ኤርዶጋን ቱርክ ለኢትዮጵያ የትኛውንም አይነት ድጋፍ ታደርጋለች አሉ

የቱርክ ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የቱርክ ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን ቱርክ ለኢትዮጵያ የትኛውንም አይነት ድጋፍ ታደርጋለች አሉ።

በፕሬዝደንቱ ይፋዊ የትዊተር አካውንት ላይ እንደተገለጸው፤ ፕሬዝደንት ኤርዶጋን ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ በተወያዩበት ወቅት ፕሬዝደንት ኤርዶጋን ቱርክ ለኢትዮጵያ የትኛውንም አይነት ድጋፍ ማድረጓን ትቀጥላለች ብለዋል።

አናዱሉ የዜና ወኪል የቱርክ ኮሚኒኬሽን ዳይሮክቶሬትን በመጥቀስ እንደዘገበው ኤርዶጋን ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት ቱርክ ለኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት ትልቅ ዋጋ ትሰጣለች ብለዋል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

ቱርክ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ካደረጉ አገራት መካከል አንዷ ስትሆን የጨርቃ ጨርቅ እና የኤሌክትሪክ ማስተላላፊያ ገመዶች ማምረቻዎችን ጨምሮ የቱርክ ኩባንያዎች 2.5 ቢሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ ፈሰስ ማድረጋቸውን ከዚህ ቀደም የቱርኩ ዜና ወኪል አናዱሉ ዘግቧል።

ቱርክ በመካከለኛው ምሥራቅ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ ነች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአምስት ዓመት በፊት ቱርክ ውስጥ በመንግሥት ላይ ተሞክሮ የከሸፈውን መፈንቅለ መንግሥት 5ኛ ዓመት ለማሰብ በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ከቱርክ ተቋማትና በኢትዮጵያ ከሚገኙ ዲፕሎማቲክ ሚሸኖች ጋር ከጥቂት ሳምንት በፊት በነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያና ቱርክ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ ይገኛሉ ብለው ነበር።

አምባሳደሯ "ፖለቲካዊ ግንኙነታችን ጥሩ ነው። የንግድ ግንኙነቱ መጠናከር አለበት በዚህ ላይም እየሰራን ነው። ኢትዮጵያና ቱርክ ወዳጅ አገራት ናቸው ወዳጅ ሆነውም ይቀጥላሉ" ስለማለታቸው የቱርኩ አናዱሉ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ጨምረውም በቱርክ መንግሥት አሸባሪ የተባለውን የፌቱላህ ጉለን ድርጅት የጸጥታ ስጋት እንዳይፈጥር አንካራ እና አዲስ አበባ በጥምረት እየሰሩ ነው ብለው ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም ቱርክ ለኢትዮጵያ ሠራዊት ግልጋሎት ይውላሉ የተባሉ ሰው አላባ አውሮፕላኖችን [ድሮኖች] እያቀረበች ነው መባሉን በኢትዮጵያ የቱርክ ኤምባሲ ሐሰት ነው ሲል ማስተባበሉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቱርክ ሰራሽ ድሮኖች ወደ አገር ውስጥ አስገብቷል የሚሉ ሪፖርቶች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ ነበር ኤምባሲው የማስተባበያ ምላሽ የሰጠው።

line

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ የተከሰተው ግጭት በውይይት እንዲፈታ ጥሪ አቅረበዋል።

ፕሬዝደንቱ ከትናንት በስቲያ ከጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አሕመድ ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት የሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ እንዲገባ እግዶች በሙሉ መነሳት አለባቸው ስለማለታቸው ቤተ-መንግሥታቸው ባወጣው መግለጫ ላይ ተመልክቷል።