በኢትዮጵያ 22 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ሰብአዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡ የተባበሩት መንግሥታት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ወደ 22 ሚሊዮን የሚደርሱ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሰዎች ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (ዩኤን ኦቻ) አስታወቀ።
በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር እጨመረ መምጣቱን ድርጅቱ ያወጣው ሪፖርት ይጠቁማል።
በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ነፍስ አድን የምግብ እርዳታ የሚጠብቁ ሰዎች ቁጥር አምና ነሐሴ ላይ ከነበረው 8.1 ሚሊዮን ዘንድሮ መስከረም ላይ ወደ 9.4 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሪፖርት ያሳያል።
በጦርነቱ ሳቢያ በአማራ ክልል እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር በአንድ ጊዜ ወደ 3.7 ሚሊዮን አሻቅቧል።
በጦርነቱ እንዲሁም በድርቅ ምክንያት በኢትዮጵያ በቀጣዩ የፈረንጆች 2022 ላይ እርዳታ የሚሹ ዜጎች ቁጥር እንደሚጨምር ኦቻ አስታውቋል።
"ግጭት፣ ድርቅ፣ የአንበጣ ወረርሽኝ እና በሽታዎች ተደማምረው ሕይወታቸውን በእርዳታ የሚገፉ ሰዎችን ቁጥር ጨምረውታል" ይላል ሪፖርቱ።
2022 ላይ ኦቻ ለ22.3 ዜጎች እርዳታ የማቅረብ ዕቅድ አለው።
በድርቅ ተጠቂ የሆኑት የምሥራቅ እና ደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎችን ጨምሮ በጦርነቱ የተጎዱ ክልሎችም አፋጣኝ ድጋፍ ይሻሉ።
"በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ያለው ድርቅ እጅግ አሳሳቢ ነው" ሲል ኦቻ በሪፖርቱ ጠቅሷል።
የምግብ እጥረት መለኪያን ተጠቅሞ ድርጅቱ በሠራው ዳሰሳ መሠረት በደቡብ እና ምሥራቅ ኢትዮጵያ ያለው ችግር ደረጃ 3 እና ደረጃ 4 የሚባሉት ላይ ደርሷል።
ለዚህ አሳሳቢ የምግብ እጥረት ምክንያቱ በዋነኛነት የዝናብ እጦት ነው።
አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የውሃ እጥረት ገጥሟቸዋል። የቀንድ ከብቶቻቸውም ለከፍተኛ አደጋ ተጋልጠዋል። የገቢ መጠን ማሽቆልቆል ደግሞ ሌላው ችግር ነው።
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ኤጀንሲን አጣቅሶ ኦቻ እንዳለው፤ በእነዚህ አካባቢዎች የቀንድ ከብት ዋጋ ከዚህ ቀደም ከነበረው ዝቅ በማለቱ ነዋሪዎች ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ገጥሟቸዋል።
"የቀንድ ከብቶች አካለ መጠንም ቀንሷል። ከብቶች ቶሎ ከመሞታቸው ባሻገር ድርቅ ወደሌለባቸው አካባቢዎችም እየተሰደዱ ነው" ብሏል።
ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች እርዳታ ለማቅረብ ከወዲሁ ዝግጅት መደረግ እንዳለበት የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቁሟል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ ዑመርን ጠቅሶ እንዳለው፤ በቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥ 3.3 ሚሊዮን ሰዎች ለአስጊ የምግብ እጥረት ይጋለጣሉ።
አሁን ላይ 2.2 ሚሊዮን ሰዎች የውሃ እጥረት ገጥሟቸዋል። 173,000 ሕጻናት ደግሞ የተመጣጠነ ምግብ እያገኙ አይደለም።
ኦቻ በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች በሁለተኛ ዙር እርዳታ ለመስጠት 2 ሚሊዮን ዶላር እንደመደበ ይፋ አድርጓል።
በዋነኛነት ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት እና ለነፍሰ ጡር እናቶች እርዳታ እንደሚቀርብም አክሏል።
በመላው ኢትዮጵያ ወደ አራት ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ይህም ዘንድሮ የተፈናቀሉትን 1.5 ሚሊዮን ሰዎች ይጨምራል።
ወደ 60 በመቶ የሚሆኑ ተፈናቃዮች የሚገኙት ከአካባቢያቸው ውጪ ባሉ ማኅበረሰቦች ሥር ተጠልለው እንደሆነም የኦቻ ሪፖርት ይጠቁማል።
"አብዛኞቹ ሰዎች የተፈናቀሉት ግጭት በመሸሽ ነው። በ2021 አጋማሽ ከቤት ንብረታቸው ከተፈናቀሉ 2.7 ሚሊዮን ሰዎች በኋላ የተፈናቃዮች ቁጥር ጨምሯል። ከጥቅምት ወዲህ በርካቶች እየተፈናቀሉ ያሉት ከምዕራብ ትግራይ ነው" በማለት ድርጅቱ ገልጿል።
ጥቅምት ላይ በተሠራው ዳሰሳ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከ10,000 በላይ ሰዎች በደቡብ ምዕራብ ትግራይ ተጠልለዋል። ቁጥሩ ይጨምራል ተብሎም ይሰጋል።
ከተፈናቃዮቹ መካከል አብዛኞቹ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያን እና የታመሙ ሰዎች እንደሆኑም ተጠቁሟል።
ከመስከረም ወዲህ ከአማራ ክልል 542,000 ሰዎች፣ ከአፋር ክልል ደግሞ 255,000 ሰዎች ተፈናቅለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ እርዳታ ለማዳረስ ኦቻ 614 ሚሊዮን ዶላር እንዳወጣና ገንዘቡ ከሚያስፈልገው በጀት አንጻር በቂ እንዳልሆነ ድርጅቱ ተናግሯል።
ለሚያከናውነው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ለጋሽ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉለትም ጥሪ አቅርቧል።














