የብሔር ግጭትን ፈርተው ከምዕራብ ትግራይ የተሰደዱ የትግራይ ተወላጆች

ግጭት ከተንሰራፋበት ከምዕራብ ትግራይ፣ በየቀኑ ወደ ሱዳን ይሻገራሉ
የምስሉ መግለጫ, ግጭት ከተንሰራፋበት ከምዕራብ ትግራይ፣ በየቀኑ ወደ ሱዳን ይሻገራሉ
    • ፀሐፊ, አንድሩ ሃርዲንግ
    • የሥራ ድርሻ, (ሐምዳይት-ሱዳን)

በእያንዳንዱ ምሽት ማለት ይቻላል ጥብቅ ጥበቃ በሚደረግለት ድንበር ሰዎች ይሾልካሉ፡፡ ቡናማውን ወንዝ ዋኝተው ይሻገራሉ፡፡ የሚሻገሩት ወደ ሱዳን ነው፡፡ የብሔር ግጭት ከተንሰራፋበት ከምዕራብ ትግራይ፣ በየቀኑ ወደ ሱዳን፡፡

ምዕራብ ትግራይ አካባቢው ለም ነው፡፡ አሁን ለኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ታማኝ በሆኑ ወታደሮች ቁጥጥር ሥር ነው፡፡

የትግራይ አማጺዎች እያማተሩ ያሉትም ወደዚህ ቦታ ነው፡፡ ምናልባትም በእጃቸው ለማስገባት ቀጥለው ጥቃት እንፈጽማለን ብለው የሚያልሙት ወደዚህ አካባቢ ነው፡፡ ቁጥጥራቸውን ማጥበቅ ይሻሉ፡፡ ከሱዳን ጋር የሚያገናኛቸው የስንቅና ትጥቅ መስመር እንዲሆናቸው ይሻሉ፡፡

በትግራይ ያለው ቀውስ ከዕለት ዕለት መጠኑን እያሰፋ ነው የመጣው፡፡ ምናልባትም ኢትዮጵያን ወደለየለት የብሔሮች ግጭት ውስጥ እንዳይከታትም ይፈራል፡፡

"እንድንለቅ የሰጡን የጊዜ ገደብ ሁለት ቀን ነው"

"እንድንለቅ የሰጡን የጊዜ ገደብ ሁለት ቀን ነው፡፡ አለዚያ ግን እንደምንገደል ነገሩን" ይላል የ18 ዓመት ዕድሜ ያለው ትግራዋይ፡፡

ይህ ልጅ ገና ወንዙን መሻገሩ ነው፡፡ ከሦስት የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር ሆኖ ነው ወደዚህ የመጣው፡፡ ማንነቱ በሚዲያ እንዲገለጽ አይፈልግም፡፡ ምክንያቱም አገር ቤት ባሉ ዘመዶቹ ላይ የበቀል ጥቃት ይፈጸምባቸዋል ብሎ ይሰጋል፡፡

ይህ ልጅ ከአጎራባች አማራ ክልል የመጡትንና አሁን ይቺን ሑመራ የምትባል ቁልፍ ከተማ የተቆጣጠሩትን ወታደሮች ይከሳል፡፡

"(እነዚህ የአማራ ወታደሮች) ዕድሜያቸው ለትግል ደርሷል ብለው የሚያምኑ ትግራዋይ ወጣቶችን ያጠቃሉ" ይላል፡፡

አሁን እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች እነዚህ የአማራ ሚሊሻዎች በብዙ ቁጥር፣ አዳዲስ ከሚመለምሉት ጋር በመሆን ወደዚህ አካባቢ እየተመሙ መሆኑን ነው የሚጠቁመት፡፡

እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ሲዳማና ኦሮሚያን ጨምሮ ከተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ሚሊሻዎች ወደዚህ ሥፍራ በአያሌ ቁጥር እየጎረፉ ስለመሆኑ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡

"የአማራ ሚሊሻ ቤት ለቤት እየሄዱ ይፈትሻሉ፡፡ ትግራዋይ መሆንን ሲያውቁ ወይ ይገድሉሃል ወይ ያስሩሃል፡፡ በዚህ ጊዜ ስሜታችን ይጎዳል፡፡ ምክንያቱም አገሩ የኛም ነው እኮ፡፡ (በዚህ የተነሳ) ማንኛውም ሰው ከቻለ ለመሰደድ ይሞክራል"፤ ይህን የሚለው ደግሞ ሌላ ዕድሜው በዐሥራዎቹ የሚገመት ወጣት ነው፡፡

ወጣቱ ይህን የነገረኝ በአንድ ማለዳ ሀምዳያት በምትባል የሱዳን ድንበር ከተማ ሳለ ነው፡፡ ሐምድያት የምትገኘው ከሑመራ ማዶ ነው፡፡

ቢቢሲ በቅርብ ቀናት ውስጥ ከሑመራ ሸሽተን መጣን ከሚሉ ስምንት ሰዎችን አነጋግሯል፡፡ ሁሉም እያሉ ያሉት በዚያ አካባቢ የዘር ማጽዳት ጥቃት እንደሚፈጸም ነው፡፡ ሆኖም በትግራይ የስልክ አገልግሎ ስለሌለ ሁኔታዎችን በተጨማሪ ለማመሳከርና ለማረጋገጥ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰሞኑ በሰጠው መግለጫ የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነቱን ሊያቆም እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል፡፡

ምክንያቱ ደግሞ የትግራይ አማጺዎች ትንኮሳ እያደረሱብኝ ነው የሚል ነው፡፡ ይህን ተከትሎም ከተለያዩ ክልሎች ሠራዊት ወደዚያ እየተጋዘ ይገኛል፡፡

የአይቀሬው ጦርነት ምልክቶች

በጭቃማ መሬቶች እና በክረምት መብረቆች የታጀበው የሱዳን የድንበር ከተማ ሐምዳይት በሺህ ለሚቆጠሩ የትግራይ ስደተኞች ሁነኛ የመሸጋገሪያ መስመር ሆኗል፡፡

ለትግራይ ስደተኞች ብቻም ሳይሆን ለትግራይ አማጺዎችም ይህ መስመር መሸጋገሪያ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። አማጺያኑ አንዳንድ ጊዜ ከአቅራቢያ ኤርትራ ታከውም ቢሆን ወደ ሐምዳይት ገባ ወጣ ማለታቸው አልቀረም፡፡

የስደተኞች ቁጥር ደግሞ በቅርብ ጊዜያት ረገብ ማለትን አሳይቷል፡፡

የስደተኞች ጎርፍ የጀመረው ባለፈው ጥቅምት ሲሆን ይህም በማዕከላዊው መንግሥትና በትግራይ ኃይሎች የለየለት ጦርነት የተቀሰቀሰበት ወቅት ስለነበር ነው፡፡

ከዚያ ወዲያ 50ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች በሱዳን መጠለያ ይኖራሉ፡፡ የኑሮ ሁኔታው አስቸጋሪ ነው፡፡ የክረምቱ ዝናባማ ሁኔታና ጎርፍ ተደማምሮ መጠለያቸውን በተደጋጋሚ በንፋስ ጭምር የሚወሰድበት ሁኔታ አለ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ በዚህ ረገድ ብዙ ወቀሳ እየደረሰበት ይገኛል፡፡

በርካታ የደኅንነት ምንጮች ለቢቢሲ እንደሚናገሩት ከሆነ በትግራይና በሁመራ አካባቢ የብሔር ጥቃቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያየሉ መምጣታቸው በራሱ በመጪዎቹ ጊዜያቶች ጠንከር ያለ ጦርነት ስለመኖሩ አመላካች ናቸው፡፡

የትግራይ ኃይሎች በቅርቡ ወደ ደቡብ እና ምሥራቅ ትግራይ የቁጥጥር አድማሳቸውን ማስፋታቸውና ድንገቴና አስደናቂ ድል ማስመዝገባቸው የዝናብ ወቅቱ ሳያይል ምዕራብ ትግራይን ለመያዝ እንዲሞክሩ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

እነዚህ አካባቢዎች በአማራ የይገባናል ጥያቄ የሚነሳባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ የትግራይ ጦርነት ከተነሳ ወዲህ የአማራ ኃይል ይህን አካባቢ በእጁ አስገብቷል፡፡

አሁን ስጋት እየሆነ ያለው በዚህ አካባቢ የሚነሱ ግጭቶች ለተቀረው ኢትዮጵያ ብሎም ለሱዳንና ኤርትራ አለመረጋጋት ምክንያት ሊሆኑ የመቻላቸው ጉዳይ ነው፡፡

‹‹ጦርነቱ አይቀሬ ነው፡፡ የአማራና የትግራይ ሕዝቦች ወንድምና እህት ሕዝቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን መሬታችንን አሳልፈን ልንሰጥ አንችልም፡፡ የደም መፋሰሱ መቀጠሉ ጥርጥር የለውም›› ትላለች በቅርቡ ሐምዲያት ከተማ የደረሰችውና ከስደት በፊት የባንክ ሰራተኛ የነበረች አንዲት አስተያየት ሰጪ፡፡ እሷም ቢሆን ስሟ እንዲገለጽ አትሻም።

‹‹ጦርነት አይቀሬ ነው፡፡ በአማራ ሚሊሻ የሚታሰሩ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል፡፡ ይህ የዘር ማጽዳት ነው፡፡ ትግራዊያንን ከምዕራብ ትግራይ ገፍቶ ማስወጣቱ ተባብሶ ቀጥሏል›› ይላል ዶ/ር ቴዎድሮስ ተፈራ፡፡

"እህቶቼን ከደፈሩ ሰዎች ጋር…አንድ ፓስፖርት እንዲኖረኝ አልሻም"

ዶ/ር ቴዎድሮስ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ነው የሱዳንን ድንበር አቋርጦ ወደዚህ የመጣው፡፡ አሁን በሐምዳይት ትንሽዬ ክሊኒክ ከፍቶ ስደተኞችን ያክማል፡፡

እሱም እንደ ብዙዎቹ ትግራዊያን የነጻ ትግራይን አገር ሆኖ መወለድ ይናፍቃል፡፡

‹‹ራስን እንደ ኢትዮጵያዊ መቁጠር ድሮ ቀረ፡፡ እህቶቼን ከደፈሩ ሰዎች ጋር አገር መጋራትን አልሻም፡፡ ወንድሞቼን ከገደሉ ሰዎች ጋር አገር መጋራትን አልሻም፡፡ ከነዚህ ሰዎች ጋር አንድ ፓስፖርት እንዲኖረኝ አልፈልግም፡፡ ያ እንዲሆን የምፈልግበት ጊዜ ድሮ ቀረ፡፡ አለፈ›› ይላል ዶ/ር ቴዎድሮስ፡፡