የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ መንግሥት የእርዳታ ድርጅቶችን ሊወቅስ አይገባም አለ

የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ

የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች ለትግራይ ተዋጊዎች ያደላሉ እንዲሁም ያስታጥቃሉ ማለታቸው "አደገኛ" ነው አሉ።

ኃላፊው ማክሰኞ ዕለት የእርዳታ ድርጅቶች ላይ የተቃጣው "መሠረተ ቢስ ወቀሳ" ሊቆም ይገባል ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

"ማስረጃ ካለ በማስረጃ ሊደገፉ ይገባል፤ እውነት ለመናገር ግን ይህ አካሄድ አደገኛ ነው" ብለዋል ኃላፊው።

በምዕራብ ደቡብ በኩል ወደ አጎራባቾቹ የአማራና አፋር ክልሎች እየገፉ ያሉት የህወሓት አማጺያን ወደ 200 ሺህ ሰዎችን አፈናቅለዋል ብለዋል ኃላፊው።

54 ሺህ ሰው የተፈናቀለው በአፋር ክልል መሆኑንም ተናግረዋል።

ከስምንት ወራት በፊት በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት እስካሁን ማብቂያ አላገኘም።

የአማራ ክልል ቃል አቀባይ ግዛቸው ሙሉነህ በአማራ ክልል ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አረጋግጠዋል።

የአፋር ክልል ቃል አቀባይ አሕመድ ኮሎይታ እና የፌዴራሉ መንግሥት በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው ምላሽ አልሰጡም።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ የህወሓት አማጺያን ከአማራና ከአፋር ክልሎች እንዲወጡ ጠይቀዋል።

አክለውም የአማራና የኤርትራ ኃይሎች ከምዕራባዊ ትግራይ እንዲወጡና የሰብዓዊ እርዳታ ያለ ምንም አክል እንዲጓዝ ጠይቀዋል።

በተያያዘ ዜና ድንበር አልባው የዶክተሮች ቡድን የደች ቅርንጫፍ የሆነው የእርዳታ ድርጅት የሥራ ፈቃዱን እንደተነጠቀ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ማክሰኞ ምሽት ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት ድርጅቱ መንቀሳቀስ እንደማይችል የሚያትት ደብዳቤ እንደፃፈላቸው ድርጅቱ ተናግሯል።

"የታገድንበትን ምክንያት ለማወቅ እና የተጣራ መረጃ ለማግኘት ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ምላሽ እየጠየቅን ነው" ብሏል የድንበር የለሽ የዶክተሮች ቡድን [ኤምኤስኤፍ] ባወጣው መግለጫ።

ኖርዌጂያን ሬፊውጂ ካውንስል የተሰኘው እርዳታ ሰጪም ተመሳሳይ ትዕዛዝ እንደተሰጠው ነገር ግን "ከባለሥጣናት ጋር ውይይት እያደረገ" እንደሆነ ይፋ አድርጓል።

የተባበሩት መንግሥታት ትግራይ ውስጥ 400 ሺህ ያክል ሰዎች የረሃብ አደጋ እንደተጋረጠባቸው እንዲሁም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የክልሉ ነዋሪዎች እርዳታ እንደሚያሻቸው ይናገራል።

ቃል አቀባዩ "ቢያንስ 100 እርዳታ የጫኑ መኪናዎች በየቀኑ ወደ ትግራይ ክልል መጓዝ አለባቸው" ሲሉ አዲስ አበባ ለሚገኙ ጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ኃላፊው አክለው በቅርቡ 122 መኪናዎች ወደ ትግራይ ክልል አቅንተዋል ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት ወኪል የሆነው ዩኒሴፍ ባለፈው ሳምንት ትግራይ ውስጥ ከ100 ሺህ በላይ ሕፃናት ለሞት የሚያጋልጥ የምግብ እጥረት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አስጠንቅቆ ነበር።