ቶኪዮ ኦሊምፒክ 2020፡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚጠበቁባቸው ውድድሮች የትኞቹ ናቸው? መቼስ ይካሄዳሉ?

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Athletics Federation
ባለፈው ሳምንት አርብ የተጀመረው የቶኪዮ ኦሊምፒክ በድምቀት መካሄዱን ቀጥሏል።
በቶኪዮ ኦሊምፒክ 33 አይነት ስፖርታዊ ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን ኢትዮጵያም በአራት አይነት የስፖርት አይነቶች ማለትም በአትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ውሃ ዋናና በቴኳንዶ ትሳተፋለች።
በጉጉት በሚጠበቀው የአትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ ለተሰንበት ጊደይ፤ ሹራ ቂጣታ፤ ሰለሞን ባረጋ እና ዮሚፍ ቀጀልቻ በሚወዳደሩባቸው ርቀቶች ሜዳሊያ ያስገኛሉ ተበሎ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል።
ለመሆኑ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚጠበቁባቸው ውድድሮች የትኞቹ ናቸው? መቼስ ነው የሚካሄዱት?
የወንዶች 3ሺህ ሜትር መሰናክል ማጣሪያ
ነገ አርብ ሐምሌ 23 የወንዶች 3ሺህ ሜትር መሰናክል የማጣሪያ ውድድር ይካሄዳል።
በዚህ ውድድር ሦስት ኢትዮጵያውን አትሌቶች ይሰለፋሉ። ተወዳዳሪዎቹ አትሌቶችም ታደሰ ታከለ፣ አብረሃም ስሜ እና ኃ/ማርያም አማረ ናቸው።
የማጣሪያ ውድድሩ በሦስት ቡድን ተከፍሎ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ሌሊት 9፡30 እስከ 4፡05 ድረስ ይካሄዳል።
የሴቶች 800 ሜትር ማጣሪያ
በተመሳሳይ የሴቶች 800 ሜትር ማጣሪያ በስድስት ቡድን ተከፍሎ አርብ ከ10፡25 እስከ ንጋት 11፡05 ድረስ ይካሄዳል።
ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩት አትሌቶች ሀብታም አለሙ፣ ወርቅነሽ መሰለ እና ነጻነት ደስታ ናቸው።
የሴቶች 5ሺህ ሜትር ማጣሪያ
በዚሁ ቀን ሌላኛው የሴቶች 5ሺህ ሜትር ማጣሪያ ውድድር በሁለት ቡድን ተከፍሎ ይካሄዳል።
የመጀመሪያው ቡድን የማጣሪያ ውድድሩን ቀን 7 ሰዓት የሚጀምር ሲሆን ሁለተኛው ማጠሪያ ደግሞ 7፡26 ደቂቃ ሲል ይጀምራል።
በ5ሺህ ውድድር ላይ ሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን እነሱም ጉዳፍ ጸጋይ፣ እጅጋየሁ ታዬ እና ሰምበሬ ተፈሪ ናቸው።
ጉዳፍ ፀጋይ በዚህ ዓመት የካቲት ወር ላይ በፈረንሳይ በተካሄደ የ1ሺህ 500 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ክብረ ወሰን ማሻሻል ችላለች።
በዚህ ምድብ ኬንያውያኑ ሄለን ኦቢሪ እና አግነስ ቲሮፕ እንዲሁም ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሲፋን ሐሰን ቀንደኛ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
የወንዶች 10ሺህ ሜትር የፍጻሜ ውድድር
ነገ ከሚካሄዱት ውድድሮች እጅግ በጉጉት ከሚጠበቁት አንዱ የወንዶች 10ሺህ ሜትር የፍጻሜ ውድድር ነው።
ኢትዮጵያ በዚህ መስክ በሰለሞን ባረጋ፣ በዮሚፍ ቀጄልቻ እና በበሪሁ አረጋዊ የምትወከል ሲሆን ውድድሩም ከቀኑ 8፡30 ላይ እንደሚካሄድ የቶኪዮ ኦሊምፒክ መርሃ ግብር ላይ ተመልክቷል።
ሰለሞን ባረጋ ከሁለት ዓመት በፊት በዶሃ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በወንዶች የ5ሺህ ሜትር ውድድር የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።
ዮሚፍ ቀጄልቻ ደግሞ በተመሳሳይ የውድድር መድረክ በ10 ሺህ ሜትር ውድድር የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።
ሰለሞን እና ዮሚፍ በኦሊምፒክ መድረክ ሲሳተፉ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።
ሌላኛው አትሌት በሪሁ አረጋዊ በኔዘርላንድስ ሄንግሎ በተካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ማጣሪያ ላይ ሦስተኛ ሆኖ መጨረስ ችሏል።
የወንዶች የ800 ሜትር ማጣሪያ
ቅዳሜ ሌሊት ከ9፡50 እስከ 10፡30 ድረስ በስድስት ቡድኖች ተከፍሎ የወንዶች የ800 ሜትር ማጣሪያ ይካሄዳል።
በዚህ ውድድር ላይ ብቸኛው አትሌት መለሰ ንብረት ኢትዮጵያን ወክሎ ይወዳደራል።
የሴቶች 800 ሜትር የግማሽ ፍጻሜ
በተመሳሳይ የፊታችን ቅዳሜ የሴቶች 800 ሜትር የግማሽ ፍጻሜ ማጣሪያ ውድድር በሦስት ቡድኖች ተከፋፍሎ ይካሄዳል።
የመጀመሪያውን ማጣሪያ ማለፍ የሚችሉ ከሆነ አትሌት ሀብታም አለሙ፣ ወርቅነሽ መሰለ እና ነጻነት ደስታ የግማሽ ፍጻሜ ውድድሩ ተሳታፊ የሆናሉ።

የሴቶች 3ሺህ ሜትር መሰናክል ማጣሪያ
እሁድ ለሰኞ አጥቢያ የሴቶች 3ሺህ ሜትር መሰናክል ማጣሪያ ሌሊት 3፡40 እስከ 10፡10 ድረስ በሦስት ቡድን ተከፍሎ ውድድሩ ይከናወናል።
በዚህ ማጣሪያ ኢትዮጵያም በመቅደስ አበበ፣ በሎሚ ሙለታ እና በዘርፌ ወንድማገኝ ትወከላለች።
የወንዶች 800 ሜትር ግማሽ ፍጻሜ
አትሌት መለሰ ንብረት የመጀመሪያውን የ800 ሜትር ማጣሪያ የሚያልፍ ከሆነ በዚሁ ቀን የግማሽ ፍጻሜ ውድድር ያደርጋል።
የ1500 ሜትር የሴቶች ማጣሪያ
የፊታችን ሰኞ ሐምሌ 26 ደግሞ የ1500 ሜትር የሴቶች ማጣሪያ ይደረጋል። በዚህም ኢትዮጵያውያኑ ፍሬወይኒ ኃይሉ፣ ድርቤ ወልተጂ እና ለምለም ኃይሉ ይወዳደራሉ።
ይህ የማጣሪያ ውድድር ሰኞ ለማክሰኞ አጥቢያ ለሊት 9፡35-10፡00 ድረስ ይካሄዳል።
የወንዶች 3ሺህ ሜትር መሰናክል የፍጻሜ
ታደሰ ታከለ፣ አብራሀም ስሜ እና ኃ/ማርያም አማረ የ3ሺህ ማጣሪያን የሚያልፉ ከሆነ የፊታችን ሰኞ ከቀኑ 9፡15 ላይ ለፍጻሜ ይወዳደራሉ።
የሴቶች 5ሺህ ሜትር ፍጻሜ
በጉጉት በሚጠበቀውና ሰኞ ቀን 9፡40 ሲል በሚደረገው የ5ሺህ ሜትር የፍጻሜ ውድድር ላይ ኢትዮጵያውያኑ ጉዳፍ ጸጋይ፣ እጅጋየሁ ታዬ እና ሰምበሬ ተፈሪ ማጣሪያውን ካለፉ ተጠባቂ አትሌቶች ይሆናሉ።
ኬንያውያኑ ሄለን ኦቢሪ እና አግነስ ቲሮፕ እንዲሁም ሲፋን ሐሰን ሌሎች ተጠባቂ አትሌቶች ናቸው።
የወንዶች 1500 ሜትር ማጣሪያ
የፊታችን ማክሰኞ የወንዶች 1500 ሜትር ማጣሪያ የሚደረግ ሲሆን ታደሰ ለሚ፣ ሳሙኤል አባተ እና ሳሙኤል ተፈራ አገራቸውን ወክለው የሚወዳደሩ አትሌቶች ናቸው።
ይህ ውድድር ማክሰኞ ለዕረቡ አጥቢያ ከለሊቱ 9 ሰዓት እስከ 9፡30 ድረስ በሦስት ቡድኖች ተከፋፍሎ የሚደረግ ይሆናል።
የወንዶች 5 ሺህ ሜትር ማጣሪያ
በተመሳሳይ የወንዶች 5 ሺህ ሜትር ማጣሪያ በተመሳሳይ ቀን ይካሄዳል። በማጣሪያውም ጌትነት ዋለ፣ ንብረት መላክ እና ሚልኬሳ መንገሻ የሚሳተፉ ይሆናል። በሁለት ቡድን ተከፍሎ የሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር ከቀኑ 7 ሰዓት እና 7፡20 ላይ ይካሄዳል።
የወንዶች 800 ሜትር ፍጻሜ
የወንዶች 800 ሜትር ፍጻሜም የሚካሄደው ማክሰኞ ዕለት ይሆናል።
አትሌት መለሰ ንብረት የመጀመሪያውን ዙር ማጣሪያ እና ግማሽ ፍጻሜን የሚያልፍ ከሆነ የፊታችን ማክሰኞ የ800 ሜትር ፍጻሜ ተወዳዳሪ ይሆናል።
የሴቶች 1500 ሜትር ግማሽ ፍጻሜ
የሴቶች 1500 ሜትር ግማሽ የፍጻሜ ውድድር ረቡዕ ዕለት የሚካሄደው ይሆናል።
ፍሬወይኒ ኃይሉ፣ ድርቤ ወልተጂ እና ለምለም ኃይሉ በዚህ ርቀት አገራቸውን ወክለው የሚወዳደሩ አትሌቶች ናቸው።
የሴቶች 3 ሺ ሜትር መሰናክል ፍጻሜ
አትሌት መቅደስ አበበ፣ ሎሚ ሙለታ እና ዘርፌ ወንድማገኝ ማጣሪያውን የሚያልፉ ከሆነ የ3ሺህ ሜትር መሰናክል ፍጻሜ ተወዳዳሪ መሆን ይችላሉ።
ውድድሩ ከቀኑ 8 ሰዓት ሲል ይጀምራል።
የወንዶች የ5ሺህ ሜትር ፍጻሜ
አርብ ዕለት በጉጉት የሚጠበቀው የወንዶች የ5ሺህ ሜትር ፍጻሜ ውድድር ቀን 9 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።
አትሌት ጌትነት ዋለ፣ ንብረት መላክ እና ሚልኬሳ መንገሻ ማጣሪያውን አልፈው በ5ሺህ ሜትር የወንዶች ፍጻሜ ውድድር ላይ እንደሚኖሩ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎባቸዋል።
የሴቶች ማራቶን
ቅዳሜ ጠዋት 1 ሰዓት ላይ የሴቶች ማራቶን ይካሄዳል። ኢትዮጵያውያኑ ትዕግስት ግርማ፣ ብርሀኔ ዲባባ እና ሮዛ ደረጄ ደግሞ ለአገራቸው ሜዳሊያ ለማስገኘት የሚፋለሙት አትሌቶች ናቸው።
የሴቶች 10 ሺህ ሜትር ፍጻሜ
ቅዳሜ ከቀኑ 7፡45 ላይ የሴቶች 10ሺህ ሜትር የፍጻሜ ውድድር ይካሄዳል። በመድረኩም ኢትዮጵያ በአትሌት ለተሰንበት ጊደይ፣ ጽጌ ገ/ሰላማ እና ፀሐይ ገመቹ ትወከላለች።
የ23 ዓመቷ ወጣት አትሌት ለተሰንበት ጊደይ የ5 ሺህ ሜትር የሴቶች ክብረ ወሰን ባለቤት ስትሆን በቅርቡም የ10 ሺህ ሜትር ክብረ ወሰንን አሻሽላለች።
በዚህ ውድድር የለተሰንበት ግደይ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሲፋን ሐሰን ፉክክር በበርካቶች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ነው።
የወንዶች ማራቶን
በቀጣዩ ቀን እሁድ ነሐሴ 01/2013 ዓ.ም ደግሞ የወንዶች ማራቶን ይካሄዳል። በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሏት አትሌቶች ሹራ ቂጣታ፣ ሌሊሳ ዴሲሳ እና ሲሳይ ለማ ናቸው።
አትሌት ሹራ ቂጣታ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው በኦሊምፒክ የሚወዳደረው። አትሌት ሹራ "በዚህ ውድድር ለአገርም ለግልም ወርቅ ማምጣት አለብን በሚል ነው እየተዘጋጀን ያለነው" ብሎ ነበር ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ።
ከአንድ ዓመት በፊት በለንደን ማራቶን የኬንያውን ኢሉድ ኪፕቾጌን ያሸነፈው ሹራ፤ በቶኪዮ ኦሊምፒክም የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት ከኪፕቾጌ ጋር ይወዳደራል።
ሌላኛው ኢትዮጵያዊው የማራቶን ሯጭ ሌሊሳ ዴሲሳ ከሁለት ዓመት በፊት በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በወንዶች ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፉ ይታወሳል።














