የተመድ ባለስልጣን በትግራይ 'ረሃብ አለ' ብለዋል ለመሆኑ ረሃብ አለ የሚባለው ምን ሲከሰት ነው?

አንድ ሕጻን በትግራይ ክልል የእርዳታ የእህል ማዳበሪያ ላይ ተኝቶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አንድ ሕጻን በትግራይ ክልል የእርዳታ የእህል ማዳበሪያ ላይ ተኝቶ

የተባበሩት መንግሥት ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርክ ሎውኮክ "በአሁኑ ወቅት ትግራይ ውስጥ ረሃብ አለ" ሲሉ ትናንት ተናግረዋል።

ሎውኮክ ይህን ያሉት ትግራይን በተመለከተው የአውሮፓ ሕብረት እና የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት የውይይት መድረክ ላይ ነው።

በውይይቱ ማን ምን አለ የሚለውን ለመመልከት ከዚህ በታች ያለውን ሊንክ ይጫኑ፡ ትግራይን በተመለከተው ውይይት የአሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ባለስልጣናት ምን አሉ?

ሎውኮክ "አዎ ረሃብ አለ" ካሉ በኋላ "ሁኔታው እየከፋ ይሄዳል" ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሥልጣን በትግራይ ያለውን ሁኔታ የገለጹበት ቃል በእንግሊዝኛው 'ፋሚን' (famine) የሚለውን የከፋ ረሀብና ቸነፈር መከሰትን የሚያጠቁመውን ቃል ነው።

ማርክ ሎውኮክ ይህን ያሉት በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፍ ጥናት በክልሉ ከተደረገ በኋላ ነው። ይህ የሁኔታዎችን የአስከፊነት ደረጃ የሚተነትነው ሥነ ዘዴ "ኢንተግሬትድ ፌዝ ክላሲፊኬሽን" ወይም በምህጻሩ (አይፒሲ) በመባል ይጠራል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በአንጻሩ ሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በአብዛኛው የትግራይ ክልል ውስጥ እየተዳረሰ መሆኑንና አቅርቦቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጿል። ከቀናት በፊት መንግሥት በሰጠው መግለጫ ላይ በትግራይ ረሃብ ተከስቷል መባሉን አጣጥሎታል።

በትግራይ ረሀብ ተከስቷል ያሉት የተመድ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርክ ሎውኮክ

የፎቶው ባለመብት, FABRICE COFFRINI

የምስሉ መግለጫ, በትግራይ ረሀብ ተከስቷል ያሉት የተመድ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርክ ሎውኮክ

ኢንተግሬትድ ፌዝ ክላሲፊኬሽን ትንተና ምን ይላል?

በአንድ አካባቢ ያለ የምግብ አቅርቦት ችግር በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለመናገርና የችግሩ ስፋት ለመግለጽና ሁኔታውን ለመበየን አገልግሎት ላይ የሚውል ትንታኔ ነው።

ይህ ትንተና በትግራይ ክልል እንዲሁም በአጎራባች የአማራና የአፋር አካባቢዎች ውስጥ ከ350 ሺህ በላይ ሰዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳሉ አሳይቷል።

በተለይ በትግራይ ጦርነቱን ተከትሎ ዜጎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙና 1.7 ሚሊዮን ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉም ትንተናው አውስቷል።

በዚህ ትንተና መሠረት በትግራይ የምግብ ሁኔታ ደረጃ አምስት 'ካታስትሮፊ' በሚባል አደጋን በሚኣስከትል ደረጃ ያለ እንደሆነ አስቀምጧል። ይህም ማለት የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ረሃብ ለሞት ሲዳርጋቸውና ይህም ሁኔታ እየሰፋ ሲሄድ ማለት ነው።

ነገር ግን ወደለየለት ረሃብና ቸነፈር [ፋሚን] ያልደረሰ የምግብ እጥረት ችግርን ነው ይህ 'ካስትሮፊ' የሚለው ቃል የሚያመላክተው።

ትንተናው እንደሚለው ይህ ሁኔታ የተከሰተው በጦርነቱ የተነሳ የሰዎች መፈናቀል፣ የጉዞ እቀባ፣ የተገደበ የሰብአዊ እርዳታ እንደቅስቃሴ፣ ገበሬዎች ምርታቸውን አለመሰብሰብ፣ ከብቶቻቸውን ማጣት የተስተጓጎለ ወይም ፈጽሞ የቆመ ግብይት መከሰት ሲሆን ይህም የረሃብ ደረጃው 'ካታስትሮፊ' በሚለው እርከን እንዲሆን የሚያድርጉ ናቸው።

ይህ ትንተና እንደሚለው ከግንቦት ወር ወዲህ 5.5 ሚሊዮን ሰዎች በከፍተኛ የምግብ እጦት ላይ የሚገኙ ሲሆን ይህም እስከ መስከረም ድረስ እየከፋ እንደሚሄድ ይተነብያል።

ይህ ትንታኔ ክስተቱን በከፋ ረሃብና ቸነፈር ወይም በእንግሊዝኛው [ፋሚን] በሚል አልገለጸውም።

የአይፒሲ ትንተና እስከ አሁን በኢትዮጵያ መንግሥት ዕውቅና ወይም ተቀባይነት አልተሰጠውም።

የለየለት ረሀብ [ፋሚን] ምንድነው?

በወል ስም ረሃብ የምንለው ቃል በእንግሊዝኛው 'ፋሚን' በሚለው ቃል ቢወከልም ይህን የእንግሊዝኛ ቃል ተጠቅሞ የረሃብን ስፋት ለመግለጽ እና የረሃብ ችግርን 'ፋሚን' ብሎ ለመጥራት መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ።

የኢንተግሬትድ ፌዝ ክላሲፊኬሽን ትንተና በትግራይ የተከሰተውን ሁኔታ የለየለት ረሃብ በእንግሊዝኛው 'ፋሚን' በሚል ቃል ከመጥራት ተቆጥቧል።

ይህም የሆነው የለየለት ረሃብ የችግሩ የመጨረሻ ደረጃ በመሆኑና ይህን ቃል ለመጠቀምም መሟላት ያለባቸው ሁኔታዎች በመኖራቸው ነው።

ለጊዜው ይህን ትንታኔ ለመጠቀም የመረጠው ቃል 'ካታስትሮፊ' የሚለውን ነው። ይህም ከፋሚን አንድ ደረጃ ዝቅ ብሎ የሚገኝ ሆኖ ነገር ግን ወደለየለት ረሃብ [ፋሚን] የሚወስዱ ሁኔታዎች እንዳሉ የሚጠቁም ቃል ነው።

በሚቀጥሉት ወራትም በትግራይ የለየለት ረሃብና ቸነፈር [ፋሚን] ሊከሰት እንደሚችል ይተነብያል።

ደረጃ አምስት ካታስትሮፊ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሲራቡና ቁጥራቸውና ችግሮቻቸው ቀስበቀስ እየተስፋፋ ሲሄድ የሚያሳይ ሁኔታ ሲታይ አገልግሎት ላይ የሚውል ቃል ሲሆን፤ የለየለት ረሃብና ቸነፈር [ፋሚን] የሚለው ቃል ግን ከፍ ያለ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ በረሃብ መርገፍ ሲጀምር አገልግሎት ላይ የሚውል ቃል ነው።

በአሁኑ ወቅት በትግራይ ፋሚን በሚለው ቃል የሚገለጽ ሁኔታ እንደሌለ ትንታኔው ይደመድማል።

ሆኖም ግን አንዳንድ ተንታኞች ነገሩን የቃላት ፖለቲካ እንጂ ሌላ አይደለም ብለው ያምናሉ። ምናልባትም የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ ይህን የቃላት ብያኔ ልዩነት ቸል ብለው በትግራይ 'የለየለት ረሃብ ገብቷል' ለማለት ፋሚን የሚለውን ቃል ጭምር ለመጠቀም የፈለጉት በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሎ ተገምቷል።

ተመድ ረብ ተከተሰ የሚለው መቼ ነው?

የተባበሩት መንግሥት በአንድ አካባቢ ረሃብ ተከስትሏ ብሎ ከመፈረጁ በፊት የሚከተለው መመሪያ አለው።

ዘለግ ላለ ጊዜ የቆየ ድርቅ እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች የምግብ አቅርቦትን ሲገድቡ የግድ የለየለት ረሃብ ገባ የሚያስብሉ ሁኔታዎች ላይፈጠሩም ይችላሉ ይላል መመሪያው።

የለየለት ረሃብ ገባ ሊባል የሚችለው በምግብ እጦት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍ ሲል፣ ለመኖር የሚያስፈልግ መሠረታዊ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አጋጥሞ ሁኔታው ከዕለት ዕለት እየከፋ ሲሄድ ነው።

የለየለት ረሃብ ገባ ለመባል ቢያንስ 20 ከመቶ ቤተሰብ የከፋ የምግብ እጥረት ሲያጋጥመው እንዲሁም የአልሚ ምግብ እጥረት (ማልኒዩትሪሽን) እጥረት በ30 ከመቶና ከዚያ በላይ ሲሆን ነው።

የሞት ምጣኔውም ከ10ሺህ ሰዎች በቀን ሁለት እና ከዚያ በላይ ሰዎች የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ሕይወታቸው ሲያልፍ ነው ይላል።

በአንድ አገር የለየለት ረሃብና ቸነፈር መግባት በተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት ላይ የሚጥለው ግዴታ ባይኖርም ፋሚን የሚለው ቃል አገልግሎት ላይ በይፋ ከዋለ የችግሩን ጥልቀትና ስፋት ስለሚያሳይ አባል አገራት ልዩ ትኩረት እንዲሰጡት የሚያስገድድ ሊሆን ይችላል።