"በሰብአዊ ድጋፍ ስም የጦር መሳሪያ አሾልኮ ለማስገባት ተሞክሯል" የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia

በትግራይ ክልል በሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ የተሰማሩ አንዳንድ ወገኖች የጦር መሣሪያ አሾልከው ለመስገባት መሞከራቸውን የውጭ ጉዳይ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለውን ጥረት ከግንዛቤ ባላስገባ ሁኔታ "ተከፈተባት ባሉት ዘመቻ" ዙሪያ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ላይ ነው።

ሚኒስትሩ የተወሰኑ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አባላት የሆኑ ግለሰቦችና አጋሮች ሰብአዊ ስጋቶችን እንደሰበብ በመጠቀም "የአገሪቱን የግዛት አንድነትና ሉአላዊነትን የሚጻረር ተግባርን እያከናወኑ ነው" በማለት ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።

ጨምረውም አንዳንድ ወገኖች "በሰብአዊ ድጋፍ ስም የጦር መሳሪያዎችን ለሽብርተኛ ቡድን አሾልከው ለማስገባት መሞከራቸውን የሚያመለክቱ አሳማኝ ማስረጃዎች" እንዳሏቸው ያመለከቱ ሲሆን ዝርዝሩን ግን ከመናገር ተቆጥበዋል።

የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ወራትን ያስቆጠረውን በትግራይ ክልል ውስጥ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ለችግር ለተጋለጡ ነዋሪዎች አስፈላጊውን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ማቅረብ ባለመቻሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከረሃብ አፋፍ ላይ መሆናቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰብአዊ እርዳታ የማይቀርብ ከሆነ ከአስርት ዓመታት በፊት በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው አይነት ረሃብ ሊከሰትና በርካታ ሰዎች ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት የሰብአዊ እርዳታ ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ማርክ ሎውኮክ አስጠንቅቀው ነበር።

አንዳንዶችም የኢትዮጵያ መንግሥት ረሃብን እንደጦር መሳሪያ እየተጠቀመበት ነው ሲሉም ከሰዋል።

ይህንን በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ "ኢትዮጵያ በዜጎቿ ላይ ረሃብን እንደጦር መሳሪያ እየተጠቀመች ነው የሚለው ክስ በእጅጉ የሚያሳዝን ውሸት ከመሆኑ በተጨማሪ ለሠላም፣ ለትብብርና ለመረጋጋት የማያግዝ" በማለት ውድቅ አድርገውታል።

ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ የያዘችበትን መንገድ በተመለከተ እየተካሄደባት ነው ባሉት ተገቢ ያልሆነ ዘመቻ ማዘኗን የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን፤ በትግራይ ክልል መንግሥትና ሌሎች የረድኤት ድርጅቶች ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች እስካሁን ስላቀረቡት እርዳታ በዝርዝር አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ውስጥ የተከሰተውን ሰብአዊ ቀውስ በተመለከተ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ ከመሆኑ በተጨማሪ በክልሉ ውስጥ ሙሉና ያልተገደበ የእንቅስቃሴ ፈቃድ መስጠቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሚኒስትሩ ለመንቀሳቀስ የደኅንነት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ወደሚኖሩ ሰዎች የረድኤት አቀርቦት እንዲደርስ መንግሥት ወታደራዊ እጀባ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት ችላ በማለት በተከፈተበት ዘመቻ በእጅጉ ማዘኑን የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥታቸው በአዎንታዊና ገንቢ በሆነ መልኩ አብረውት ለመሥራት ከሚፈልጉ አጋሮች ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በርካታ አገራት በትግራይ ክልል ያለው ሰብአዊ ቀውስ በእጅጉ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ የተኩስ አቁም እንዲደረግና አስፈላጊው የእርዳታ እንዲቀርብ በተናጠልና በጋራ ጥሪ እያደረጉ ይገኛሉ።

በአሁኑ በትግራይ ክልል አስከፊ የረሃብ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል በመግለጽ አስፈላጊው ድጋፍ በአስቸኳይ እንዲቀርብ ግፊት እየተደረገ ሲሆን፤ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ እየተደረገ ባለው የቡድን ሰባት ስብሰባ ላይ በትግራይ ያለው ሁኔታ ከውይይት አጀንዳዎች መካከል አንዱ እንደሚሆን ተነግሯል።

ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በትግራይ ክልል ውስጥ በርካታ ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው የተነገረ ሲሆን፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው በክልሉ ውስጥ እንደሚገኙና ከክልሉ ነዋሪ አብዛኛው የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈለገው ተገልጿል።

በጦርነቱ ሳቢያ በተከሰተ የምግብ አቅርቦት ችግር ምክንያት ከ350 ሺህ በላይ ሰዎች በትግራይ ክልል ውስጥ በረሃብ አደጋ ውስጥ እንደሚገኙና ሌሎች ሚሊዮኖች ተመሳሳይ አደጋ እንደተጋረጠባቸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶችና በእርዳታ ተቋማት የተሰራን ትንተናን ጠቅሶ ሮይተርስ ባለፈው ሳምንት ዘግቦ ነበር።

የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ግን በክልሉ ውስጥ ምንም አይነት የምግብ እጥረት እንደሌለ አመልክተው "ምክንያቱም 91.3 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በአምስት እርዳታ ድርጅቶች እየተረዳ ይገኛሉ" ብለዋል።

ኮሚሽነሩ ከቀናት በፊት በክልሉ ውስጥ ስላለው የእርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ እንደተናገሩት "ለ4.5 ሚሊዮን ሕዝብ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎች በመጀመሪያው ዙር፣ በሁለተኛውና በሦስተኛው ዙር ለ5.2 ሚሊዮን ሕዝብ" ቀርቧል ብለዋል።