የአሜሪካ ከቀረጥ ነጻ ንግድ ተጠቃሚነት ዕድል የማገድ ውሳኔ ኢትዮጵያ እንዳሳዘናት አሳወቀች

ልብስ የሚሰፉ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, EYERUSALEM JIREGNA

የአሜሪካ ከቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት እድል የማገድ ውሳኔ ኢትዮጵያን "በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሳዘናት" አስታውቃለች።

" የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያን ከቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት እድል 'አጎዋ' ለማስወገድ የወሰነው ውሳኔ በከፍተኛ ውሳኔ አሳዝኖናል" በማለት የኢትዮጵያ ንግድ ሚኒስቴር በትናንትናው ዕለት አስታውቋል።

አሜሪካ ከትግራዩ ጦርነት ጋር በተያያዘ ጥሰት ተፈፅሟል በሚል አጎዋ ከተሰኘው የቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት ያገደቻት ሲሆን ከኢትዮጵያ በተጨማሪም የሰብዓዊ መብትና ዲሞክራሲ ስጋቶች ጋር በተያያዘም ማሊና ጊኒም እንዲወገዱ ተደርገዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አሜሪካ በሰብዓዊ መብቶች ያላትን ስጋት ቢረዳም ከቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት እድል የማገድ ውሳኔ ላይ አያደርስም ብሏል።

ውሳኔውንም የተሳሳተና የአሜሪካ መንግሥት ለዜጎች ደህንንት ያለውን ቁርጠኝነት ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ብሎታል።

ኢትዮጵያን ከቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት እድል፣ አግዋ ማስወጣትም ከ200 ሺህ በላይ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ቤተሰቦች ላይ ተፅእኖ እንደሚኖረው ጠቅሶ በተለይም ከግጭቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ሴቶች ላይ ጉዳቱ ይበረታል በማለትም መግለጫው አስፍሯል።

እንዲሁም በአቅርቦት ሰንሰለት ምህዳር ውስጥ የሚሳተፉትን የአንድ ሚሊዮን ነዋሪዎች ህይወት በእጅጉ እንደሚጎዳም አፅንኦት ሰጥቷል።

ኢትዮጵያውያን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና በተለይም ከአሜሪካ በአሁኑ ወቅት የሚጠብቁት ነገር አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ያለው አድሎአዊ ግምገማ እና ለተጎጂዎች በጣም አስፈላጊ የሆነውን የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት እንደሆነም ጠቅሷል።

የንፁኃን ዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል የሚደረጉ ማስፈራራቶች ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ አይሰጥም ያለው መግለጫው ከዚህ ጀርባ ያሉትም የኢትዮጵያ ጠላቶች ናቸው ብሎ እንደሚያምንም አትቷል።

በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ እለት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለአሜሪካ ኮንግረስ በጻፉት ደብዳቤ ኢትዮጵያ "በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የታወቁ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈፅማለች" ብለዋል።

የምዕራብ አፍሪካ ሃገራቱ ማሊ እና ጊኒ በቅርብ ወራት ውስጥ በተከሰቱት መፈንቅለ መንግሥት ምክንያቶች ታግደዋል ።

የኢትዮጵያ ንግድ ሚኒስቴር በበኩሉ ውሳኔው በያዝነው ዓመት ታህሳስ መጨረሻ አካባቢ ድረስ መቀልበስ አለበት በማለት ጥያቄውን አቅርቧል።

"አሜሪካ፣ ሰላም እና የህግ የበላይነትን ለማስፈንና ወደነበረበት ለመመለስ የምናደርገውን ጥረት እንድትደግፍ እንጠይቃለን። ህዝባችን ከአማፂ ኃይል ጋር በመጋፈጡ አትቅጡት" በማለት ሚኒስቴሩ አስፍሯል።

"የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሉንም የሰብዓዊ መብት ክሶች በጥብቅ ይከታተላቸዋል። ክሶቹን እየተመለከትንና ምርመራ እያደረግን ነው። ተጠያቂነትንም ለማረጋገጥ ቁርጠኞች ነን" ብሏል መግለጫው