ኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት ልዑክ መግለጫ "ኃላፊነት የጎደለው" ነው አለች

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia
የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአውሮፓ ሕብረት ልዩ ልዑክ ፔካ ሃቪስቶ የኢትዮጵያ ከፍተኛ አመራሮች "የትግራይን ሕዝብ ማጥፋት ይፈልጋሉ" የሚለው ንግግር ኃላፊነት የጎደለውና ፍፁም ሐሰት ነው በማለት ኢትዮጵያ አስታውቃለች።
"ይህ ኃላፊነት የጎደለው ነው፣ ፈፅሞ ሐሰት ነው፣ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ መንገድን የተከተለ አይደለም" ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ አርብ ሰኔ 11/2013 ዓ.ም በማኅበራዊ ትስስር ገፁ ባወጣው መግለጫ።
ሚኒስቴሩ የአውሮፓ ሕብረት ልዩ ልዑክ በመሆን በኢትዮጵያና በሱዳን ያደረጉትን ጉብኘት አስመልክቶ ሰኔ 8/2013 በሕብረቱ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴና የልማት ኮሚቴ ባደረጉት የጣምራ ስብሰባ ላይ ነው ይህንን የተናገሩት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የልዑኩን መግለጫ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደረገው ሲሆን "የኢትዮጵያ መንግሥትን ሆን ብሎ ዝቅ ለማድረግና በአሳሳች መረጃና ፍፁም በሆነ ሐሰት የማያስፈልግ ጣልቃ ገብነት ለመፍጠር የሚደረግ ግልፅ ማሳያ ነው" ብሏል።
ሚኒስቴሩ መግለጫውን "አሳፋሪ" ያለው ሲሆን ኢትዮጵያ ያለችበትን እውነታንም ሆነ ኢትዮጵያን የማያውቅ ብሎታል።
ሚኒስትሩ በሁለት አጭር ጉብኝት "ኢትዮጵያንም ሆነ ሕዝቧን አውቃለሁ ያሉበት መንገድ የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን እንደሳቸው ባሉና ትክክል ነን ብለው በሚያምኑ መካከል የቅኝ ግዛት እሳቤ እንዳልተለያቸው ማሳያ ነው" ብሏል።
ልዑኩ የአውሮፓ ሕብረት በትግራይ ክልል ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባቸዋል የሚሉትን ተግባራትን በተመለከተና ስላለው ሂደት ተናግረዋል።
የሕብረቱ አቋም የኤርትራ ወታደሮች ክልሉን ለቀው እንዲወጡ፣ ያልተቋረጠ የሰብዓዊ እርዳታ መድረስ፣ ነፃ ገለልተኛ ምርመራ፣ በትግራይና በማዕካላዊ መንግሥት ውይይት እንዲደረግና የተኩስ አቁም አዋጅ የሚሉ ናቸው።
ሚኒስትሩ በየካቲት ጉብኝታቸው ወቅት በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የኤርትራ ወታደሮች በክልሉ አልገቡም የሚለውን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና መፈናቀሎች አልተፈፀሙም የሚል ነበር ብለዋል።
ነገር ግን ሚያዝያ ወር ላይ በነበረው ጉብኝት በተወሰነ መልኩ የሰብዓዊ እርዳታ እንደደረሰ ተናግረዋል፤ ነገር ግን ያልተገደበ አይደለም ብለዋል።
በሁለተኛ ወገን ነፃና ገለልተኛ የሆነ ምርመራ የሚለው የመንግሥት የሆነው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እየሰሩ ነው ውጤቱንም እየተጠበቀ ነው ቢሉም የኤርትራ ወታደሮች ከክልሉ አልወጡምም ብለዋል፤ የተኩስ ማቆምም ተፈፃሚ እንዳልሆነም አስታውሰዋል።
በሚያዝያ ወር ላይ በነበረው ጉብኝት ሕብረቱ እንደ አቋም የያዘውን የኤርትራ ወታደሮች የሚወጡበትን መንገድ ጨምሮ፣ የተኩስ አቁም አዋጅና ከትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲ ጋር ውይይት መጀመር አለበት የሚለውንም መልዕክት እንዳስተላለፉ ተናግረዋል።
ትግራይን በጎበኙበት ወቅት የጤና ማዕከላት መውደማቸውን፣ የተደፈሩ ሴቶችን ማየታቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከምዕራብ ትግራይ ከ1 አስከ 2 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ መፈናቀሉንና በርካቶቹ በትምህርት ቤቶችና በሌሎች አካባቢዎች ጊዜያዊ መጠለያ እንዳሉም በዚህ ወቅት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ተፈናቃዮቹን እንደሚመልስ ቢናገርም እርግጠኛ የሆነ እቅድ የለም ያሉት ሚኒስትሩ፤ በአጠቃላይ በክልሉ ከፍተኛ የሰብዓዊ ከፍተኛ ቀውስ ሊመጣ እንደሚችልም አስረድተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መንግሥት ከትግራይ ተቃዋሚዎች ጋር ውይይት የሚለውን እንደማይቀበለውና "ህዋሱ በትግራይ ተቃዋሚ ሳይሆን በሕገ መንግሥታዊ መንገድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ የተባለ ነው" ብሏል።
የተኩስ አቁም መካሄድ አልተቻለም በሚለውም ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩሉ "የሕግ ማስከበር ዘመቻው በሁለት እኩል ኃይሎች ሳይሆን የአሸባሪው ህዋስ በአገሪቱ ላይ ብጥብጥ እንዳያመጣ የሚደረግ ነው። መንግሥት የአሸባሪው ህዋስ ትግሉን ትቶ እጁን እንዲሰጡ በመንግሥት የቀረበላቸውን ጉዳይ ሚኒስትሩ ችላ ብለውታል" ብሏል።
የልዑኩ መግለጫ የተደበቀ አላማ ያለው ሲሆን በተለይም ከፍተኛ የኢትዮጵያ አመራሮች የትግራይን ሕዝብ ማጥፋት ይፈልጋሉ የሚለውም ጉዳይ ልዑኩ በምናባቸው ወይም በሆነ መንገድ ትውስታቸው ተዛብቶ ይሆናል ብሏል።
ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ አባሉ ሚክ ዋላስ በዚህ ወቅት "በኢትዮጵያ የጦር ወንጀሎች ተፈፅመዋል? ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ኢሳያስ አፈወርቂ የጦር ወንጀሎችን ፈፅመዋል ብለው ያምናሉ? ነፃ የሆነ ምርምራስ ይኖራል ብለው ያስባሉ? እነዚህ አመራሮች በጦር ወንጀሎች ይጠየቃሉ?" ለሚለው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው።
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ወይም የጦር ወንጀሎች ተፈፅመዋል የሚሉ ጥያቄዎች አሉ ያሉት ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት ነፃ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሪፖርቶች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ድርጅት ሪፖርት መጠበቅ እንዳለበት መክረዋል። ይሄ ጉዳይም በተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ ጉባኤ ሊታይ እንደሚገባው ጠቅሰዋል።
"ለኔ በተለይም በሴቶች ላይ ያለው ጥቃት በቀጠናው ባለው የትኛውም ጦርነት ተፈፅሞ አያውቅም" ብለዋል ልዩ ልዑኩ።
የኢትዮጵያ ፍላጎት በዚህ ጉዳይ ላይ ምንድን ነው የሚለውን ያስረዱት ሚኒስትሩ "በየካቲት ወር የኢትዮጵያን ከፍተኛ አመራር ባገኘሁበት ወቅት ይጠቀሙበት የነበረው ቋንቋ የትግራይን ሕዝብ እንደሚያጠፉት፤ የትግራይን ሕዝብ ሙሉ በሙሉ በሚቀጥሉት 100 ዓመታት እንደሚጠራርጉት የመሳሰሉትን ነው።
"ይህ ለኔ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችንና ወንጀሎችን የሚያመላክት ነው። የራስህን ዝቅተኛ ቁጥር ያለውን ሕዝብ ጠራርገህ የምታጠፋ ከሆነ ይሄ ምንድን ነው? ሁሉንም የትግራይ ሕዝብ ልታጠፋ አትችልም። በጣም ግልፅ የሆነ ነገር ነው፤ ምላሸ ልንሰጥ ይገባል ምክንያቱም ይሄ ለኛ የዘር ማፅዳት ሊሆን ይችላል" ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በአውሮፓ ፓርላማ ላይ "የኢትዮጵያ ከፍተኛ አመራሮች የትግራይን ሕዝብ ለመቶ ዓመታት ጠራርገው ማጥፋት" ይፈልጋሉ የሚለው የልዑኩ ቃል ፈፅሞ የተፈበረከ ነው ብሏል።
"በሰብዓዊ ስጋት ሽፋን እንዲህ አይነት የቅኝ ግዛትና የበላይነት ሁኔታን ማካሄድ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ መንግሥት አይቀበለውም" ብሏል።
ልዑኩ ሁለት ጊዜ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ በመጡበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ፣ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና የሰላም ሚኒስትሯን ሙፈሪያት ካሚል ጋር የትግራይ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፤ እንዲሁም ደመቅ ያለ አቀባበል ነው የተደረገላቸው ብሏል መግለጫው።
መግለጫው አክሎም በዚህ ምክንያት ፔካ ሃቪስቶ የኢትዮጵያንና የአውሮፓ ሕብረትን ግንኙነት ታማኝ ተወካይ መሆናቸውን እንደማይቀበል ተናግሯል።
ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር የአጋርነቱን ግንኙነት ብትፈልግም የአውሮፓ ሕብረት ገለልተኛ በሆነ መንገድ ሊሰራ ይገባል። ችግሩንም ለመፍታት ገንቢ በሆነ መልኩ ሊሰራ ይገባል ብሏል።
የአውሮፓ ሕብረት በበከሉ ጦርነቱ ከተጀመረበት ዕለት ጀምሮ ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከህወሓት እንዲሁም ከአውሮፓ ሕብረት አምባሳደሮች ጋር ውይይት ማድረጉንና ስጋቱንም መግለፁን አስታውቆ፣ ጦርነቱ በርካቶችን መግደሉን፣ ሁለት ሚሊዮኖችን ማፈናቀሉንና እንዲሁም መሰረተ ልማቶችን አውድሟል ብሏል።












