መንግሥት በሦስት የእርዳታ ድርጅቶች ላይ ዕገዳ የጣለበትን ምክንያት አስታወቀ

የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን እና ኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስል አርማ

የፎቶው ባለመብት, MSF/NRC

የምስሉ መግለጫ, የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን እና ኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስል አርማ

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ በአገሪቱ ይሰሩ የነበሩ ሦስት የእርዳታ ተቋማትን ያገደበትን ምክንያቶች ይፋ አደረገ።

የሆላንድ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን፣ ኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስል እና አል ማክቱም ፋውንዴሽን ለሦስት ወራት እገዳ እንደተጣለባቸው መንግሥት አስታውቋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ሦስቱ የውጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ከመንግሥት በሰጣቸው ፍቃድ በተለያዩ የሰብዓዊ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሶ፤ ኤጀንሲው በሚያደርገው ክትትል መሠረት ድርጅቶቹ ከተቋቋሙለት አላማ ውጪ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው ለሦስት ወራት ታግደዋል ብሏል።

የሆላንድ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን እና ኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስል እግዱን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እግዶች

የአስቸኳይ ጊዜ መረጃ አጣሪ ትዊተር ገጽ ላይ የወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው የሆላንድ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን "ፍቃድ ያልተሰጣቸው የሳተላይት መገናኛ መሳሪያውችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባ የድርጅቱ ሠራተኞች አፍራሽ ለሆኑ አላማ ሲጠቀሙበት እና ይዘው ሲንቀሳቀሱ በጸጥታ አካላት ቀጥጥር ስር ውለዋል" ይላል።

የሆላንድ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን እና ኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስል ሐሰተኛ መረጃዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ እና በሌሎች ዘዴዎች ሲያሰራጩ ተገኝተዋልም ተብሏል።

"ሦስቱም ድርጅቶች ስልጣን በተሰጠው አካል የሥራ ፍቃድ ያልተሰጣቸውን የውጭ አገር ዜጎች ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ከስድስት ወር በላይ ቀጥረው ሲያሰሩ ተገኝተዋል" ሲል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ከሷል።

አል ማክቱም ፋውንዴሽን ደግሞ "የትምህርት ሚንስቴር የኮቪድ-19 ፕሮቶኮልን ባለማክበር፣ የበጀት አጠቃቀም ግልጽነት የጎደለውና በትምህርት ቤቱ ስም የሚመጣን በጀት ከአላማው ውጭ እየተጠቀመ በመሆኑ እንዲሁም በሠራተኞች አስተዳደር ችግር የታየበት በመሆኑ" መታገዱን አመልክቷል።

ኤጀንሲው "ሦስቱ ድርጅቶች ከተቋቋሙለት ዓላማ ውጪና የአገርን ጥቅም በሚጻረር መልኩ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው" እንዲታረሙ በተደጋጋሚ ውይይት ቢደረግም ሊያስተካክሉ ስላልቻሉ አጠቃላይ ምርመራ ተደርጎ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የድርጅቶቹ እንቅስቃሴ ለሦስት ወራት መታገዱን ገልጿል።

ድርጅቶቹ ምን አሉ

ኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስል ከሐምሌ 23/2013 ዓ.ም ጀምሮ መንግሥት እንቅስቃሴውን እንደተገደበው አረጋግጧል።

የድርጅቱ የቀጠናው ሚዲያ እና ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ጄረሚ ቴይለር መንግሥት በአስቸኳይ ተግባራዊ የሚሆን እግድ መጣሉን እና በጉዳዩ ላይ ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ከሐምሰሌ 23 ጀምሮ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስል ሁሉንም እንቅስቃሴዎችን ማገዳቸውን አረጋግጣለሁ። ትዕዛዙን እክብረን በመላው አገሪቱ የሚገኙ እንቅስቃሴዎቻችንን ገተናል። በጉዳዩ ላይ ከባለሥልጣናት ጋር እየተነጋገርን ነው" ብለዋል ጄረሚ ቴይለር ለቢቢሲ።

በድርጅቱ የአጋርነት እና የፖሊሲ ዳይሬክተር የሆኑት ኦሌ ሶልቫንግ በበኩላቸው ድርጅቱ ከአውሮፓውያኑ 2011 ጀምሮ ከሁሉም የኢትዮጵያ የመንግሥት ቅርንጫፎች ጋር በአክብሮትና ትብብር በተሞላበት መንፈስ ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

አስፈላጊ የሆነውን የሰብዓዊ ስራዎችን ለመቀጠል ይቻል ዘንድ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ባለስልጣናትም ጋር ስለተፈጠረው ነገርና ያሏቸውንም ጥያቄዎች በተመለከተም እየተነጋገሩ መሆኑን ገልፀዋል።

ድርጅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርት ፣ ንፁህ ውሃ እና የንፅህና መጠበቂያ ተቋማት ፣ መጠለያ ፣ ምግብ እና ህጋዊ መታወቂያ ሰጥቷል።

በአውሮፓውያኑ 2020 ም በስድስት ክልሎች ማለትም በኦሮሚያ ፣ በደቡብ ክልል ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣ በጋምቤላ እና ሶማሌ ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ 585 ሺህ ሰዎችን አግዟል።

"የኢትዮጵያ መንግሥትና ኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስል ዕርዳታ በመርህ እና በተቀላጠፈ መልኩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲደርስ የሚል ተመሳሳይ መርህ አላቸው። በተቻለ ፍጥነት ሥራችንን እንደምንቀጥል ተስፋችን ከፍ ያለ ነው" በማለት አሌ ሶልቫንግ ተናግረዋል።

የሆላንድ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በተመሳሳይ ከሐምሌ 21/2013 ጀምሮ እንቅስቃሴያቸው መገደቡን የሚያትት ደብዳቤ ከኢትዮጵያ መንግሥት እንደደረሰው አስታውቋል።

ኤምኤስኤፍ ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ "እግዱ የተጣለበትን ምክንያት ዝርዝር ለመረዳት ከባለሥልጣናት ማብራሪያ ለመጠየቅ በሂደት ላይ ነን" ብሏል።

በእነዚህ ክልሎች ውስጥ የጤና እንክብካቤ ተደራሽነት ቀድሞውኑ የተገደበ ነው እናም የበለጠ እንዲህ በአገልግሎቶች ላይ ያለ እገዳ የሚያሳድረው ተፅእኖ የከፋ ነው ብሏል።

በድርጅቱ መታገድ ምክንያት በሚረዳቸው የኢትዮጵያ ዜጎችና ስደተኞች ላይ አስከፊ መዘዞችን እንደሚያስከትል አሳስቧል።

ኤምኤስኤፍ በአሁኑ ወቅት ተግዳሮቶች ቢኖሩም ነፃ እና ጥራት ያለው የጤና እንክብካቤ እንደሚሰጥ አስታውሶ አስፈላጊ የሆነ የሰብዓዊ ዕርዳታ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆናቸውንም በመግለጫው አስረድቷል

በአውሮፓውያኑ 2020 ብቻ ኤምኤስኤፍ 220 ሺህ ተመላላሽ ታካሚዎችን፣ 16,000 ሰዎችን የወባ ህክምና፣ 3 ሺህ 300 ሰዎችን ልዩ እንክብካቤና ለ3 ሺህ800 ሰዎች የአእምሮ ጤና ምክር እንዲሁም 2 ሺህ 700 ሕፃናትን በማዋለድ መርዳታቸውንም መግለጫው ጠቁሟል።

"የሕክምና እና የሰብአዊ ዕርዳታ ፈላጊ ሰዎች አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያገኙ ከዚህ እገዳ ጋር የተያያዙ ማናቸውንም ስጋቶች ለመፍታት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መወያየታችንን እንቀጥላለን" ብሏል በመግለጫው

አል ማክቱም የተባለው ድርጅት ስለተጣለበት ዕገዳ እስካሁን ያለው ነገር የለም።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም አንዳንድ እርዳታ ድርጅቶች ለህወሓት አማጺያን የልተፈቀዱ ድጋፎችን ለማድረግ ስለመሞከራቸው ማስረጃ አለ በማለት ስማቸው ያልተገለጹ ድርጅቶችን ሲወቅሱ ነበር።

በተያያዘ ዜና ትናንት አዲሱ የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች ለትግራይ ተዋጊዎች ያደላሉ እንዲሁም ያስታጥቃሉ ማለታቸውን "አደገኛ" ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ኃላፊው ማክሰኞ ዕለት እንደተናገሩት የእርዳታ ድርጅቶች ላይ የተቃጣው "መሠረተ ቢስ ወቀሳ" ሊቆም ይገባል ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

"ማስረጃ ካለ በማስረጃ ሊደገፉ ይገባል፤ እውነት ለመናገር ግን ይህ አካሄድ አደገኛ ነው" ብለዋል በቅርቡ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ያጠናቀቁት አዲሱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ኃላፊ።