የኒውዚላንድ አየር መንገድ ለመንገደኞቹ የሚበላ ኩባያ አቀረበ

የሚበላው ኩባያ

የፎቶው ባለመብት, AIR NEW ZEALAND

በአየር ጉዞ ላይ ቡና ከቀረበልዎ በኋላ የበረራ አስተናጋጆች ኩባያዉን ለመሰብሰብ ፍዳቸውን ይበላሉ።

መንገደኞች የበሉበትን ሳህን፣ ማንኪያና ሹካ ለማስወገድም በርካታ ወጪን ይጠይቃል።

የኒውዚላንድ ብሔራዊ አየር መንገድ አንድ ነገር ለምን አንሞክርም በሚል አዲስ ፈጠራን ይዞ ብቅ ብሏል።

ቡና የሚቀርብበት ኩባያ የቫኒላ ቃና እንዲኖረው ተደረገ። ከዚያም የሚበላ አንዳች ብስኩት ነገር ቢሆንስ ብሎ ተነሳ።

ተጓዡ ቡናውን ከጨለጠ በኋላ ኩባያውን ይበላዋል ማለት ነው።

ኩባያው ቡና ቢቀዳበትም በጭራሽ እንደማያፈስ ተረጋግጧል።

ኩባያውን ያመረተው ትዋይስ የሚባል የዚያው የአገር ኩባንያ ነው።

የኒውዚላንድ አየር መንገድ በዓመት 8 ሚሊዮን ኩባያ ቡና ለደንበኞቹ ያቀርባል።

ይህን ሁሉ ኩባያ ታዲያ ቆሻሻ ገንዳ ውስጥ እየጣሉ ማስወደገድ አየር መንገዱን አማሮት ነበር።

ለአየር መበከልም ሆነ ለአካባቢ ጥበቃ አንድ እርምጃ ነው የተባለለት ይህ ዘዴ ገና በሙከራ ደረጃ ነው እየተተገበረ ያለው።

በታላቋ ብሪታኒያ ብቻ በዓመት 2.5 ሚሊዮን የቡና ኩባያ ወደ ቆሻሻ ገንዳ ይጣላል። ከዚህ ውስጥ ተመልሶ ወደ ሥራ የሚገባው 0.25 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, አብራሪ አልባ አውሮፕላን