ሲፈን ሐሰን፡ ''ለኢትዮጵያ የመሮጥ ፍላጎት ኖሮኝ አያውቅም''

የፎቶው ባለመብት, Michael Steele
"የምፈራው አትሌት የለም። ማሸነፍ እንጂ ለቅጽበትም ቢሆን መሸነፍን አላስብም" ትላለች የ26 ዓመት ወጣት የዓለም ሻምፒዮኗ አትሌት ሲፈን ሐሰን።
"ለኢትዮጵያ እንድሮጥ የጠየቁኝ ሰዎች አሉ። እኔ ግን ለኢትዮጵያ የመሮጥ ፍላጎት ኖሮኝ አያውቅም። ኦሮሚያ ነጻ ካልወጣች በቀር" በማለት አትሌት ሲፈን ሃሰን ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ተናግራለች።
ለኔዘርላንድስ የምትሮጠው ሲፈን በአሁኑ ወቅት በዓለም አትሌቲክስ የሴቶች አጠቃላይ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በቅርቡ በኳታር ዶሃ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ10 ሺህ፣ በ1 ሺህ እና 5 መቶ ሜትር ውድድሮች የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት መሆኗ ይታወሳል። ከዚህ በተጨማሪም እየተጠናቀቀ ባለው የፈረንጆቹ ዓመት በሦስት የተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በበላይነት አጠናቃለች።
በአዳማ ከተማ የተወለደችው ሲፈን፤ ገና የ15 ዓመት ወጣት ሳለች በስደት ከሃገር እንደወጣች እና በለጋ ዕድሜዋ ብዙ ውጣ ውረዶችን ለማለፍ መገደዷን ትናገራለች።
ወደ ትምህርት ቤት በሩጫ ትሄድ እንደነበረ እና ለአትሌቲክስ ስፖርት ፍቅር ያደረባት ገና ታዳጊ ሳለች እንደሆነ ታስረዳለች። ወደ ኔዘርላንድስ ካቀናች በኋላ አትሌቲክሱን አጠናክራ እንደያዘችም ትናገራለች።
እዚያም የአዲሱ አገር የኑሮ ዘይቤ እና የአየር ሁኔታ ለአንድ ዓመት ፈተና ሆኖባት እንደቆየ ሲፈን ታስረዳለች። ሆኖም ብዙም ሳትቆይ በአትሌቲክሱ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደጀመረች ታስታውሳለች።
ሲፈን አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ 'የእኔ ጀግና ነው' ትላለች። ለዚህም ምክንያቷ በሪዮ ኦሊምፒክ የማራቶችን ውድድር ሁለተኛ ሆኖ ሊያጠናቅቅ ሲል ያሳየው ምልክት በውስጧ ልዩ ስሜት ፈጥሮባታል።
"ፈይሳ ለኦሮሞ ህዝብ ብዙ ነገር አድርጓል። ያን ምልክት ካሳየ በኋላ ብዙ ሰዎች ወደ እኔ እየመጡ 'እጅን ማጣመር ምን ማለት ነው?' እያሉ ይጠይቁኝ ነበር። ትርጉሙን ስነግራቸው ብዙዎች በጣም አድንቀውታል።"
በአንድ ወቅት ነርስ ለመሆን ትምህርት ቤት ገብታ የነበረችው ሲፈን፤ ለሁለት ዓመታት ያህል ትምህርቷን ከተከታተለች በኋላ አቋርጣ ሙሉ ትኩረቷን ለአትሌቲክሱ ማድረጓን ታስረዳለች።
በዶሃው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የ1ሺህ 5መቶ ሜትር የወርቅ ባለቤት ከመሆኗም በላይ ኢትዮጵያዊያን የሚታወቁበትን የ10 ሺህ ሜትር ውድድር አሸንፋ የወርቅ ባለቤት መሆኗ ልዩ ስሜት እንደፈጠረባት ትናገራለች።

"የቤት ውስጥ ረዥም ርቀት ውድድር አልወድም፤ አሰልቺ ይመስለኛል። እንደውም አልወዳደርም ብዬ ትቼው ነበር። አሰልጣኜ ነው ካልተወዳደርሽ ያለኝ። እኔም የ1ሺህ 5መቶ ሜትር ሩጫዬ ደካማ ስለነበር 'እራሴን መቅጣት አለብኝ' ብዬ ነው ወደ ትራኩ የገባሁት። ከዚያም ወርቅ አገኘው። በጣም ተደስቼበታለሁ" ትላለች ሲፈን።
ሲፈን ለኢትዮጵያ እንድትሮጥ እንደተጠየቀች ትናገራለች። "ለኢትዮጵያ እንድሮጥ የጠየቁኝ ሰዎች አሉ። እኔ ግን ለኢትዮጵያ የመሮጥ ፍላጎት ኖሮኝ አያውቅም። ኦሮሚያ ነጻ ካልወጣች በስተቀር" የሚል አቋም አላት።
"ኢትዮጵያ ብዙ ልጆች አሏት። ለእነርሱ ድጋፍ ቢደረግ እና ቢሰራባቸው ኖሮ እኔም ለኢትዮጵያ የመሮጥ ፍላጎት ይኖረኝ ነበር። ግን ባሉት ላይም አልተሰራም። ለምሳሌ ዮሚፍ ቀጄልቻ ጋር አብረን ልምምድ እናደርጋለን። ዮሚፍ ብዙ ችግሮችን ነው እያለፈ ያለው። ስለዚህ ለኢትዮጵያ ለመሮጥ ፍላጎቱ የለኝም። እንዲያውም እንኳን ወጣሁ እላለሁ።"
በተለያዩ ርቀቶች እየተወዳደረች አመርቂ ውጤት የምታስመዘግበው ሲፈን ለዚህ ምሥጢሩ ጠንክሮ ልምምዶችን ማድረግ እና ትዕግስተኛ መሆን ነው ትላለች።"አሸነፍኩም አላሸነፍኩም የውድድሩን ቪዲዮ ቁጭ ብዬ እመለከታለሁ። ትኩረቴን እና ሙሉ ጊዜዬን ለአትሌቲክሱ ነው የምሰጠው" ትላለች።
በኔዘርላንድም አመርቂ ውጤት ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ሲፈን ትናገራለች።
"ከፌዴሬሽን ሰዎች ጋር መጣላት ብሎ ነገር የለም። 'ምን እናድርግልሽ?' 'ወደየትኛው የልምምድ ማዕከል መሄድ ትፈልጊያለሽ?' ነው የሚሉት። ለልምምድ ወደ ሌላ አገር ብሄድ እንኳ 'የሆቴል እና የምግብ ወጪሽን እኛ ነን የምንከፍለው' ይላሉ።"
ከአትሌቲክስ ጎን ለጎን በኢንቨስትመንት ተሰማርታ እራሷን እና ሌሎችን የመርዳት ጅማሬ ላይ እንዳለች ሲፈን ትናገራለች። በአዲስ አበባ ሩፋኤል ተብሎ በሚጠራው ስፍራ እና ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በሚገኘው ሱሉልታ ከተማ ኢንቨስት ለማድረግ ጥረት እየደረገች መሆኗን ትናገራለች።
"ያው እኔ ገና ታዳጊ አትሌት ነኝ። እንደሌሎቹ ያስቀመጥኩት ሚሊዮን እና ቢሊዮን ገንዘብ የለኝም" የምትለው ሲፈን ወደፊት በኢንቨስትመንቱ ላይ መሰማራት እንደምትፈልግና በተለይ ደግሞ ባደገችባት አርሲ ውስጥ በሚገኙ ትንንሽ ከተሞች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ዕቅድ አላት።
"ተጨቁነው የሚገኙ ሴቶችን እና ታዳጊ ሴት ህጻናትን መርዳት እፈልጋለሁ። ለእራሴ ገንዘብ ማጠራቀም እና ሃብት ማካበት ብቻ ሳይሆን ሌሎችን መርዳት እና ተደስተው መመልከትም ሌላ ሃብት ነው ብዬ ነው የማስበው።"
የምፈራው አትሌት የለኝም የምትለው ሲፈን "የምፈራው አትሌቶችን ሳይሆን እሩጫን ነበር። ሁሌም ማሸነፍ ነው የምፈልገው። ለቅጽበትም ቢሆን መሸነፍን አላስብም። ጠንካራ አትሌት ነች ብዬ የማስባት አትሌት አልማዝ አያናን ነው። አደንቃታለሁ።"
ከስድስት ወር በፊት በእስልምና ሥርዓት መሰረት ኒካህ ያሰረችው ሲፈን፤ ከኦሮምኛ በተጨማሪ የደች እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎችን እንደምትችል አማርኛም ትንሽ ትንሽ እንደምትሞክር ትናገራለች።
የሲፈን የቀድሞ አሰልጣኝ አልቤርቶ ከአበረታች እጽ ጋር በተያያዘ ከአሰልጣኝነት መታገዳቸው ይታወሳል። የቀድሞ አሰልጣኟ ከአትሌቲክሱ እንዲታገዱ መደረጉ በእርሷ ላይ ያስከተለው አሉታዊ ተጽእኖ ስለመኖሩ የተጠየቀችው ሲፈን፤ "ይህ ከእኔ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። እሱ የታገደበት ምክንያት የተፈጠረው ከአስር ዓመት በፊት ነው። እኔ አልቤርቶ መልካም ሰው መሆኑን እና አትሌቶችን ለመርዳት ብዙ የሚጥር ሰው መሆኑን ነው የማውቀው። እኔ በንጹህ ስፖርት ነው የማምነው። ይሁን እንጂ የአልቤርቶ ነገር በጣም አሳዝኖኛል።"
ጃፓን ቶኪዮ ውስጥ በሚካሄደው ኦሊምፒክ ላይ ለመወዳደር ከ800 እስከ 10 ሺህ ሜትር ባሉት የውድድር መስኮች ላይ ለመወዳደር ዕቅድ አላት።
"ጊዜው ሲቃረብ ጠንካራ የሆንኩበትን እመርጣለሁ። ግን 5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር የምመርጥ ይመስለኛል" ትላለች ሲፈን።

















