ፕሬዝዳንት ባይደን ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት የሚያግደውን ውሳኔ ፈረሙ

ልብስ የሚሰፉ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, EYERUSALEM JIREGNA

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስት የአፍሪካ አገራት አጎዋ ተብሎ ከሚታወቀው የአፍሪካ የእድገትና የንግድ ዕድል ድንጋጌ ተጠቃሚነት እንዲሰረዙ የቀረበላቸውን ውሳኔ በፊርማቸው አጸደቁ።

ይህ አጎዋ የተባለው አሰራር የአፍሪካ አገራት የተለያዩ ምርቶችን ወደ አሜሪካ ገበያ ከቀረጥና ከታሪፍ ነጻ በሆነ ሁኔታ በማስገባት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው።

ይህ የውሳኔ ሐሳብ የአሜሪካ መንግሥት የንግድ ፖሊሲ ከፍተኛ ባለሥልጣን በሆኑት በአምባሳደር ካትሪን ታይ በኩል ነበር ይፋ የተደረገው።

ለዚህ ውሳኔ አንድ ዓመት ያስቆጠረው በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ምክንያት እንደሆነና በሚቀጥለው ሳምንት ከሚጀምረው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት በፊት መሻሻሎች ከታዩ የውሳኔ ሐሳቡ ተግባራዊ እንደማይሆን ባለሥልጣኗ አመልክተው ነበር።

ይህ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተፈረመበትና ተግባራዊ እንዲሆን የተላለፈው ውሳኔ ከአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ጀምሮ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ውጭ ያደርጋታል።

ይህ የውሳኔ ሐሳብ በቀረበበት ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት አሜሪካ ተገቢ ያልሆነ ጫናን ለማሳደር እየሞከረች መሆኗን በመግለጽ፣ እርምጃው በአጎዋ አማካኝነት ሲገኙ የነበሩ ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታዎችን፣ ሴቶች እና ሕጻናትን ይጎዳል ብሏል።

ሁለት አስርት ዓመታት በቆየው የአጎዋ ከቀረጥ እና ታሪፍ ነጻ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑ 38 አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ የነበረች ስትሆን፣ በየዓመቱ እስከ ከ150 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የቆዳ፣ ጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ምርቶችን ወደ አሜሪካ ስትልክ ቆይታለች።

ኢትዮጵያ የአጎዋ ተጠቃሚ ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ ወደ አሜሪካ የምትልካቸው ምርቶች መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሄደ ሲሆን፣ ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድልን ፈጥሯል።

ከዚህም ውስጥ የአልባሳትና የቆዳ ምርቶች ኢንዱስትሪ ለ200 ሺህ ዜጎች ቀጥተኛ የሥራ ዕድልን የፈጠረ ሲሆን 80 በመቶዎቹ ደግሞ ሴቶች ናቸው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በቅርቡ በአፍሪካ ጉብኝት ባደረጉበት ጊዜ ስለውሳኔው ተገቢነት ተጠይቀው "በአጎዋ ስምምነት መሠረት በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ውስጥ የተሳተፈች አገር ከስምምነቱ ተጠቃሚ እንደማትሆን ተመልክቷል" ብለው ነበር።

ጨምረውም "በኢትዮጵያ ያለው ችግር የሚቀጥል ከሆነ ከጄነዋሪ 1 (ታህሳስ 23) ጀምሮ በሕጉ መሠረት አጎዋ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ጥቅም ማንሳት አለብን" ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ የእገዳ ውሳኔው ሐሳብ ሲቀርብ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ "አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ከቻለች በተጠቃሚነቷ ትቀጥላለች" ሲሉ ካተሪን ታይ አመልክተው ነበር።

የአሜሪካ መንግሥት በአገሪቱ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እያሳደረ ሲሆን፣ የአገሪቱ ከቀረጥ ነጻ ተጠቃሚነትም ጥያቄ ውስጥ መውደቁ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነጻ በሆነ መንገድ ወደ አሜሪካ በመላክ ላይ ያሉ የጨርቃ ጨርቅ አምራች ፋብሪካዎች እርምጃውን ተገቢ እንዳልሆነና በኢንዱስትሪዎቹ እየሰሩ የሚተዳደሩ ሰዎችን የሚጎዳ መሆኑን በመግለጽ ሲከራከሩ ቆይቷል።

በቅርቡ የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደራቸው ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ለማስጣት ማሰቡ ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ውሳኔው እንዳይጸድቅ የሚጠይቅ ደብዳቤ መጻፋቸው ተነግሮ ነበር።

የውሳኔ ሐሳቡ በቀረበበት ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያን ከአጎዋ ለማገድ ያሳለፈው ውሳኔ እንዳሳዘነው ገልጾ ነበር።

አሜሪካ ለአፍሪካ አገራት ከዘረጋችው የቀረጥና ታሪፍ ነጻ የንግድ ተጠቃሚነት ለማገድ ያሳለፈችው ውሰኔ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ማሊና ጊኒን ያካትታል።

ለአሜሪካ ውሳኔ ምክንያት የሆነው በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በሁሉም ወገኖች መፈጸማቸውን የመንግሥታቱ ድርጅትና የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ሲገልጹ መቆየታቸው ነው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ባለሥልጣናት ላይ ከወራት በፊት የቪዛ እገዳ መጣሉን ያሳወቀ ሲሆን ፕሬዝዳንት ባይደንም የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችል ትዕዛዝ መፈረማቸው ይታወሳል።

አሜሪካ እየወሰደችው ያለው እርምጃ ለአማጺያኑ ያደላና ፍትሃዊ ያልሆነ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥ በተደጋጋሚ ሲቃወም ቆይቷል።