የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል እግዱ ለተጨማሪ ሁለት ወራት ያህል መራዘሙን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Norwegian Refugee Council FACEBOOK
በኢትዮጵያ እንዳይንቀሳቀስ የታገደው የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል እግዱ ለተጨማሪ ሁለት ወራት ያህል መራዘሙን አስታወቀ።
ድርጅቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔም እንዳዘነ በድረ-ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እገዳው ለተጨማሪ ሁለት ወራት መራዘሙን ከሰሞኑ ጥቅምት 18፣ 2014 ዓ.ም ማሳወቃቸውንም የረድዔት ድርጅቱ ገልጿል።
የረድዔት ድርጅቱ እግድንም አስመልክቶ የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ጃን ኢንግላንድ በነሐሴ ወር አዲስ አበባን እንደጎበኙና ከፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ገንቢ የሚባል ውይይትም እንደነበራቸው ተገልጾ ነበር።
"የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ ውስጥ የምናደርገውን እንቅስቃሴ እግድ ለተጨማሪ ሁለት ወራት ለማራዘም ባደረገው ውሳኔ በጣም አዝነናል። በአሁኑ ወቅትም ውሳኔውን አስመልክቶ የበለጠ መረዳት እንዲኖርና ምላሽ ለመስጠት ከሚመለከታቸው ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገርን ነው" በማለት የድርጅቱ ዳይሬክተር ኒጅል ትሪክስ መናገራቸውም በመግለጫው ሰፍሯል።
ዳይሬክተሩ አክለውም ከውይይቱም ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ህዝብ ጋር ወደ ቀድሞ የትብብር ደረጃዎች በፍጥነት ለመመለስ እንደሚሰሩም አስረድተዋል።
የኖርዌይ የስደተኞች ካውንስልን ጨምሮ ሦስት የረድዔት ድርጅቶች ለሦስት ወራት የታገዱት ሐምሌ 23/2013 ዓ.ም ነበር።
የሆላንድ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን፣ የኖርዌይ የስደተኞች ካውንስልን እና አል ማክቱም ፋውንዴሽን ከተቋቋሙለት አላማ ውጪ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው እግዱ መተላለፉን የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አስታውቆ ነበር።
ኤጀንሲው "ሦስቱ ድርጅቶች ከተቋቋሙለት ዓላማ ውጪና የአገርን ጥቅም በሚጻረር መልኩ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው" እንዲታረሙ በተደጋጋሚ ውይይት ቢደረግም ሊያስተካክሉ ስላልቻሉ አጠቃላይ ምርመራ ተደርጎ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የድርጅቶቹ እንቅስቃሴ ለሦስት ወራት መታገዳቸውን በወቅቱ አስታውቋል።
መንግሥት ረድዔት ድርጅቱን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ለሚሰሩ አለም አለም አቀፍ ሰራተኞች ተገቢውን ፈቃድ ባለማግኘቱ እንደከሰሰውም የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል ባወጣው መግለጫ አትቷል።
ድርጅቱ ከአውሮፓውያኑ 2011 ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርት፣ በንፁህ ውሃ እና የንፅህና መጠበቂያ ተቋማት፣ መጠለያ፣ ምግብ እና ሕጋዊ መታወቂያ ሰጥቷል።
በአውሮፓውያኑ 2020ም በስድስት ክልሎች ማለትም በኦሮሚያ፣ በደቡብ ክልል፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ እና በሶማሌ ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ 585 ሺህ ሰዎችን ማገዙ ተነግሯል።
የረድዔት ድርጅቱ በበኩሉ በህጋዊና በጎ አላማን ባነገበ መልኩ እንደሚሰራ ጠቅሶ ምላሽ የሰጠ ሲሆን የመንግሥትንም ውሳኔ በማክበር ፕሮግራሞቹንም እንዳጠፈ አስታውቋል።.












