ህወሓት የተኩስ አቁሙን እንዲቀበል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት እንዲያደርግ ተጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, The Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia
የፌደራሉ መንግሥት ያወጀውን የተናጠል የተኩስ አቁም ተግባራዊነቱ ይረጋገጥ ዘንድ ህወሓት ስምምነቱን እንዲያከብር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት እንዲያደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።
ይህ የተነገረው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በየሳምንቱ በሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በኩል ነው።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሰብዓዊ የተኩስ አቁም ተግባራዊነት የጋራ ጥረት እንዲሁም ሌላኛው ወገን እንዲቀበል ግፊት ማድረግ አለበት ተብሏል።
በክልሉ ያለው አካል የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንዲቀበል ካልተገደደ ድርጅቶች ደኅንነታቸውን ማረጋገጥ ካልተቻለም እንደ በረራ፣ የባንክ አገልግሎት እና ቴሌኮምዩኒኬሽን ያሉ አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ ማስገደድ አንችልም ብለዋል ቃለ አቀባዩ በመግለጫቸው።
ህወሓት በስምምነት ላይ የተደረሰ የተኩስ አቁም እንደሚቀበል ያስታወቀ ሲሆን ካስቀመጣቸው ሰባት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ከክልሉ የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ክልል ኃይሎች ወጥተው ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚጠይቀው ይገኝበታል።
ባለፉት ወራት ጦርነቱን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን እንዲመረመሩ እንዲሁም ቴሌኮም፣ መብራትና የአውሮፕላን በረራን ጨምሮ የተቋረጡ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች እንዲጀመሩም ጠይቋል።
የፌደራሉ መንግሥት በበኩሉ እነዚህ አገልግሎቶች እንዲቀጠሉም ከተፈለገ "ሌላኛው ወገን ጠብ አጫሪነቱን ማቆም አለበት" ብለዋል ቃለ አቀባዩ።
በዚህ ወቅት መንግሥት ዋስትና የሚሰጠው ሁሉም የሰብዓዊ ድጋፎች ደኅንነታቸው ተጠብቆ በሰላማዊ መንገድ ወደ ትግራይ ክልል ድንበር መድረሳቸውን ማረጋገጥ ነው ሲሉም የመንግሥትን አቋም አስታውቀዋል።
አምባሳደሩ እንደሚናገሩት ምንም እንኳን በመንግሥት የተወሰነው የአንድ ወገን ተኩስ አቁም ብዙዎችን ቢያስገርምም ውሳኔው በድንገት አልተወሰደም ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት ከተመረጠ የተኩስ አቁም ማወጅ እና ከምርጫው በኋላ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር ሁሉን አቀፍ ውይይ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን እያሰበ ነበር ብለዋል።
ይህም ከታችኛው አመራርና ተራ የህወሓት አባላትን እንደሚጨምርም ጠቁመዋል።
በክልሉ ተፈጽመዋል በተባሉ የመብት ጥሰቶችም ላይ የተባበሩት መንግሥታትና ኢሰመኮ የሚያደርጉትን የጋራ ምርመራዎች ለመደገፍ መንግሥታቸው ቁርጠኛ መሆኑንም ተናግረዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን በኩል ኢትዮጵያ የተኩስ አቁሙን ለማወጅ የወሰነችበት ሁኔታም ተገልጿል፤ ከዚህም መካከል አብዛኛዎቹ የህወሓት የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎች በመገደላቸውና በመታሰራቸው እንዲሁም የቀሩትን ጥቂት የህወሓት አመራሮች ለመያዝ ሲባል ጦርነቱን መቀጠል አስፈላጊ ባለመሆኑ ነው ተብሏል።
በክልሉ ያሉ ነዋሪዎች የግብርና ወቅታቸውን እንዳይስተጓጎል፣ የረድዔት ድርጅቶች የበርካቶችን ህይወት እንዲያድኑ እድል ለመስጠት እንዲሁም የግጭቱ የመጀመሪያ ገፈት ቀማሽ የትግራይ ሕዝብ ሰላም የሚያስፈልገው በመሆኑ እና ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሄ የሚፈልግ በመሆኑ ከጠቀሷቸው ምክንያቶች ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላይ ባደረጉት ንግግር አገሪቱ የማያስፈልጓት በርካታ ኤምባሲዎች እንዳሏትና ለተጨማሪ ወጪ እየዳረጓት ስለሆነ ከ30 በላይ ኤምባሲዎችን እንደምትዘጋ ተናግረው ነበር።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የኬንያው ጋዜጣ ኔሽን በኬንያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሚዘጉ 30ዎቹ መካከል እንደሆነ በሰኔ 28 ዕትሙ አስነብቦ ነበር።
በኬንያ የሚገኘው ኤምባሲም መረጃው ስህተት እንደሆነና "እንደ ኬንያ ያሉ የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት ለኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ ቀዳሚ ሆነው ይቀጥላሉም" ተብሏል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አገሪቱ ከዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዋ የምትጠብቀውን እንድታገኝ የአንዳንድ የተልዕኮዎችን መዋቅር እንደገና ማዋቀር ሊኖርበት እንደሚችልም ጠቁሟል።
ከዚህም በተጨማሪ በሄግ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኔዘርላንድስ በጨረታ ሊሸጡ የነበሩ ቅርሶችን ማስመለሱም ተገልጿል።
ቅርሶቹ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን በፊት በመካከለኛው ዘመን የነበሩ ጥንታዊ መፃህፍትና ሌሎች ቅርሶች እንደሚገኙበት ተጠቅሷል። ቅርሶቹ ኔዘርላንድ ውስት በቬንዱሁይስ ደር ኖታሬስ ባለፈው ወር ለጨረታ ሊቀርቡ ነበር።












