የረሃብ ደመና ያንዣበበበት የትግራይ አርሶ አደሮች ክረምት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የ60 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋው አቶ ገብረማርያም በትግራይ ክልል ዓጸላ በተባለች ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ የሰድስት ልጆች አባት ናቸው።
ከዚህ በፊት ሞዴል ገበሬ ተብለው ተመርጠው ተሸልመው ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ትግራይ ውስጥ ባለው ጦርነት ምክንያት ከብቶቻቸውን ጨምሮ ሌላው ጥሪታቸው ተዘርፎብኛል ብለው በመደበኛው የእርሻ ሥራቸው ላይ ሊሰማሩ ቀርቶ የሚላስ የሚቀመስ እንደሌላቸው በምሬት ይናገራሉ።
ዓጸላ በትግራይ ደቡባዊ ዞን በአላጀ ወረዳ የምትገኝ ቀበሌ ስትሆን አብዛኛው የአካባቢው ኅብረተሰብ የሚተዳደረው በእርሻ ሥራ ነው። አቶ ገብረማርያምም ቀደም ሲል በአንድ የእርሻ ወቅት ከ30 እስከ 100 ኩንታል ምርት ያነኙ ነበር።
"የመስኖ ሞተርም ነበረኝ፤ ከሞዴልም ሞዴል ገበሬ ነበርኩኝ። አሁን ግን ለአፍ የሚቀመስ ነገር የለኝም። ምናልባት መንግሥት ማዳበሪያ ከሰጠኝ በማለት ማሳዬን እያለሰለስኩኝ ነው'' በማለት ያስረዳሉ።
በትግራይ ገበሬዎች ታኅሣሥ ወር ላይ ምርት ከሰበሰቡ በኋላ ከጥር ወር ጀምረው ለቀጣዩ የእርሻ ወቅት ማሳቸውን ማዘጋጀት የሚጀምሩበት ነበር።
ዘንድሮ ግን በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በአካባቢው ያሉ የኤርትራ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚልሻዎች የእርሻ ማሳዎችን ምሽግ ስላደረጓቸው አርሶ አደሮች የእርሻ ሥራቸውን ለማካሄድ ችግር እንደገጠማቸው ይናገራሉ አቶ ገብረማርያም።
"የእርሻ ቦታችን ከምንኖርበት አካባቢ እስከ አንድ ኪሎ ሜትር ራቅ ያለ ከሆነ ረፋድ አራት ሰዓት ላይ ማረስ እንጀምርና ከሰዓት 8 ሰዓት ላይ እንመለሳለን'' በማለት ይስረዳሉ።
የእርሻ ሥራቸውን በአግባቡ እንዳያካሂዱ ከመከልከላቸው በተጨማሪ የእንስሳቶቻቸውና ሌሎች ንብረቶቻቸው እንደተወሰደባቸውም ይናገራሉ። ሆኖም ግን ቢቢሲ ይህን ጉዳይ በራሱም ሆነ በሌላ ሦስተኛ አካል በኩል ማረጋገጥ አልቻለም።
የኤርትራና የአማራ ኃይሎች በአካባቢው መኖር አለመኖራቸው በመከታተል የእርሻ ሥራቸውን ለማካሄድ የሚሞክሩ የወረዳው አርሶ አደረች፤ እንደከዚህ ቀደሙ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ባይኖርም ነገሮች ይለወጡ ይሆናል በሚል ተስፋ ሥራቸውን እንደሚከውኑ ይናገራሉ።
"ሴቶች ገበያ መውጣት የሚችሉበት ሁኔታ የለም፤ ወንዶቹም ወደ ገበያ አንሄድም። ሕዝቡ 'ፈጣሪ ያውቃል' ብሎ ነው እርሻውን እያከናወነ ያለው። ቀንና ሌሊቱን መለየት አንችልም ሁሉም ተመሳሳሎብናል" በማለት ያሉበትን ሁኔታ ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባለስልጣናት ግን "የአገሪቱ ሠራዊት ይህንን ተግባር የሚፈጽም አይደለም" በማለት ክሶቹን ሲቃወሙ፤ የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ "የስም የማጥፋት ዘመቻ ነው" ይላል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳር ባለሥልጣን አስተዳደርም [አቶ ኣበበ ገብረሂወት] "የትግራይ ገበሬዎች እንዳያርሱ በኤርትራ ሰራዊት በኩል ጫና እየደረሰባቸው መሆኑን" በመግለጽ፤ የአማራ ሃይሎችም ዘርና ማዳበሪያ ወደ ክልሉ እንዳይገባ እንደሚከልክሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የህወሓት ሃይሎችም ሆን ብለው እዚህም እዚያም ተኩስ በመክፈትና ግጭቱ እንዲራዘም በማድረግ ህዝቡ ተረጋግቶ ኑሮውን እንዳይቀጥል እያደረጉ መሆናቸው የጊዚያዊ አስተዳደሩ ባለስልጣናት ይገልጻሉ።

የፎቶው ባለመብት, TIGHAT
የእርሻ ሥራ በስጋት ውስጥ
በደጉ ጊዜ ከአንድ ሄክታር እስከ 30 ኩንታል ምርት ያገኙ የነበሩት የቦራ ወረዳ ኗሪና የአራት ልጆች አባት አቶ መረሳ ከዚህ በፊት በአንበጣ ወረራ የተቸገረው አርሶ አደር ገና ምርቱን ሳይሰበስብ ውጊያ በመጀመሩ ከባድ ችግር ላይ መውደቁን ይናገራሉ።
"በሬ ያላቸው አንዳንድ አርሶ አደሮች ሰሞኑን ማረስ ጀምረዋል፤ በሬ የሌለው ግን ተቀምጧል። ገበሬው በተጎሳቆለ ኑሮ ላይ ነው ያለው" የሚሉት አቶ መረሳ አካባቢያቸው ከአማራ ክልል ጋር በመዋሰኑ ምክንያት ባለው ስጋት የእርሻ ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንዳልቻሉ ይገልጻሉ።
"ማዳበሪያና ምርጥ ዘር የለም። መሬቱም ቀድሞ እንዲዘጋጅ አልተደረገም። ሰሞኑን እርሻውን የጀመርነው የኤርትራና የአማራ ኃይሎች ከአካባቢያችን ለቀው ወደ አላጀ ስለሄዱ ነው እንጂ እነሱ ሲኑሩማ ማረስ አይቻልም" ይላሉ አቶ መረሳ።
ከዚህ ቀደም ወታደሮች በቦራ ወረዳ እንስሳት አርደው እንደበሉና የተሰበሰበ ጤፍ በመድፋት ከአፈር ጋር እንደደባለቁ ያሚያስታውሱት አርሶ አደሩ፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት 'የሚሊሻ ጠብመንጃ የት ነው ያለው?' በማለት በአካባቢያቸው በርካታ ሰዎችን ገድሏል ይላሉ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ምን ይላል?
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ለቀረቡት ክሶች በሰጡት ምላሽ ሠራዊቱ ግዴታውን አሳምሮ እንደሚያውቅ በመግለጽ የቀረበውን ክስ ወሃ እንደማይቋጥር ሲሉ ገልጸውታል።
"የትግራይ ገበሬ በኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጦርነት ጊዜ በግራም በቀኝም የተኩስ ልውውጥ እየተደረገ ሲያርስ የነበረ ጠንካራ ገበሬ ነው። ወጣቶች በእርሻና ሌሎች ልማቶች ላይ እንዳይሰሩ ወደ ጦርነት እየማገደ ያለው ህወሓት ነው። የኢትዮጵያ ሠራዊት በሕግም በሞራልም ይሄን ሊያደርግ አይችልም" ብለዋል።
የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ እንዲሁም የኤርትራ ሠራዊት በትግራይ አርሶ አደሮች ላይ ፈጸመውታል ስለተባለው ክልከላ፣ ዝርፊያና ግፍ በማስመልከት ሲናገሩም፤ "ክሱ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ጫና ለመፍጠር የሚደረግ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አካል መሆኑን" በማስገንዘብ ሠራዊቱ ከአስተዳደሩና የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር እንደሚሰራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በርካታ አርሶ አደሮች ተገደሉ ስለመባሉ በሰጡት ምላሽ "ይህ ሊታሰብም የማይችል ነገር ነው። ብዙ ክሶች ናቸው የሚቀርቡት። ሠራዊቱ በኢትዮጵያ ሕዝብ ሥነልቦናና ሞራል የተቀረጸ ነው። እናቱንና አባቱን፤ እህቱንና ወንድሙን በፍጹም ሊገድል አይችልም" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, GEREB TSANA
"ማሳችን ውስጥ ፈንጂ ተቀብሯል"
በገለበዳ ገጠሮች፣ ተንቤንና አካባቢዋ፣ ወርዒ፣ በዓዴት ከተሞች፣ በዕዳጋ ዓርቢና አካባቢዋ፣ በፈረስማይ፣ በእንትጮ፣ በነበለት፣ በእምባሰነይቲና በሐውዜን የሚገኙ ገበሬዎች የእርሻ መሬቶቻቸውን እንዳያርሱና እንዳያዘጋጁ መከልከላቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
የኤርትራ ሠራዊት በእርሻ ማሳዎች ላይ ፈንጂዎች እንደቀበሩና በዓድዋ አካባቢ ገሊላ በሚባል ቦታ 'ሳንፈቅድላችሁ አለያም ምርቱን አብረን የማንካፈል ካልሆነ ማረስ አትችሉም' መባላቸውን አቶ ኃይሌ [ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ የተቀየረ] የአካባቢው አርሶ አደር ለቢቢሲ ተናግሯል።
ሆኖም በዚህ ክስ ላይ የሚመለከታቸው የኤርትራ መንግሥት አካላትን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
በትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ የኤርትራ ሠራዊት ፈጸማቸው ስለሚባሉ ግድያዎች፣ ጾታዊ ጥቃቶችና ዝርፊያዎችን በሚመለከት በሚቀርቡ ክሶች ላይ በትዊተር ገጻቸው ምላሽ የሚጽፉት የአገሪቱ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ የማነ ገብረመስቀል ክሶቹን "ስምን የማጠልሸት ዘመቻ ነው" ሲሉ ይገልጿቸዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምን ይላል?
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበበ ገብረሕይወት፤ ገበሬዎች ላይ ተፈጽመዋል የሚባሉ በደሎችን ለመቅረፍ ከአማራ ክልል መንግሥትና ከመከላከያ ሠራዊት ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በተለይም በአማራ በኩል ወደ ትግራይ በሚገባ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ላይ የክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ መንገድ በመዝጋታቸው በአፋር ክልል በኩል እንዲገባ አማራጭ መወሰዱን ያስረዳሉ።
በአማራ በኩል ሲመጡ ከሁለት እስከ ሶስት ቀን እንዲቆሙ ስለሚደረግ ከአዲስ አበባ 1300 ኪሎሜትር በሚርቀው የአፋር መንገድ በኩል ለመጠቀም እንደተገደዱ ነው አቶ አበበ የሚናገሩት።
የኤርትራ ሠራዊት ከአካባቢው እንዲወጣ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን በማስታወስም "የሻዕቢያ ሠራዊት እንዲወጣ እየተሰራ ስለሆነ ገበሬዎች በእርሻ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጥረት እያደረግን ነው። የተወሰነ ለውጥም አለ" ብለዋል።
"ሆን ተብሎ" የሚፈጸም ዘር የመበተንና የእርሻ መሳሪያዎችን ከጥቅም ውጪ የማድረግ ተግባርን ለማስቆምም የመከላከያ ሠራዊት ኃላፊነት ወስዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ባለስልጣኑ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሽምቅ ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን በመጥቀስ ነዋሪዎች ተረጋግተው መደበኛ ሕይወታቸውን እንዳይመሩ ማድረጉን የሚገልጹት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው፤ የህወሓት ኃይሎች በሚከፍቱት ተኩስ ሕዝቡ ተደናግጦ እንደሚሸሽ አስረድተዋል።
"እርሻ እንዳይካሄድና መረጋጋት እንዳይኖር በማድረግ በኩል በተለይም በደቡብ ትግራይ አካባቢ ላለው ችግር ህወሓት ድርሻ አለው። ትግራይ ውስጥ ሰላም እንዳይኖርና ውጊያው እንዲቀጥል ሆን ብለው እየተንቀሳቀሱ ነው። ታዲያ ግጭት ካለ ገበሬው እንዴት የእርሻ ሥራውን ማከናወን ይችላል?" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ጥያቄዎች
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ወደ 12 ለሚደርሱ ወረዳዎች ምርጥ ዘር ማዳረሱን የሚናገሩት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ወደ ሽሬና ማዕከላዊ ትግራይ አካባቢዎች ማዳበሪያ የማድረስ ሥራዎች ተከናውነዋል በማለት ያስረዳሉ።
እንደ ጂአይዜድ፣ ዩኤስኤይድ እና ማረት ያሉ የእርዳታ ድርጅቶች ምርጥ ዘር በማቅረቡ ሥራ ላይ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውንም አስታውሰዋል።
"በተለይም ጂኣይዜድ [የጀርመን ተራድኦ ድርጅት] ምርጥ ዘር ማድረስ የማይቻል ከሆነ ጥሬ ገንዘብ ለማከፋፈል እየተንቀሳቀሰ ነው" ያሉት አቶ አበበ ማዳበሪያውን በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ለማከፋፈል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ዩኤስኤይድ ለትራክተሮች መግዣ የሚሆን 54 ሚልዮን ብር ሲሰጥ፤ ኬር የተባለ የእርዳታ ድርጅትም በማረት (ማኅበረ ረድኤት ትግራይ) በኩል 20 ትራክተሮች እንዲሁም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተጨማሪ 20 ትራክተሮችን ለመግዛት በሂደት ላይ ይገኛሉ።
ረሃብና መፈናቀል በትግራይ
በትግራይ ክልል የተቀሰቀው ግጭት አሁን ከሰባት ወራት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን በዚህም ምክንያት በክልሉ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ መከሰቱን ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የእርዳታ ተቋማት እየገለጹ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካላት በትግራይ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል ስጋታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል። የተለያዩ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፣ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረትም በክልሉ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ ጥሪ በማቅረብ ላይ ናቸው።
በግጭቱ ውስጥ በሁሉም በኩል የተሰለፉ ኃይሎች ሰብአዊ እርዳታዎች ካለምንም ገደብ እንዲቀርቡ እንዲፈቅዱ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለው ግጭት በሺዎች የሚገመቱ ሰዎችን ህይወት እንዳጠፋ ሲገመት፣ ከ 1.7 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ እንዲሁም ከ60 ሺህ በላይ ደግሞ ወደ ሱዳን እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል።
ከ5.2 ሚሊዮን በላይ ማለትም ከ90 በመቶ በላይ የትግራይ ክልል ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው የዓለም ምግብ ፕሮግራም መረጃ ያመለክታል።
የትግራይ አርሶ አደሮች በዚህ የክረምት ወቅት ማረስና መዝራት ካልቻሉ በክልሉ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ችግር ሊከሰት እንደሚችል የሚመለከታቸው አካላት ሲያስጠነቅቁ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።














