ ጎሎች ለማስቆጠር የቡርኪና ፋሶን የተከላካይ መስመር የፈተኑት ዋሊያዎቹ ጎል ማግኘት አልቻሉም።

ኢትዮጵያ ወደ ቀጣዩ ዙር ቢያንስ ምርጥ ሶስተኛ ሆና ለማለፍ ተጨማሪ ጎሎችን ማስቆጠር ይጠበቅባት ነበር።