ቱርክ ለኢትዮጵያ ድሮኖችን እያቀረበች ነው መባሉን ሐሰት ነው አለች

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አለፕ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

የምስሉ መግለጫ, በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አለፕ

ቱርክ ለኢትዮጵያ ሠራዊት ግልጋሎት ይውላሉ የተባሉ ሰው አላባ አውሮፕላኖችን [ድሮኖች] እያቀረበች ነው መባሉን በኢትዮጵያ የቱርክ ኤምባሲ ሐሰት ነው ሲል አስተባበለ።

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ለሚያካሂደው ወታደራዊ ዘመቻ የሚያገለግሉ ቱርክ ሰራሽ ድሮኖች ወደ አገር ውስጥ አስገብቷል የሚሉ ሪፖርቶች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት መሰራጨታቸውን ተከትሎ ነው ኤምባሲው ምላሽ የሰጠው።

ኤምባሲው በትዊተር ገጹ ላይ እንዳሰፈረው "በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ቱርክ ለኢትዮጵያ መንግሥት ድሮኖችን እያቀረበች ነው በሚል የሚሰራጨው መረጃ የሐሰት ነው" ብሏል።

በትግራይ በተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ላይ የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ተለያዩ ተልዕኮዎችን ማካሄዱን ከዚህ በፊት መገለጹ ይታወሳል።

ቱርክ ከኢትዮጵያ ጋር ሰፊ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ያላት አገር ስትሆን በወታደራዊው መስክ ስላላቸው ግንኙነት ግን በስፋት የሚታወቅ ነገር የለም።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአምስት ዓመት በፊት ቱርክ ውስጥ በመንግሥት ላይ ተሞክሮ የከሸፈውን መፈንቅለ መንግሥት 5ኛ ዓመት ለማሰብ በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ከቱርክ ተቋማትና በኢትዮጵያ ከሚገኙ ዲፕሎማቲክ ሚሸኖች ጋር ሐሙስ ዕለት መወያየታቸውን አናዱሉ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አለፕ በዚሁ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያና ቱርክ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ ይገኛሉ።

"ፖለቲካዊ ግንኙነታችን ጥሩ ነው። የንግድ ግንኙነቱ መጠናከር አለበት በዚህ ላይም እየሰራን ነው። ኢትዮጵያና ቱርክ ወዳጅ አገራት ናቸው ወዳጅ ሆነውም ይቀጥላሉ" ስለማለታቸው የቱርኩ አናዱሉ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ጨምረውም በቱርክ መንግሥት አሸባሪ የተባለውን የፌቱላህ ጉለን ድርጅት የጸጥታ ስጋት እንዳይፈጥር አንካራ እና አዲስ አበባ በጥምረት እየሰሩ ነው ብለዋል።

"ዛሬ ላይ አሸባሪው የፌቱላህ ድርጅት የተዳከመ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች አገራት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል" ብለዋል አምባሳደሯ።

ቱርክ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ካደረጉ አገራት መካከል አንዷ ስትሆን የጨርቃ ጨርቅ እና የኤሌክትሪክ ማስተላላፊያ ገመዶች ማምረቻዎችን ጨምሮ የቱርክ ኩባንያዎች 2.5 ቢሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ ፈሰስ ማድረጋቸውን አናዱሉ አመልክቷል።