
የፎቶው ባለመብት, EPA
በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ
እንቅስቃሴዎችን የዘጋችው አሜሪካ፤ በኢራን ባንዲራ የሚንቀሳቀስ የጭነት መርከብን መጥለፏን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ በሶሻል ትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው
እንዳስታወቁት ‘ቱስካ’ የተሰኘው መርከብ የተያዘው ጉዞውን እንዲያቆም በአሜሪካ ባሕር ኃይል የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ባለማክበሩ ነው።
ኢራን የአሜሪካ እርምጃ የተኩስ አቁም ጥሰት
እንደሆነ የገለጸች ሲሆን “በትጥቅ የታገዘ የባሕር ላይ ውንብድና” ስትል ለጠራችው ለዚህ ድርጊት አጸፋውን እንደምትመልስ ዝታለች።
እርምጃው እንደተወሰደ የተገለጸው ምክትል
ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ከኢራን ጋር የሚደረገውን ጦርነት ለመቋጨት ፓኪስታን ውስጥ በሚካሄደው ሁለተኛ ዙር ድርድር ላይ የአሜሪካን
ልዑክ እንደሚመሩ ዋይት ሀውስ ካረጋገጠ በኋላ ነው።
እስካሁን ኢራን በድርድሩ የመሳተፏን ነገር
አላረጋገጠችም። የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት የአገሪቱ ባለሥልጣናት የአሜሪካ እገዳ በተጣለበት ሁኔታ ድርድር ውስጥ
አንሳተፍም የሚል አቋም ይዘዋል።
ትራምፕ መርከቡ መጠለፉን ባስታወቁበት ልጥፋቸው፤
“ዛሬ የኢራንን ባንዲራ ያነገበ፣ 900 ጫማ የሚጠጋ ቁመት ያለው እና ክብደቱ ከአውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከብ ጋር የሚቀራረብ ቱስካ
ተሰኘ መርከብ የጣልነውን የባሕር እግድ ለማለፍ ሞክሯል፤ ጥሩ አልሄደላቸውም” ሲሉ ጽፈዋል።
አሜሪካ መርከቡ እንዲቆም ማስጠንቀቂያ ብትሰጥም እንዳልተቀበለው ገልጸዋል። “ስለዚህ ባሕር ኃይላችን ኢንጅን የሚገኝበት ክፍል ላይ በመምታት አቁሟቸዋል” ሲሉ የተወሰደውን
እርምጃ ተናግረዋል።
“ቱስካ ከዚህ ቀደም በነበረው የሕገ ወጥ ተግባር
እንቅስቃሴ ምክንያት በአሜሪካ ግምጃ ቤት ማዕቀብ ተጥሎበታል። መርከቡ ላይ ሙሉ በሙሉ ቁጥጥር አለን፤ የተጫነውንም ነገር እያየን
ነው” ብለዋል።
የኢራን ጦር ዋና መስሪያ ቤት ኻታም አል አንቢያ
ቃል አቀባይ ባወጡት መግለጫ አሜሪካ “ከኢራን የንግድ መርከቦች አንዱ በኦማን ባሕር ላይ እያለ ተኩስ በመክፈት፣ የጉዞ ስርዓቱን
በማጥፋት እና መርከቡ ላይ በመውጣት የተኩስ አቁም ጥሰት ፈጽማለች” ብለዋል።
ይህንን ያደረገችው ወታደሮቿን በማሰማራት እንደሆነ
ጠቅሷል። “ኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጦር ኃይሎች በቅርቡ ምላሽ ይሰጣሉ፤ ለዚህ በአሜሪካ ባሕር ኃይል ተፈጸመ በትጥቅ የታገዘ የባሕር
ላይ ውንብድና ድርጊት አጸፋውን ይመልሳሉ” ሲሉም ዝተዋል።