እየተካሄደ ስላለው የአፍሪካ ዋንጫ ሊያውቋቸው የሚገቡ አንኳር ነጥቦች

ሳዲዮ ማኔ፣ ሪያድ ማሃሬዝ እና ሞሐመድ ሳለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሳዲዮ ማኔ፣ ሪያድ ማሃሬዝ እና ሞሐመድ ሳለ

የፈረንጆቹ 2022 የመጀመሪያውና ትልቁ የእግር ኳስ ድግስ በሚቀጥለው እሑድ በካሜሩን መዲና ያውንዴ ይጀመራል።

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን ጨምሮ በሌሎች ሊጎች የምናውቃቸው ኮከቦች መናኸሪያቸውን ካሜሩን አድርገዋል።

በመክፈቻው ጨዋታ አዘጋጇ ካሜሩን ቡርኪና ፋሶን ታስተናግዳለች። ለጥቆ ደግሞ ኢትዮጵያ ከኬፕ ቨርድ ትገናኘለች።

የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ሊካሄድ የነበረው ባለፈው ዓመት ጥር ነበር። ነገር ግን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በአንድ ዓመት ተራዝሞ ወደ ዘንድሮ ተሸጋግሯል።

የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ካፍ ባለፈው ወር ውድድሩን በኦሚክሮን ዝርያ መስፋፋት ምክንያት ያራዝመዋል ተብሎ የተናፈሰው ወሬ ሃሰት ነው ማለቱ ይታወሳል።

የቀድሞው የአርሰናልና የእንግሊዝ አጥቂ የነበረው ኢያን ራይት መገናኛ ብዙሃን ስለአፍሪካ ዋንጫ ሲዘግቡ "በንቀትና የዘረኝነት መንፈስ ተላብሰው ነው" ሲል ወቅሶ ነበር።

የጨዋታው ሰንጠረዥ ምን ይመስላል?

የአፍሪካ ዋንጫ 24 ብሔራዊ ቡድኖችን ያሳትፋል። ይህ በውደድሩ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ይህ ማለት እያንዳንዳቸው አራት ቡድኖችን ያቀፉ ስድስት ምድቦች አሉት ማለት ነው። ከእነዚህ መካከል አንደኛና ሁለተኛ የሚወጡት ወደ ቀጣዩ ዙር በቀጥታ ሲያልፉ፤ አራት ምርጥ ሶስተኛ ቡድኖችም ወደ ዙር 16ን ይቀላቀላሉ።

የምድብ ጨዋታዎች ቀን 10 ሰዓት እንዲሁም ምሽት 1 ሰዓትና ማታ 4 ሰዓት ይከናወናሉ። በቀጣዩ የጥሎ ማለፍ ውድድር ጊዜ ደግሞ `ጨዋታዎቹ ማታ 1 እና 4 ሰዓት ይታያሉ።

ለዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ጥቅም ላይ የሚውለው ኳስ ቶጉ የሚባል ካሜሩን ውስጥ ታዋቂ ከሆነ ጨርቅ ስሙን ያገኘ ኳስ ነው።

ለዋንጫ እነማን ይፎካከራሉ?

በማንችስተር ሲቲው የክንፍ ተጫዋች የምትመራው ያለፈው የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ አልጄሪያን ለዋንጫው አለማጨት ከባድ ነው።

የሳድዮ ማኔ ሃገር ሴኔጋል በአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች ሰንጠረዥ አናት ላይ የምትገኝ ሲሆን ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ በአልጄሪያ ተረታ ሁለተኛ መሆኗ አይዘነጋም።

ያለፉትን 34 ጨዋታዎች ሽንፈት ካላስተናገደችው አልጄሪያና ከሴኔጋል ቀጥሎ በወቅቱ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ኮከብ ሞሐመድ ሳላህ የምትመራው ግብፅም ስሟ ለዋንጫ ከሚቀናቀኑ መካከል ይነሳል።

ግብፅ የአፍሪካ ዋንጫ ለሰባት ጊዜ በማንሳት የሚገዳደራት የለም።

ጋና እና ናይረጄሪያ በአፍሪካ በጣም ውጤታማ ከሚባሉ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ቢሆኑም ለ2022 የዓለም ዋንጫ ያደረጉት ጉዞ ግን ብዙም አሳማኝ አልነበረም።

ለስድስተኛ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ለማንሳት የምትፋለመው ካሜሩን ደግሞ በሕዝቧ ፊት ዋንጫውን ለማስቀረት ትጥራለች።

የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ጨዋታዎችን ያለምንም ሽንፈት ያከናወነችው ማሊ የውድድሩ ክስተት ልትሆን ትችላለች።

አይቮሪ ኮስት፣ ሞሮኮና ቱኒዚያም ከዚህ በፊት ውድድሩን ያነሱ ቡድኖች ሲሆኑ ኮሞሮስና ጋምቢያ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሳተፉ ይሆናል።

ውድድሩ የሚካሄድበት ወቅት

አንዳንድ የአውሮፓ ሊግ ክለቦች ተጫዋቾችን በዚህ ወቅት አንለቅም በማለት ብዙ ግርግር አስነስተው ነበር።

ዋትፈርድ የተሰኘው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለብ ለምሳሌ የናይጄሪያውን ኢማኔኤል ዴኒስ አልለቅም በማለት ክርክር አስነስቶ ነበር።

ቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ በሚቀጥለው ዓመት ሰኔና ሐምሌ በአይቮሪ ኮስት አዘጋጅነት ይካሄዳል።

የፊፋው አለቃ ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የብሔራዊ ቡድን ውድድሮች በመስከረምና ኅዳር መካከል ይከናወኑ የሚል ሐሳብ አቅርበዋል።

የኮሮናቫይረስ ጉዳይ?

ወረርሽኙ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ጥላውን ማንዣበቡ አልቀረም። ካፍም የታዳሚዎችን ቁጥር 60 በመቶ ቀንሷል።

አዘጋጇ ካሜሩን የምታደርጋቸው ፍልሚያዎች 80 በመቶ ታዳሚ እንዲኖራቸውና ሁለት ጊዜ የተከተቡና የኮቪድ ውጤታቸው ኔጌቲቭ የሆኑ ሰዎች ናቸው ወደ ስታድዬም መግባት የሚችሉት።

እስካሁን 2 በመቶ ሕዝቧ ብቻ የተከተበው ካሜሩን በሚቀጥሉት 30 ቀናት ሕዝቧ ለጨዋታው በማለት ወደ ክትባት ጣቢያዎች ያመራ ይሆን የሚለው አጓጊ ሆኗል።

በኢትዮጵያ ምድብ የምትገኘው ኬፕ ቨርደን ጨምሮ የተወሰኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫቾች እንዲሁም ጋምቢያ ልምምድ እያደረጉ በሚገኙበት ካምፕ ወረርሽኙ አግኝቷቸው ነበር።

የ2019 የአፍሪካ ዋንጫን እንድታስተናግድ ተመርጣ የነበረችው ካሜሩን በቂ መሠረተ ልማት የላትም ተብሎ ውድድሩ ወደ ግብፅ መዛወሩ ይታወሳል።

ካሜሩን የደህንነት ጉዳይም ያሳስባታል። በደቡብ ምዕራብ የምትገኘው የሊምቤ ከተማ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በታጣቂዎች ጥቃት እየታመሰች ትገኛለች።

ውድድሩን እንዴት መከታተል እችላለሁ?

ቢቢሲ፤ ሁለት የሩብ ፍፃሜ ፍልሚያዎች፣ ሁለት የግማሽ ፍፃሜ ግጥሚያችና ፍፃሜውን ጨምሮ 10 የተመረጡ ጨዋታዎችን ያስተላልፋል።

ስካይ ስፖርት የተሰኘው ጣቢያ ሁሉንም ጨዋታዎች በቴሌቪዥን ሲያስተላልፍ፤ ሱፐርስፖርት፣ ቤይንስፖርትና ካናልፕላስ ካሜሩን ተገኝተው ውድድሩን በቴሌቪዥን መስኮት ከሚያቀርቡ መካከል ናቸው።

የቢቢሲ ስፖርት ድረ-ገፅ ደግሞ ከስር ከስር ሁሉንም ክስተቶች እየተከታተለ ይዘግብላችኋል።