በቶክዮ ኦሎምፒክ የሁለት አገራት አትሌቶች የወርቅ ሜዳሊያውን ለመጋራት ተስማሙ

የኳታር እና የጣሊያን አትሌቶች

በቶክዮ ኦሎምፒክ የከፍታ ዝላይ የፍጻሜ ውድድር ተወዳዳሪ የነበሩት ሁለት አትሌቶች የወርቅ ሜዳሊያውን ለመጋራት መወሰናቸው በርካቶችን አስገርሟል።

ከኳታር የተወከለው ሙታዝ ባርሺም እና ጣልያናዊው ጂያንማርኮ ታምቤሪ ናቸው የወርቅ ሜዳሊያውን ለመጋራት የወሰኑት።

ሁለት ሰዓታት በፈጀው አድካሚ የመጨረሻ ዙር የከፍታ ዝላይ ውድድር ሁለቱን አትሌቶች መለየት ከባድ የነበረ ሲሆን ሁለቱም 2.37 ሜትር ድረስ ከዘለሉ በኋላ አንደኛውን ከአንደኛው መለየት ከባድ ሆኗል።

አትሌቶቹ በመጨረሻም የመለያ ዝላይ እንዲያደርጉ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

ነገር ግን በሚያስገርም ስፖርታዊ ጨዋነት ሁለቱም አትሌቶች ለአንድ አሸናፊ ብቻ የሚሰጠውን የወርቅ ሜዳሊያ ለመጋራት መስማማታቸው በርካቶችን በደስታ ያስጨፈረ ነበር።

ሁለቱም የኦሎምፒክ ሬከርድ የሆነውን 2.39 ሜትር ከፍታ ላይ ለመድረስ ሶስት ጊዜ ሙከራ ቢያደርጉም አልተሰካላቸውም ነበር። በስተመጨረሻም የወርቅ ሜዳሊያውን የግላቸው ለማድረግ ይፋለማሉ ተብሎ ሲጠበቅ እነሱ ግን ወርቁን አንድ ላይ መውሰድ ነው የምንፈልገው ብለዋል።

በዚህም ታሪክ መስራት ችለዋል። ከአውሮፓውያኑ 1912 በኋላ በኦሎምፒክ መድረክ በአትሌቲክስ የውድድር ዘርፍ የሁለት አገራት አትሌቶች የወርቅ ሜዳሊያውን መጋራት የቻሉ የመጀመሪያዎቹ አትሌሎች መሆን ችለዋል።

የኳታሩ ተወዳዳሪ ሙታዝ ከአድካሚው የሁለት ሰአት ፉክክር በኋላ ወደ አስተባባሪው ጠጋ ብሎ እንደው የወርቅ ሜዳሊያውን መጋራት እንችላለን? ሲል ጥያቄ ያቀርባል። ጥያቄውን ሁለታችሁ ከተስማማችሁ ችግር የለውም የሚል ምላሽ ያገኛል።

የጣልያኑም አትሌት በዚሁ መስማማቱን ተከትሎ የወርቅ ሜዳሊያውን የተጋሩ ሲሆን ለየብቻቸው ደስታቸውን ከመግለጻቸው በፊት አትሌቶቹ ከቡድናቸው ጋር አንድ ላይ ላይ በመሆን አስገራሚ ስፖርታዊ ትእይንት አሳይተዋል።

"በጣም አስገራሚ ነው። ይሄ መንቃት የማልፈልግበት አስገራሚ ህልም ነው የሆነብኝ" የኳታሩ ተወካይ ሙታዝ።

የጣልያኑ ጂያንማርኮ ታምቤሪ ደግሞ "ከጉዳቴ በኋላ ተመልሼ ውድድር ማድረግ እፈልግ ነበር፤ ነገር ግን አሁን የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት ችያለሁ። ይህንን ሁኔታ ብዙ ጊዜ አልሜው ነበር። አሁን እውነት ሆነ" ብሏል።