የአፍሪካ ዋንጫ ፈር ቀዳጆቹ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ሲታወሱ

የፎቶው ባለመብት, CAF/Getty Images/Fifa Museum
ከተጀመረ ሳምንት በሞላው የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በሜዳ ላይ ይህ ነው የሚባል ድምቀት ባይታይበትም የውድድር ፈር ቀዳጅ የሆኑት አገራት በአንድ ላይ ተሳታፊ በመሆናቸው በታሪካዊነቱ እየተጠቀሰ ነው።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በአውሮፓውያኑ 1957 የተጀመረውን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ የጠነሰሱና የጀመሩ አገራት ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ታሪክ ይዘክራቸዋል።
ከ52 ዓመታት በኋላም የውድድሩ ሦስት የመጀመሪያ ተፎካካሪ አገራት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው በአንድ ላይ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ተሳታፊ የሆኑት።
"የሦስቱም አገራት ቡድኖች በዚህ ውድድር አንድ ላይ መመለሳቸው ኩራትን እንዲሁም ጥልቀት ያለውን የውድድሩን ባህልን የሚያንጸባርቅ ነው" በማለት የስፖርት ጋዜጠኛው ባደርልዲን ባከይት ተናግሯል።
በአፍሪካ ዋንጫ ቀዳሚ ስፍራ ያላቸው ሦስቱ አገራት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውን ዋንጫ አሸናፊ ቢሆኑም ግብፅ ሰባት ጊዜ በማሸነፍ ክብረ ወሰንን ጨብጣለች። ኢትዮጵያና እና ሱዳን ደግሞ አንዳንድ ዋንጫዎችን በስማቸው አስመዝግበዋል።
እግር ኳስ በምሥራቅ አፍሪካ አገራቱ ኢትዮጵያና ሱዳን ከፍተኛ ተወዳጅነት ቢኖረውም እንዲሁም ከፍተኛ ተሰጥኦ ያላቸው ተጫዋቾች እንዳላቸው ቢነገርም ከነበራቸው ከ1960ዎቹና 70ዎቹ ታላቅነት ወደ ኋላ ቀርተዋል።
ከምሥራቅ አፍሪካ አገራት በብቸኝነት ዋንጫውን ያነሱት ጎረቤት አገራቱ ኢትዮጵያ እና ሱዳን በጨዋታው ተመሳሳይ ታሪክ አላቸው።
በአፍሪካ ዋንጫ ቀደምት ስፍራ ቢኖራቸውም ሁለቱም ድሎቻቸውን ያገኙት በአገራቸው መሬት ነበር።
ኢትዮጵያ ለ31 ዓመታት ያህል ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ማለፍ አቅቷት በአውሮፓውያኑ 2013 ነበር ወደ ውድድሩ መመለስ የቻለችው፤ በተመሳሳይ ሱዳንም እንዲሁ ለ32 ዓመታት ያህል ርቃ በአውሮፓውያኑ 2008 ነበር ተሳታፊ የሆነችው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"በእግር ኳሱ ዘርፍ ሱዳንና ኢትዮጵያን ወደ ኋላ በመመለስ ረገድ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሚና ተጫውተዋል" በማለት የሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርና 'አፍሪካን ሶከርስኬፕስ፡ ሀው ኤ ኮንቲነንት ቼንጅድ ዘ ወርልድ'ስ ጌም' መጽሐፍ ደራሲ ፒተር አሌጊ ይናገራሉ።
"ነገር ግን የአፍሪካ ዋንጫ እየተስፋፋና የዓለም ዋንጫ 2026 ማጣሪያ ባለበት በአሁኑ ወቅት የሁለቱ አገራት ቡድኖች አዎንታዊ ሁኔታዎችን እያሳዩ ያሉ ይመስላል" ሲሉ ያስረዳሉ።
በሁለቱም አገራት የተራዘሙ የእርስ በርስ ጦርነቶች፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የኢኮኖሚ ውድቀት እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተደማምረው በእግር ኳስ ጨዋታው እድገትና ሂደት ላይ በአሉታዊ መልኩ ተጽዕኖ አሳድረዋል።
ይሁን እንጂ ሁለቱም አገራት ቀደም ባለው ስኬታቸው የተነሳ የሰፈነው ኩራት ለትውልዶች እንደ አስጨናቂ ማስታወሻና ማበረታቻ ሆኖም አገልግሏል።
ኢትዮጵያ ካሜሩን እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ዋንጫ ባደረገቻቸው ሁለቱም ጨዋታዎች ሽንፈትን ማስተናገዷን ተከትሎ ለቀጣዩ ዙር የማለፊያ ዕድሏን አጥብቦታል። ነገር ግን ሱዳን ከጊኒ ቢሳዎ ጋር በነበረው ጨዋታ አቻ መውጣቷን ተከትሎ ወደ ቀጣዩ ዙር ልታልፍ ትችላለች።
በናይጄሪያ ሽንፈት ያጋጠማት ግብፅም በቀጣዩ ከዚህ ማገገም አለባት።
የአፍሪካ ዋንጫ ውልደት
በአውሮፓውያኑ 1956 የኢትዮጵያ የግብፅና የሱዳን ባለሥልጣናት ከደቡብ አፍሪካ ተወካይ ጋር በመሆን የአፍሪካ አህጉራዊ ውድድርን ለመመስረት በፖርቹጋል በነበረው የዓለም እግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ አጠቃላይ ጉባኤ ላይ ተገኙ።
የመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ በአውሮፓውያኑ 1957 በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የተካሄደ ሲሆን ሲሆን የደቡብ አፍሪካ ፌደሬሽን ከተለያዩ ዘሮች የተውጣጣ ቡድን ለመላክ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ከውድድሩ ተገለለች።
ሱዳንን የረታችው ግብፅ፣ ኢትዮጵያንም በፍፃሜው ጨዋታ 2 ለ 1 በማሸነፍ ሻምፒዮን ሆነች።
ነገር ግን የኢትዮጵያ ቡድን በአውሮፓውያኑ 1962 በተካሄደው በሦተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ያኔ አረብ ሪፐብሊክ ትባል የነበረችውን ግብፅ 4 ለ 2 በመርታት ሻምፒዮን በመሆን ድሏን አጣጣመች።
የቡድኑ አምበል ኤርትራዊው ሉቺያኖ ቫሳሎ ዋንጫውን ከአፄ ኃይለሥላሴ እጅ የተቀበለ ሲሆን ይህ ውድድር ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀችው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Fifa Museum on Twitter
"ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ዘርፍ በጣም ታዋቂ ናት፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ በጣም ተወዳጅ ስፖርት እግር ኳስ ነው" በማለት በአዲስ አበባ የሱፐር ስፓርት ተንታኝ ሰይድ ኪያር ይናገራል።
በመጀመሪያዎቹ ሁለት ውድድሮች ተሳታፊዎች የነበሩት የሦስት አገራት ቡድኖች ነበሩ ቀስ በቀስም ሌሎች አገራት መቀላቀል ጀመሩ። ይህንን በተመለከተ ሰይድ ኪያር እንደሚያምነው ያለፉትን ድሎችንም ቢሆን በጥልቀት ልንመረምረው ይገባል ይላል።
"በተጫዋቾቻችን፣ በአሰልጣኞች፣ በታሪክ ሰሪዎቻችን ኩራት እና ክብር ይሰማናል። ነገር ግን እንደ አይቮሪኮስት፣ ናይጄሪያና ቱኒዝያ በርካታ የአፍሪካ አገራት በቅኝ ግዛት ውስጥ ነበሩ። ብሔራዊ ቡድኖቻቸውም አልነበሩም" በማለት የወቅቱን ፖለቲካዊና ታሪካዊ ዳራ ማጥናት እንደሚያስፈልግ ያስረዳል።
ለሱዳን እክል የሆነው የአገር ውስጥ ፖሊሲ
ሱዳን በአውሮፓውያኑ 1970 እነ አሊ ጋጋሪ፣ ጃክሳ በመባል የሚታወቀው ናስር ኤዲን ባካተተው ወርቃማ በሚባለው የእግር ኳስ ትውልዷ ጋናን 1 ለ ምንም በመርታት ብቸኛዋን ዋንጫ አሸንፋለች።
የሱዳን ቡድን በዚያው ዓመት በሜክሲኮ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ተቃርቦ ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላ ቡድኑ በአውሮፓውያኑ 1972 ሙኒክ ኦሊምፒክ ተሳትፎ በአንፃራዊነት ጥሩ አፈጻጸም አሳይቷል።
ነገርግን በቀጣዮቹ ዓመታት 'ዘ ሴክሬታሪ በርድስ' ቡድን ውድቀት ገጠመው።
"በወቅቱ አገሪቱ ውስጥ የነበረው መረጋጋት ለእግር ኳስ ማደግ ከፍተኛ ሚና ተጫውቶ ነበር። ነገር ግን የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የምጣኔ ሀብት ችግሮች አገሪቱ በሌሎች ጉዳይ ላይ እንድታተኩር አድርጓታል" በማለት የወርቃማው ትውልድ ቡድን አባል የነበረው በአሁኑ ወቅት የ77 ዓመት እድሜ አዛውንቱ ጃክሳ ያስረዳል።

የፎቶው ባለመብት, CAF ONline
በርካታ የመንግሥት ፖሊሲዎች በእግር ኳሱ ላይ የራሳቸውን ጥላ አጥልተውበታል። ከእነዚህም መካከል የ1976ቱ አል-ሪያዳ አል-ጃማሂሪያ ወይም የቀድሞው አምባገነን ጃፋር ኒሜሪ የብሔራዊ ሊግን በማገድ እግር ኳስን ወደ አካባቢያዊ ውድድር ያወረዱበት "ስፖርት ለሰፊው ሕዝብ" ፖሊሲዎች ይጠቀሳሉ።
በምላሹም የሱዳን ታዋቂ ተጫዋቾች ወደ ጎረቤት አገራት እና ሊጎች በተለይም ወደ አረብ ባሕረ ሰላጤ አቀኑ። ከአንድ ዓመት በኋላ ፖሊሲው እንዲቀር ቢደረግም ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰ በኋላ ነበር።
"ሱዳን ማገገም ያልቻለችበት የትውልድ መቆራረጥ አጋጠመ" በማለት የኩራ ዶት ኮም ድረ ገፅ ጋዜጠኛ ባኬት ይናገራል።
ጨዋታዎቹ አካላዊ እንዲሁም የታክቲክ ለውጦች በመጡበት ወቅት የምሥራቅ አፍሪካ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ከዘመኑ ጋር መራመድ ወይ መላመድ አለመቻላቸው ከምዕራብ እና ሰሜን አፍሪካ አገራት ጋር መፎካከር አዳጋች እንዲሆን ያደረጉባቸው ሌሎች ምክንያቶችም ሊታሰብባቸው ይገባል።
"የእኛን የአጨዋወት ዘይቤ ከአካላዊ ወደ አእምሯዊ መለወጥ ከቻልን ኳስን በመቆጣጠር፣ በአጫጭር ቅብብሎች፣ በቴክኒክ ችሎታዎች ጥሩ ነን" ሲል ሰይድ ያስረዳል።
ከሜዳ ውጭ ያለው አደረጃጀት መስተከካል
የተሻሻለ የጨዋታ አያያዝ እና የረጅም ጊዜ ስልቶችን መንደፍ ያስፈልጋል። ለምሳሌም ያህል እንደ ስፔን የማለፊያ ስታይል መተግበር ወይም በአውሮፓ ሻምፒዮና ደካማ ውጤቶችን ተከትሎ ጀርመን የታዳጊዎች የእግር ኳስ ፕሮግራሞችን ማዋቀር የመሳሰሉትን አይነት ፕሮግራሞች ልንከተል ያስፈልጋል።
"ገንዘብ ማግኘት ወይም ጥሩ ተጫዎቾች እንዲኖረን ማድረግ ብቻ ሳይሆንን ይህንንም በአግባቡ ማስተዳደር እና ማቀድ ያስፈልጋል" ሲል የሞደርን ስፖርት ባልደረባ ሀሰን ኤል ሚስታዊ ይናገራል።
አንጋፋው የስፖርት ጋዜጠኛ አሁንም ግብፅ ለመሻሻል ቦታ እንዳላት ያምናል። ለዚህም በአፍሪካ ዋንጫ በመሳተፍ ክብረ ወሰንን መጨበጥ ብቻ ሳይሆን ከአውሮፓውያኑ 2006-2010 ባለው ሦስት ተከታታይ ዋንጫዎችም ድሎችን በማስመዝገብ እንዲሁም በዓለም ዋንጫም ሦስት ጊዜ መሳተፏን ይጠቅሳል።
ሌላኛው ባክሄት የሚጠቅሰው የሱዳን ትልልቅ ክለቦች የበላይነትን ሲሆን ይህም የሌሎችን ጉዳዮችንም እድገት የሚነካ ጉዳይ ነው።
አል-ሂላል እና አል-ሜሪክ የተሰኙት ቡድኖች በአህጉር አቀፍ ውድድር በአንፃራዊነት ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ቢሆንም ከሀብታም ደጋፊዎች የሚያገኙት ድጋፍ ውድድሮችን እያደናቀፈ ይገኛል።
የምዕራብ እና የሰሜን አፍሪካ አገራትም ተጫዋቾቻቸው በከፍተኛ የአውሮፓ ክለቦች እና ሊጎች መጨዋታቸው ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ሲሆን ኢትዮጵያ እና ሱዳን በበኩላቸው በአብዛኛው በአገር ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዎች ነው ያሏቸው። በካሜሮንም ለሚደረገው ውድድር እነዚህኑ ተጫዋቾችን ነው ይዘው የቀረቡት።
"ለአውሮፓ ክለቦችና ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾቹ ልምዳቸውን ወደ አገራቸው ብሔራዊ ቡድኖቻቸው ያመጣሉ" ይላል ኤል ሚስታካዊ።
ኢትዮጵያና ሱዳን ከአፍሪካ ዋንጫ ተፎካካሪነት ርቀው ቢገኙም በኢትዮጵያ በቀጠለው የርስ በርስ ጦርነትና በሱዳን ባለው መፈንቅለ መንግሥት ተመሳሳይ የፖለቲካ ፈተና ላይ ያሉት አገራት ደጋፊዎቻቸው በጨዋታቸው እንደሚያስደንቁ ተስፋን ሰንቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, CAF ONLINE












