የኢትዮጵያ ከአግዋ መታገድ በሥራ ዕድል እና በውጭ ምንዛሪ ምን ያጎድልባታል?

የፎቶው ባለመብት, EYERUSALEM JIREGNA
የአሜሪካ መንግሥት ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገራት የዘረጋው ከቀረጥ ነጻ ዕድል ተጠቃሚ የነበረችው ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሳቢያ ከዚህ ዕድል መታገዷ ተሰምቷል።
በ2005 ዓ.ም የአግዋ ፎረምን ያስተናገደችው ኢትዮጵያ በአግዋ በኩል ለሁለት አስርት ዓመታት የተለያዩ ምርቶችን [በስፋት ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት] ለአሜሪካ ገበያ በማቅረብ ለመቶ ሺዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በሚሊዮኖች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ ስታገኝ ቆይታለች።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2000 ይፋ በተደረገው በዚህ የቀረጥ ነጻ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑ 38 አገራት አንዷ የነበረችው ኢትዮጵያ የተለያዩ ምርቶችን ለአሜሪካ ገበያ ስታቀርብ ቆይታ ከዚህ ተጠቃሚነት መታገዷ የውጭ ምንዛሪ ማጣትንና የሥራ ዕድል ማጥበብን ጨምሮ በርካታ ጉዳቶችን እንደሚያስከትልባት ይታመናል።
ኢትዮጵያ ከጆ ባይደን አስተዳደር ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች በኋላ የአግዋ ዕድልን የተነጠቀች ሲሆን በኢትዮጵያ ያለው ችግር አሳሳቢ ነው የምትለው አሜሪካ አገሪቱ በሚቀጥሉት 60 ቀናት ውስጥ የሚጠበቅባትን የምታከናውን ከሆነ ወደ አግዋ ዳግም ልትመለስ እንደምትችል አስታውቃለች።
አግዋ ምንድን ነው?
The African Growth and Opportunity Act [በግርድፍ ትርጉሙ የአፍሪካ ዕድገት እና ዕድል ድንጋጌ] ወይም አግዋ በአሜሪካ የተቀመጠውን መስፈርት የሚያሟሉና ከሰሃራ በታች ለሚገኙ አገራት ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነጻ ለአሜሪካ ገበያ እንዲያቀርቡ የሚያስችል ዕድል ወይም ችሮታ ነው።
በአግዋ የተካተተ ማንኛውም አገር የሕግ የበላይነትን ለማስፈን መስራት፣ የሰብአዊ እና የሠራተኛ መብቶችን ማክበር፣ ፖለቲካዊ ብዝሃነትን ማስተናገድ፣ ገበያ መር ኢኮኖሚን መከተል ወይም ለመከተል መስራትን ጨምሮ የተለያዩ መስፈርቶች የተቀመጡ ሲሆን መስፈርቶቹ የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን እና በዕድሉ ለመቆየት የሚያስችሉ እንደሆነ በአዋጁ ተቀምጧል።
አግዋ እንደ አውሮፓውያኑ በግንቦት 18/2000 በአሜሪካ ኮንግረንስ የጸደቀ ሲሆን በ2025 ክለሳ ይደረግበታል። ይህ የንግድ ዕድል ሥርዓት እንደ አውሮፓውያኑ ከ2000 እስከ 2008 እንዲተገበር ታስቦ የተጀመረ ቢሆንም፣ በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳት የነበሩት ጆርጅ ቡሽ እስከ 2015 እንዲራዘም ፈርመዋል።
በ2015 ላይ ደግሞ ይህ ዕድል እስከ 2025 እንዲራዘም የያኔው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በፊርማቸው አጽደቀዋል።
በአሜሪካ መንግሥት ችሮታ የቀረበውና አፍሪካን በሚመለከት የአገሪቱ የንግድ ፖሊስ አካል የሆነው አግዋ ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት እና በአሜሪካ መካከል የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስርን ማበረታታት፤ በአገራቱ ያሉ ንግዶችን ለአሜሪካ ኢንቬስተሮች ክፍት ማድረግ እንዲሁም ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያን እና ዕድገትን መደገፍ ቀዳሚ ግቦቹ ናቸው።
ኢትዮጵያ ከአግዋ ምን ተጠቀመች?
እንድ አውሮፓውያኑ በ2019 በአግዋ ሥርዓት አማካኝነት አሜሪካ 8.4 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ማስገባቷን የአሜሪካ ፌዴራል መንግሥት የንግድ ጉዳዮች አማካሪ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ይህ ተቋም ባወጣው መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ በዚያው ዓመት 246 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በአግዋ አማካኝነት ወደ አሜሪካ ልካለች።
ከተላኩት ምርቶች አብዛኛውን የሚሸፍኑት አልባሳት፣ አበባ እና ጫማን የመሳሰሉ ናቸው። ናይጄሪያ በአግዋ ዕድል 3.1 ቢሊዮን ዶላር የሚገመቱ ምርቶችን [በብዛት ድፍድፍ ነዳጅ] በመላክ የዚያ ዓመት የዕድሉ ቀዳሚ ተጠቃሚ ነበረች።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢኮኖሚ አማካሪ ማሞ ምህረቱ (ዶ/ር) ፎሬይን ፖሊስ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ኢትዮጵያ በአግዋ ሥርዓት በኩል እንደ ለአሜሪካ ገበያ ያቀረበችው ምርት ወደ 150 ሚሊዮን ዶላር ማደጉን አስፍረዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ከላከችው አጠቃላይ ምርት ግማሹን የሚሸፍን ነው። አግዋ ይፋ በሆነበት ዓመት ከኢትዮጵያ የተላከው ምርት 28 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሲሆን ከ20 ዓመታት በኋላ የተላከው ምርት ከአምስት እጥፍ የላቀ ነው።
ሂደቱም ለኢትዮጵያ ዘላቂ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እና የዜጎች የሥራ ዕድል ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።
ማሞ ምህረቱ በጽሁፋቸው በአግዋ ዕድል አማካኝነት ኢትዮጵያ ከምትልካቸው ምርቶች አልባሳትና የቆዳ ምርቶች ኢንዱስትሪ ብቻቸውን ለ200 ሺህ ዜጎች ቀጥተኛ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸው ከተጠቃሚዎቹ 80 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
አማካሪው 30 ሺህ ሠራተኞች ያሉትን የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ለአብነት በማንሳት 95 በመቶ የሚሆኑት ሠራተኞች ሴት መሆናቸው እና የሥራ ልምድ ለሌላቸው ወጣቶች ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል።
አጠቃላይ የኢንዱስትሪ ማዕቀፉ ደግሞ እንደ ትራንስፖርትና ሆቴል ካሉ አነስተኛ ቢዝነሶች እስከ ጥሬ ዕቃ አቅራቢ ባለው ትስስር ከአንድ ሚሊዮን ለሚልቅ ዜጋ የገቢ ምንጭ መሆኑን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሯ ሌሊሴ ነሜ ለአሜሪካ መንግሥት በጻፉትና በኮሚሽኑ ማኅበራዊ ገጾች በተሰራጨ ግልጽ ደብዳቤ፣ አግዋ አሜሪካን ጨምሮ ታላላቅ የዓለም ኩባንያዎች ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ዕድል መስጠቱን አስታውሰዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱ ጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት 80 በመቶ በአግዋ በኩል የገበያ መዳረሻቸው አሜሪካ እንደሆነ ያነሱት ኮሚሽነሯ፣ አግዋ በከተሞች ዙሪያ ለሚኖሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ዜጎች የገቢ ምንጭ ሆኖ ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ እያገዘ እንደሆነ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከገጠር ወደ ከተማ ሥራ ፍለጋ ለሚፈልሱና በርካታ ሴቶች የእንጀራ ገመድ መሆኑንም በደብዳቤያቸው አስፍረዋል።
ኢትዮጵያ ከአግዋ ዕድል መታገዷ ከመገለጹ ከሳምንታት በፊት በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ስለ አግዋ አስተያየት የሰጡት ማሞ ምህረቱ አግዋ ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪን እንድታስፋፋ አስተዋፅኦ እንደነበረው ጠቁመዋል።
"ከጥቂት ዓመታት በፊት የነበረን የኢንዱስትሪ ፓርክ አንድ ብቻ ነበር። አሁን ግን በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መገንባት ችለናል። ያንንም ተከትሎ ብዙ ሠራተኞች ቀጥረናል ያንንም ተከትሎ የወጪ ንግዳችንን ማስፋት ችለናል በግብርና ላይ መሰረት ያደረገው ኢኮኖሚ ሌሎች የኢኮኖሚ ሴክተሮችንም ለማበረታታት አግዋ የራሱ የሆነ አስተዎፅኦ አበርክቷል" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, EYERUSALEM JIREGNA
የኢትዮጵያ ከአግዋ መታግድ ምን ጉዳት ያስከትላል?
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከኢንቨስትመንት ኮሚሽነሯ ተማጽኖ በተቃራኒ የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያን ከአግዋ አግዷል። ይህም አገሪቱን ከአግዋ የምታገኘውን ጥቅም በሙሉ እንድታጣ ያደርጋታል።
የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሯ በደብዳቤያቸው ኢትዮጵያ ከአግዋ የምትታገድ ከሆነ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያሉ ኢንቨስተሮችም ተጎጂ እንደሚሆኑ አንስተዋል።
ማሞ ምህረቱ ለብሔራዊ ቴሌቪዥን ሲናገሩ በኢትዮጵያ ያለው አስተዳደር የተሻለ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ በአግዋ ለመቆየት የሚስያችሏት መስፈርቶችን "ከመቼውም ጊዜ በላይ" ያሟላችበት ወቅት ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በስፋት እንዲገነቡና ሰፊ የሥራ እድል እንዲፈጠር ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች አግዋ አንዱ እንደሆነ ያነሱት ማሞ "የአግዋ እድል በሚቀርበት ጊዜ ይሄ ሁሉ ነገር ይቀራል ማለት አይደለም። ግን አሉታዊ ውጤት ይኖረዋል ማለት ነው። .... አግዋ ቢሄድም እንኳን እነዚህ ኢንቨስተሮች ነቅለው ይሄዳሉ ማለት አይደለም" ሲሉ ገልጸዋል።
ሆኖም የኢትዮጵያ ከአግዋ ዕድል መታገድ ዋነኛ ተጠቂ የሚያደርገው ከማንም በላይ የፋብሪካዎች ሠራተኞችን ቢሆንም ከእነሱ ጋር ተያይዘው የሚጎዱ ተጠቃሚዎች መኖራቸውን አመልክተዋል።
"በተለይ ሴት ሠራተኞች ይጎዳሉ። በተጨማሪም በኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ ሌሎች በተዘዋዋሪ መልኩ የሥራ እድል የፈጠሩ ሰዎችንም ይጎዳል" በማለት የምግብ፣ የትራንስፖርት፣ የትምህርት፣ የቤት ኪራይ እና መሰል አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ ሰዎች ተጎጂ እንደሚሆኑ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከቀናት በፊት የተነጠቀችው የአግዋ ዕድል በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሥራ ዕድል ያገኙ ዜጎች ላይ ጫና ከማሳረፍ እና የውጭ ምንዛሪ ግኝቷን ከመቀነስ ባሻገር በጦርነት፣ በኮቪድ 19 ወርርሽኝና በሌሎች ምክንያቶች ለተፈተነው ምጣኔ ሀብቷ ሌላ መስናክል መሆኑ አይቀርም።












