በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪል የትግራይ ተወላጆች ለእስር ተዳርገዋል - ህወሓት

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS
ህወሓት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ በማንነታቸው የሚደርስባቸው ግፍ ተጠናክሯል በማለት ፌደራል መንግሥቱን ወንጀለ።
ህወሓት ይህንን ያለው በትናንትናው ዕለት የትግራይ ክልል መንግሥት በሚል በሰጠው መግለጫ ሲሆን በርካቶች እንግልት፣ መፈናቀል እስርና ሞት እየደረሰባቸው እንደሚገኝም አስታውቋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪል የትግራይ ተወላጆች ነጋዴዎች፣ ባለሃብቶች፣ ምሁራንና ተማሪዎች፣ በመንግሥት በግልና መስሪያ ቤቶች የሚሰሩና ኢ-መደበኛ በሆኑ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ግለሰቦች በማንነታቸው ምክንያት ታስረው ይገኛሉ ብሏል።
በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በባለሥልጣናት መዋከብ እየደረሰባቸው እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ ሪፖርቶች ተሰምተዋል።
ቢቢሲ በማንነታችን ኢላማ ተደርገናል እንዲሁም በዘፈቀደ እየታሰርን ነው ያሉ የትግራይ ተወላጆችንም አናግሯል።
በተለይም በፖሊስ መዋከብ እየደረሰብን ነው የሚሉ ሪፖርቶች መሰማት የጀመሩት የኢትዮጵያ የፌደራል ሠራዊት መቀለን ለቆ መውጣቱን ካሳወቀ በኋላ ነው።
የፖሊስ ቃለ አቀባይ በበኩሉ ማንም ሰው ቢሆን በማንነቱ ኢላማ አይደረግም ሲል ክሱን አጣጥሎታል።
ህወሓት በበኩሉ በትግራይ ተወላጆች ላይ በማንነታቸው ያነጣጠረ እስር ለወራት የቀጠለ ሲሆን በርካቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ይገኛሉ፤ ግማሾቹ ደብዛቸው ጠፍቶ የገቡበት አይታወቅም ብሏል።
እንዲሁም የትግራይ ተወላጆች ሃብትና ንብረት በመዘረፍ ላይ ነው፤ በርካቶችም የሚበሉትና የሚጠጡትን አጥተዋል በማለት ከሷል።
ከዚህ ቀደም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጅ የቀድሞ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አባላት በተለያዩ ማጎርያ ስፍራዎች እየተሰቃዩ እንደሚገኙም በዚህ መግለጫ ላይ ሰፍሯል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ሰኔ 30/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባ ከተማ በአክቲቪስቶች፣ በጋዜጠኞች እና የትግራይ ተወላጅ በሆኑ ሰዎች ላይ እስር እየተፈፀመ እንዲሁም የንግድ ቤቶችም እየታሸጉ እንደሆነ መረጃዎች ደርሰውኛል ብሏል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም እንዲሁ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎችና የሚዲያ ሰዎች እንዲሁም ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎችን ሁኔታም እየተከታተለ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ከሰሞኑ አሶሺየትድ ፕሬስ በዘገባው በአዲስ መልኩ ብሄር ላይ ባነጣጠረ ሁኔታ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች እንደታሰሩና የንግድ ቦታዎችም እንደተዘጉ አስፍሯል።
ይህም በመላው አገሪቱ ላይ እየተከናወነም እንደሆነ በርካታ የትግራይ ተወላጆችን ዋቢ አድርጎ ነው የዘገበው።
በተለይም የኢትዮጵያ መንግሥት ህወሓትን አሸባሪ ነው በማለት መፈረጁን ተከትሎ የትግራይ ተወላጆች ስለ ጦርነቱ አሰቃቂ ገፅታዎች መናገር የበለጠ ጫና ውስጥ ከቷቸዋል በማለት አስነብቧል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ለረሃብ መጋለጣቸውን ተከትሎ እርዳታ ወደ ክልሉ ለመላክና ለማሰባሰብም የትግራይ ተወላጆች እክል እየገጠማቸው ነው ብሏል።
በዚሁ መግለጫ ላይ ህወሓት የትግራይ ኃይሎች መቀለና ሌሎች ከተሞች መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ የልማት አውታሮችን በመቁረጥ "የትግራይ ህዝብ ጉሮሮ ዘግቶታል" ብሏል።
በየብስና በአውሮፕላን የእርዳታ እህል ወደ ትግራይ እንዳይገባ የሕዝብ የትራንስፖርት መጓጓዣና አውሮፕላኖች ወደ ትግራይ እንዳይቀሳቀሱ ታግዷል ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪ የመብራት፣ የስልክ፣ የኢንቴርኔት፣ የባንክና ወዘተ አገልግሎቶችም እንዲቋረጡ በማድረግ ህዝቡን መንግሥት እየቀጣው ነው በማለት "ጀምላዊ የዘር ማጥፋት ወንጀል እቅድም ነው" ብሏል።
ለዚህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምላሽ እንዲሰጥና በትግራይ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን መፈናቀል፣ ሰቆቃ እንግልት፣ እስርና ግድያ እንዲያበቃ ጫና መደረግ አለበት ብሏል።
ጥፋተኞቹም በጦር ወንጀለኝነት ተከሰው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ይገባል በማለትም አፅንኦት ሰጥቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃለ አቀባይ ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው ከሰሞኑ በክልሉ ያለው አካል የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንዲቀበል ካልተገደደ ድርጅቶች ደኅንነታቸውን ማረጋገጥ ካልተቻለም እንደ በረራ፣ የባንክ አገልግሎት እና ቴሌኮምዩኒኬሽን ያሉ አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ ማስገደድ አንችልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት አስቸኳይ እርዳታን አግዷል የሚለውን ክስ አይቀበለውም።
ከሰሞኑም ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ያወጀችው የተናጠል የተኩስ አቁም 'ከበባ' ነው እንዲሁም መንግሥት ረሃብ እየፈጠረ ነው በማለት የአውሮፓ ኮሚሽን ያወጣውን ማስጠንቀቂያ ኢትዮጵያ ውድቅ አድርጋዋለች።
ኢትዮጵያ ያወጀችው "ተኩስ አቁም ሳይሆን ከበባ ነው ረሃብም እንደ ጦር መሳሪያ እያገለገለ ነው" በማለት የአውሮፓ ሕብረት የቀውስ ጉዳዮች ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺክ ለሕብረቱ ፓርላማ በሰጡት ገለፃ መተቸታቸው የሚታወስ ነው።
በብራስልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኮሚሽነሩን ንግግግር አሳዛኝ በማለት ከበባ ነው መባሉንም ውድቅ አድርጎታል።
ኮሚሽነሩ "የኢትዮጵያ መንግሥት የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በማፍረስ፤ መውጫዎችን በመዝጋት ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመበት ነው ማለታቸው መሬት ላይ ያለውን እውነታ ችላ በማለት በመንግሥት ላይ መሰረተ ቢስ ክሶችን መሰንዘርን መርጠዋል" ብሏቸዋል።
ህወሓት በመግለጫው ደቡባዊ ትግራይን መቆጣጠሩን ገልፆ 'አሁንም የሚበዛው የምዕራባዊ ዞንና አንዳንድ የደቡባዊ ትግራይ አካባቢዎች ነፃ ባለመውጣት ሕዝቡ በርካታ ዘግናኝ ግፎችና በደሎች እየደረሱበት ነው" ብሏል።
"ነፃ ባልወጡት የትግራይ ቦታዎች የሚኖረውን ሕዝባችን ጨምሮ ባጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ እንደሕዝብ በጥይት፣ በረሃብ በፆታዊ ጥቃትና ሃብትና ንብረቱን በማውደም ከምድረገፅ ለማጥፋት ቀርፀው ተግባራዊ ያደረጉትን እኩይ ፓኬጅ አሁንም አጠናክረው ቀጥለውበታል" ብሏል።
የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአውሮፓ ሕብረት ልዩ ልዑክ ፔካ ሃቪስቶ "በየካቲት ወር የኢትዮጵያን ከፍተኛ አመራር ባገኘሁበት ወቅት ይጠቀሙበት የነበረው ቋንቋ የትግራይን ሕዝብ እንደሚያጠፉት፤ የትግራይን ሕዝብ ሙሉ በሙሉ በሚቀጥሉት 100 ዓመታት እንደሚጠራርጉት የመሳሰሉትን ነው" በማለት መናገራቸው ይታወሳል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በወቅቱ "ይህ ኃላፊነት የጎደለው ነው፣ ፈፅሞ ሐሰት ነው፣ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ መንገድን የተከተለ አይደለም" በማለት የልዑኩ መግለጫ የተደበቀ አላማ ያለው ሲሆን በተለይም ከፍተኛ የኢትዮጵያ አመራሮች የትግራይን ሕዝብ ማጥፋት ይፈልጋሉ የሚለውም ጉዳይ ልዑኩ በምናባቸው ወይም በሆነ መንገድ ትውስታቸው ተዛብቶ ይሆናል ብሏል።
ከሰሞኑ ህወሓት ምዕራብ ትግራይ የሚላቸውን ግዛቶች በተመለከተ የአማራ ክልል ቀደም ሲል የተወሰዱብኝ አካባቢዎች ናቸው በማለት የሚነሳው ጥያቄ ተቀባይነት የሌላቸውና የአማራ አካባቢዎች ናቸው የሚል ምላሽ ተሰጥቷል።
የአማራ ክልል ብሔራዊ መንግሥት ከትናንት በስቲያ ባወጣው በመግለጫው፤ "የአማራ ሕዝብ የማንነትና የወሰን ጥያቄ እያነሳ ሲታገልባቸው የቆዩ የራያ አላማጣና ኮረም አካባቢዎችን ዳግም በመውረር እንዲሁም ወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ በኃይል ለመያዝ በተለይም ጠለምትና አካባቢውን ለመያዝ" እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብሏል
ክልሉ ህወሃት ከአማራ ክልል ጋር በሚያዋስኑት ሁሉም አቅጣጫዎች መጠነ ሰፊ ወረራና ጥቃት እየፈጸመ እንደሚገኝ አስመልክቶ፤ ሕዝቡ ራሱን እንዲያዘጋጅና የመንግሥትን ጥሪ እንዲጠባበቅ ጥሪ አያቀረበ ሲሆን ህወሓትም በመግለጫው የትግራይ ሕዝብ ለትግል እንዲነሳ ጥሪ አቅርቧል።
በአሁኑ ወቅት ያለውን የውጊያ መፋፋምም አስመልክቶ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ለአላስፈላጊ ስቃይ እና ሞት የሚዳርግ ነው በማለት ያላቸውን ስጋት በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
አምባሳደሯ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት በድርድር የተመሰረተ የተኩስ አቁም እና ፖለቲካዊ ውይይት ሊስማሙ ይገባል ብለዋል።












