ቶኪዮ ኦሎምፒክ 2020፡ ለተሰንበት ከሲፈን፤ ስለ ሁለቱ ስመ ጥር አትሌቶች ሊታወቁ የሚገቡ ነጥቦች

የፎቶው ባለመብት, Michael Steele/Getty Images
በሁለት ቀን ልዩነት የ10ሺህ ሜትር ክብረ ወሰንን ማሻሻል የቻሉት አትሌት ለተሰንበት ግደይ እና ሲፈን ሐሰን በትልቁ የአትሌቲክስ መድረክ ላይ በ10ሺህ ሜትር ተፋጠዋል።
እነዚህ አትሌቶች በትልቅ የአትሌቲክስ መድረክ ላይ ሲገናኙ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
በሪዮ ኦሎምፒክ የ10ሺህ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰንን በማሻሻል ወርቅ የወሰደችው አልማዝ አያና እና የወቅቱ ተፎካካሪዋ ቪቪያን ቼሪዩት በቶኪዮ ኦለምፒክ ተሳታፊ ባለመሆናቸው የፊታችን ቅዳሜ በሚደረገው የ10ሺህ ሜትር ፍጻሜ የወርቅ ሜዳሊያ ከሲፈን ወይም ከለተሰንበት እንደማያልፍ ይጠበቃል።
በዚህ ውድድር ሌሎች ተጠባቂ ከሆኑት ተወዳዳሪዎች መካከል ኢትዮጵያውያኖቹ ጽጌ ገ/ሰላማ እና ጸሃይ ገመቹ እንዲሁም በርቀቱ ብዙ ልምድ ያላት ኬንያዊቷ ሄለን ኦቢሪ ተጠቃሽ ናቸው።
እአአ 2019 ላይ በኳታር ዶሃ በተዘጋጀው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተገናኝተው ሲፈን ወርቁን ስትወስድ ለተሰንበት በሁለተኛነት አጠናቃለች።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በሚሳተፍባቸው ርቀቶች በትውልድ ኢትዮጵያዊ እና የኔዘርላንድስ ዜጋ የሆነችው ሲፈን ዋነኛ ተፎካካሪ መሆኗን ገልጿል። ሲፈን በ1500 ሜትር፣ በ5ሺህ ሜትር እና በ10ሺህ ሜትር ወርቅ ለማምጣት ቆርጣ ተነስታለች።
በ5ሺህ ሜትር እቅዷን ያሳካች ሲሆን በ1500 ሜትርም ማጣሪያውን አልፋለች። ብዙ ልምድ ያካበተችው የ28 ዓመቷ ሲፈን በቶኪዮ ኦሊምፒክ ታሪክ ለመስራት ወጥናለች።
በሌላ በኩል ገና የ23 ዓመት ወጣት የሆነችው ለተሰንበት ግደይ በኦሊምፒክ መድረክ ስትወዳደር ይህ የመጀመሪያዋ ይሁን እንጂ የምትገኝበትን ወቅታዊ አቋም ከግምት በማስገባት የ10ሺህ ሜትር ድሉን ለለተሰንበት የሚሰጡ በርካቶች ናቸው።
እአአ 1992 በባርሴሎና ኦሊምፒክ የየዛኔዋ የ23 ዓመት ወጣት፣ አትሌት ደራርቱ ቱሉ በ10ሺህ ሜትር ለአገሯ ወርቅ አስገኝታ ነበር። ከስምንት ዓመታት በኋላም በሲድኒ ኦሊምፒክ በተመሳሳይ ርቀት ወርቅ አምጥታለች።
በዘንድሮ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ለተሰንበት ኖሯት ሲፈን የማይኖራት ብቸኛው ነገር የደራርቱ ቱሉ ድጋፍ ነው።
"ሁለቱም ልጆች የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው። እንደ ዜጋችን ለተሰንበትን እንጠብቃለን። የምንደግፈውም ለተሰንበትን ነው። ይሁን እንጂ ሲፈንም የኛው ልጅ ነች። የምንኮራባት እና የምንወዳት ልጅ" ትላለች አትሌት ደራርቱ ቱሉ።
ደራርቱ ቱሉ ከለተሰንበት ጋር ልምምድ ስታደርግ እና ስታበረታታት ታይታለች።
ለተሰንበት እና ሲፈን
ለተሰንበት ተማሪ ሳለች በስፖርት ክፍለ ጊዜ 'አልሮጥም' በማለቷ 'ወላጅ አምጪ' ተብላ ነበር። ዛሬ ላይ ግን ለተሰንበት በሩጫው ሌላ ዓለም ውስጥ ነው ያለችው። የወቅቱ የ10ሺህ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን በእጇ ይገኛል።
ሲፈን ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄዳው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን በ1500 ሜትር እና በ10ሺህ ሜትር ሁለት ወርቅ በመውሰድ ታሪክ ሰርታለች።
ለኔዘርላንድ የምትሮጠው ሲፈን በኦሊምፒክ ስትሳተፍ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም። በሪዮ ኦሎምፒክ 800 ሜትር 5ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
የፊታችን ቅዳሜ ለተሰንበት በርቀቱ የኢትዮጵያን የበላይነት ለማረጋገጥ፤ ሲፈን ደግሞ በአንድ የኦሊምፒክ መድረክ ሦስት ወርቅ የማግኘት ሕልሟን ለማሳካት ይሮጣሉ።
ሲፈን ለለተሰንበት ስጋት ትሆን?
"አዎ ያሳስበናል፤ ለምን? በዓለም ቁጥር አንድ የምትባለ አትሌት ቀርቶ ሌላም አትሌት መናቅ የለበትም። ስለዚህ ጥንቃቄ ይፈልጋል። በቂ የሆነ ወድድር አድርጋለች [ለተሰንበት]። ጤንነቷ ጥሩ ነው። የአእምሮ ዝግጅቷም ጥሩ ነው። አስቀድመን በደንብ አዘጋጅተናታል" በማለት ደራርቱ ትናገራለች።
ለስደሰተኛ ጊዜ በኦሊምፒክ የሚሳተፉት እና ለተሰንበትን በዋነኛነት የሚያሰለጥኑት አሰልጣኝ ኮማንደር ሁሴን ሸቦ፣ በለተሰንበት አሁናዊ አቋም ጥርጥር ባይገባቸውም ሲፈን ጠንካራ ተፎካካሪያቸው እንደምትሆን ያምናሉ።

የፎቶው ባለመብት, EFA
ሲፈንን ለማሸነፍ የተቀመጠው ስልት
ኮማንደር ሁሴን አትሌት ሲፈን ለኢትዮጵያ አትሌቶች ስጋት ልትሆን የምትችልባቸውን ምክንያቶች እንዲህ ያስረዳሉ።
"በ5ሺህ እና በ10ሺህ ርቀቶች አሁን ባላት ልምድ እና ችሎታ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደምትሆን ምንም ጥርጥር የለውም"።
ሌላኛው ደግሞ ሲፈን በመጨረሻ ዙር ላይ ፍጥነት እንዳላት አሰልጣኙ ይናገራሉ። "ሲፈን በውድድር መጨረሻ ላይ ከለተሰንበት የበለጠ ፍጥነት አላት" በማለት ያስረዳሉ።
ለዚህም የአትሌቲክስ ቡድን ሲፈንን ለማሸነፍ መላ መዘየዱን አሰልጣኙ ይናገራሉ።
"እንደ ታክቲክ ለተሰንበት ማድረግ ያለባት እሷን [ሲፈንን] ከእራሷ ሳታርቅ ዙሩን አክርራ ሄዳ፣ አንድ ሁለት ዙር እስኪቀር ድረስ አኩል ከሮጡ ልትፈተን [ሲፈን] ትችላለች"
ሲፈን በዚህ ኦሊምፒክ በሦስት ውድድሮች ነው የምትካፈለው። የመጨረሻው ደግሞ የ10ሺህ ሜትር ውድድር ነው። በዚህ ውድድር ተሳታፊ በምትሆን ጊዜም ድካም ሊጫናት ይችላል።
"ይህ የሚሳካ ከሆነ አስደናቂ ነገር ነው [ሲፈን በሦስት ውድድር ወርቅ የማግኘት እቅድ]። ሁለት ውድድር አጠናቅቃ ሦስተኛው ላይ 10ሺህ ሜትር መሮጥ ይቅርና በዛ ሙቀት ቦታ፣ ሁለት ውድድር ማድረግ በራሱ በጣም ከባድ ነው። ሦስተኛው ውድድር ላይ በጣም ይከብዳታል የሚል ጥርጣሬ አለኝ" በማለት ኮማንደር ሁሴን ይናገራሉ።
በቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚካሄድባት ጃፓን በአሁኑ ወቅት ያለው ሙቀት ከፍተኛ በመሆኑ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ሞቃታማ ወደሆኑ እንደ መተሃራ እና አዋሽ ከተሞች ልምምድ ሲያደርግ መቆየቱን ደራርቱ ቱሉ ለቢቢሲ ተናገራ ነበር።



















