የጦርነቱ ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም 5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መመመደቡ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, J. Countess
በሰሜኑ ኢትዮጵያ በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም አምስት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መመደቡን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ገንዘብ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳስታወቀው ይህ የአምስት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን አስታውቆ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደጸደቀ በቀጥታ ሥራ እንደሚውልም አመልክቷል።
ከመንግሥት በጀት በተጨማሪ የዓለም ባንክን ከመሳሰሉ የልማት አጋሮች ለመልሶ ማቋቋሙ የገንዘብ ድጋፍ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሚመራው የብሔራዊ መልሶ ማቋቋሚያ ሴክሬታሪያት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
የመልሶ ማቋቋም ሴክሬታሪያቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባውን ታኅሣሥ 15/2014 ዓ.ም ባደረገበት ወቅት፣ የመልሶ ማቋቋሙ መርሀ ግብር የተቀናጀ፣ በፕሮግራም ተግባራዊ የሚደረግ፣ ተጠያቂነት ባለው መልኩና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ባተኮረ መልኩ የሚሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ መግለጻቸው ሰፍሯል።
በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት ለማወቅና እንዲሁም በገንዘብ ለመተመን የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት ለማድረግ የሚያስችል የመነሻ ሃሳብ በገንዘብ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ለመልሶ ማቋቋም ሴክሬታሪያት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ቀርቧል።
ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተጎጂዎች በተጨማሪ በሌሎች ክልሎች በግጭት የተፈናቀሉትም በመልሶ ማቋቋም መርሃ ግብሩ እንዲካተቱበትና፣ የሀብት አሰባሰቡ ወጥ በሆነ መንገድ እንዲቀናጅና፣ ክልሎች የሚሳተፉበት መንገድ እንዲመቻችና የግሉ ዘርፍ እንዲሁም ዲያስፖራው ይካቱ የሚል ሃሳቦችም ከአባላቱ መነሳቱ ተነግሯል።
የብሔራዊ መልሶ ማቋቋም ሴክሬታሪያት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት የትምህርት፣ የጤና፣ የፕላንና ልማት፣ የውሃና ኢነርጂ፣ የኢንዱስትሪ፣ የሴቶችና ማኅህበራዊ ጉዳይ፣ የሥራና ክህሎት፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሮች እንዲሁም ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል መሥሪያ ቤት አመራሮች በዚህ ስብሰባ ተሳታፊ ሆነዋል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።
በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች በተለያየ ደረጃ እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግና የስደተኛ ሕግ ጥሰቶችን መፈፀማቸውን የመብት ተቆርቋሪዎች ያወጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
ከአስራ ሦስት ወራት በላይ ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ እና ሌሎች አጋሮች ጥረት ቢያደርጉም ፍሬ አላፈራም።












