የተራበች እናቱ ልትመግበው ያልቻለችው ጨቅላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
- ፀሐፊ, በካትሪን ብያሩሃንጋ
- የሥራ ድርሻ, የቢቢሲ አፍሪካ ዘጋቢ
የሦስት ወሩ ጨቅላ ሱራፌል መአረግ በጦርነት ክፉኛ በተጎዳችው ትግራይ ክልል ትልቁ ሆስፒታል ውስጥ እርዳታ ባጣ መልኩ ተንጋሏል።
ዓይኖቹ በሰፊው ተከፍተዋል፤ የጎድን አጥንቶቹ በተሸበሸበው ቀጭን ቆዳው ላይም ተጣብቆ ይታያል።
ሱራፌል በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች በተዛመተውና ለ14 ወራት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነትም ምክንያት በምግብ እጦት ከሚሰቃዩ በርካታ ህፃናት መካከል አንዱ ነው።
በትግራይ ክልል መዲና መቀለ በሚገኘው የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሱራፌልን የሚያክሙት የሕፃናት ሐኪም ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት ክብደቱ 2.3 ኪሎ ግራም የሚመዝን ሲሆን ይህም ሲወለድ ከነበረው በአንድ ኪሎ ያነሰ ነው።
ማስጠንቀቂያ፡ ለእንዳንድ አንባቢዎች ከታች ያለውን ምስል የሚረብሽ ሆኖ ሊያገኙት ይችላሉ
የሆስፒታሉ ሠራተኞች ባሳተሙት የህክምና ማስታወሻ መሰረት የእናቱ ጡት በመድረቁ ወተት ሊያመነጭ አልቻለም። ወላጆቹ በአሁኑ ወቅት ሥራ ስሌላቸውም ለህፃኑ የሚሆን የህጻናት የዱቄት ወተትም የመግዛት አቅም የላቸውም።
በዋናነት የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች እንደሚናገሩት እንደ ሱራፌል ያሉ ህፃናትን ለመንከባከብ የሚያስፈልጉ አልሚና ገንቢ ምግቦች በማለቅ ላይ ናቸው።
"ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ ማንኛውም ቁሳቁስ ከመጣ ስድስት ወራትን አስቆጥሯል" በማለት ቤተሰቦቹ ላይ ጥቃት ሊሰነዘርባቸው ይችላል በሚል ስጋት ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀን የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያ ተናግሯል።
"ለመጨረሻ ጊዜ በሰኔ ወር የደረሰንን ቁሳቁሶች ጨርሰናል። በአሁኑ ወቅት ሁሉ ነገር እያለቀ ነው" ሲልም አክሏል።
በዚህ ሳምንት የአይደር ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች ለዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች እርዳታን በመሻት ሪፖርታቸውን አቅርበዋል።
በሪፖርቱ ውስጥ ከተካተቱት አንዱ ደግሞ የጨቅላው የሱራፌል ጉዳይ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የህክምና ባለሙያዎቹ እንደተናገሩት ወደ ሆስፒታሉ ከሚመጡት ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት በተመጣጠነ ምግብ ዕጥረት የሚሰቃዩ ናቸው።
ይህ አሀዝ ደግሞ በአውሮፓውያኑ 2019 ከነበረው በዕጥፍ ጨምሯል።
በአጥንቱ ብቻ የቀረው የአራት ዓመቱ ህፃን መድኃኒዬ የምግብ ቱቦ በአፍንጫው ተተክሎለት በሆስፒታል አልጋ ላይ ተኝቷል።
በህክምና መረጃው መሰረት መድኃኒዬ በምግብ እጥረት መሰቃየት የጀመረው ወታደሮች በቤተሰባቸው ላይ ጥቃት ሰንዝረው በሬያቸውን በማረድ፣ ንብረታቸውን አውድመውና ዘርፈው መሄዳቸውን ተከትሎ ነው።
ባለፈው ዓመት በጥቅምት መጨረሻ በህወሓትና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በትግራይ ክልል የመገናኛ ዘዴዎች በመቋረጣቸው ቢቢሲ በህክምና ባለሙያዎቹ የቀረበውን ሪፖርት በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም። ከሐምሌ ጀምሮም ጋዜጠኞች ወደ ትግራይ መግባት አልቻሉም።
ያለ ህክምና መገልገያ በባዶ እጅ ደም መፍሰስን ማቆም
የህክምና ባለሙያዎቹ በሪፖርታቸው ላይ እንዳሰፈሩት የፌደራል ኃይሎች እና አጋሮቻቸው ለስድስት ወራት ያህል የጣሉት "እገዳ" ለከፋ የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁሶች እጥረት እንዲያጋጥም ምክንያት ሆኗል ሲሉ ወቅሰዋል።
ይህም መቅረት የሚችሉ ሞቶችን እያስከተለ ነው ብለዋል በሪፖርታቸው።
"ክልሉ በከበባ ላይ በመሆኑ ሌሎች 35 ታማሚዎች የዲያሊስስ ህክምና በማጣት ህይወታቸው አልፏል" ይላል ሪፖርቱ።
ደም መፍሰስ ሲያጋጥም ያለ ህክምና መሳሪያ በባዶ እጃቸው ለማስቆም እንደተገደዱም ይናገራሉ። የእጅ ጓንቶችን በማጠብና እንደገና በመጠቀም እንዲሁም የራሳቸውን ፀረ-ተህዋሲያን ፈሳሾች በመስራት ላይ መሆናቸውም በሪፖርቱ ተካትቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ለገሰ ቱሉ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ ሪፖርቱ የህወሓትን "ትርክት ለመገንባት" የሚፈልግና በትግራይ ላይ ህወሓት ገደብ ተጥሏል ከሚለውም ጋር "ይመሳሰላል" ብለዋል።
"ከመንግሥት በኩል በትግራይ ላይ ሆን ተብሎ የተጣለ፣ ሕዝባችንን የሚጎዳ እገዳ የለም " ብለዋል።
ነገር ግን ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ የእርዳታ ድርጅቶች ወደ ትግራይ እርዳታ ማስገባት ባለመቻላቸው ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ታኅሣሥ 21/2014 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት መሰረት እርዳታ የጫኑ መኪኖች ከታኅሣሥ አጋማሽ ጀምሮ ወደ ትግራይ አልገቡም።
ለዚህም በቢሮክራሲ መዘግየትና የፀጥታ ችግሮች ምክንያት መሆኑም ተጠቅሷል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም በክልሉ ያለውን ከአምስት ሚሊዮን በላይ እርዳታ ፈላጊ ሕዝብ ለመድረስ ከታሰበ በየሳምንቱ 100 እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ክልሉ ሊገቡ ይገባል ቢልም፣ እንደ ኦቻ ሪፖርት ወደ ክልሉ መግባት የቻለው ከሚያስፈልገው አቅርቦት ውስጥ 12 በመቶ ብቻ ነው።
ቢቢሲ የዕርዳታ አቅርቦትን አስመልክቶ አቶ ለገሰን የጠየቃቸው ሲሆን እሳቸውም "ለትግራይ ምግብና መድኃኒት ሊያደርሱ ወደ ክልሉ ከሄዱት 1 ሺህ 100 መኪኖች ውስጥ ከ840 በላይ የሚሆኑት እስካሁን አልተመለሱም። ህወሓት ሕገወጥ ምልምሎችን፣ ወታደሮችንና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ለማጓጓዝ ይጠቀምባቸዋል ተብሎ ይጠረጠራል" ብለዋል።
ህወሓት ዕርዳታ እንዳይደርስ እያደናቀፈ ነው የሚለውን ውንጀላ አይቀበለውም። ነገር ግን ሠራዊቱ በአማራና በአፋር ክልሎች ተቆጣጥሯቸው በነበሩ አካባቢዎች የዕርዳታ ማከማቻዎችንና የጤና ተቋማትን ዘርፏል የሚል ክስ ቀርቦበታል።
የአይደር ሆስፒታል ዶክተር ለቢቢሲ እንደተናገረው በተፈጠረው ቀውስ የሆስፒታሉ ሠራተኞች ቤተሰቦች ሳይቀር እየተጎዱ ነው።
"ልጄ የትርፍ አንጀት አለበት። ነገር ግን ህክምና ማግኘት አልቻለም" ብሏል።
እጥረቱ በዚሁ ከቀጠለ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ሁሉንም ቀዶ ህክምና ከማቆም ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ተናግሯል።
"ቁሳቁስ የለንም። እዚህ ላይ ደርሰናል። ለዚህም ነው ለዓለም ለማሳወቅ የፈለግነው። አብዛኞቹ ሆስፒታሎች እየተዘጉ ነው" ብሏል።












