"ጠ/ሚሩ እርምጃ ካልወሰዱ በኢትዮጵያ የረሃብ ታሪክን በመድገም ይታወሳሉ" ዩኤስኤይድ

የዩኤስኤይድ እና የአውሮፓ ሕብረት ሎጎ

የፎቶው ባለመብት, USAID/EU

የአሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ትናንት ትግራይ ክልልን በተመለከተ ውይይት ካካሄዱ በኋላ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።

አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት በትግራይ የተጋረጠውን የረሃብ አደጋ ጉዳት ለመቀነስ መተግበር አለባቸው ያሏቸውን አምስት ጥሪዎችን ያቀረቡ ሲሆን የተኩስ አቁም ጥሪ ቀዳሚው ነው።

በትግራይ ውስጥ የሰብዓዊ እርዳታ ለማዳረስ ብሎም የሲቪሎችን ጥቃት ለማስቀረት ተኩስ አቁም ይደረግ ሲል በአራት ባለሥልጣናት ተፈርሞ የወጣው ይህ መግለጫ ጠይቋል።

የዩኤስኤድ አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር፣ የአውሮፓ ሕብረት የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌነርቼክ፣ የአውሮፓ ሕብረት ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይን እና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፕ ቦሬል ናቸው በጋራ መግለጫውን ያወጡት።

የዩኤስኤድ ኃላፊ ሳማንታ ፓወር፤ የኖቤል ተሸላሚው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ይህንን ጥቃት ካላስቆሙ እና የኤርትራን ሠራዊትን ካላስወጡ፤ በኢትዮጵያ የረሃብ ታሪክን በመድገም የሚታወሱ መሪ ይሆናሉ" ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሁለት ቀናት በፊት በሰጠው መግለጫ በትግራይ ክልል 'ረሃብ አለ' መባሉን ማጣጣሉ ይታወሳል።

በትግራይ ክልል በረሃብ ሰዎች እየሞቱ ነው ስለሚለው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሪፖርት ምላሽ የሰጡት የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ፤ በአንዳንድ ሪፖርቶች በኮረም ኦፍላ ወረዳ ሰዎች በረሃብ ሞተዋል ተብሎ የወጣ ሪፖርት እንዳለ ጠቁመው "ሐሰት ነው" ብለዋል።

"መንግሥት በክልሉ ውስጥ ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ እየተጠቀመ ነው" በሚል በመገናኛ ብዙሃንም ሆነ በተለያዩ አካላት የወጡ ሪፖርቶችንም አቶ ምትኩ አጣጥለዋል። በአብዛኛው የትግራይ ክልል እርዳታ ሰጪዎች እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙም አክለዋል።

ከሳምንት በፊት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም በሰጡት መግለጫ፤ በትግራይ ክልል በአንድ ዙር ለ4.5 ሚሊዮን ነዋሪዎች፣ በሁለተኛ እና ሦስተኛ ዙር ደግሞ ለ4.3 ሚሊዮን ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ እንደተቻለ መናገራቸው ይታወሳል።

በክልሉ እየተደረገ ባለው ሰብአዊ እርዳታ በ5.2 ሚሊዮን ብር 166 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብ መከፋፈሉን ጠቅሰው "ረሃብ እንደ ጦርነት መሣሪያ አየዋለ ነው የሚለው ክስ ተቀባይነት የለውም" ሲሉም የዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና የመብት ተሟጋቾችን ክስ ተቃውመውታል።

በመግለጫው ምን ተባለ?

አገራቱ ከውይይታቸው በኋላ ባወጡት በዚህ መግለጫ፤ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት 400 ሺህ ንጹሃን ዜጎች ወደ ረሃብ አፋፍ እና ሞት እየተገፉ ነው የሚል ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

ባለሥልጣናቱ በሁለተኛ ደረጃ ያቀረቡት ጥሪ በጦርነቱ እየተሳተፉ ያሉ አካላት ዓለም አቀፍ የጦርነት ሕጎችን እንዲያከብሩ የሚያሳስብ ነው።

ይህም የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት ማስጠበቅን የሚጨምር ሲሆን "የተኩስ አቁም ተደረገም አልተደረገም ያለ ቅድመ ሁኔታ መተግበር አለበት" ሲል መግለጫው አሳስቧል። የእርዳታ ሰጪ ተቋማት ደኅንነት እንዲጠበቅም ጥሪ ቀርቧል።

ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ መጠን ያለውን የረሃብ አደጋ ለማስቀረት ሁሉም አካላት ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ ለማዳረስ የሚያስችል መንገድ እንዲፈጥሩ ተጠይቀዋል።

ሌላው የቀረበው ጥያቄ ከዚህ ቀደም በተገባው ቃል መሠረት የኤርትራ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ለቆ እንዲወጣ ለሁለቱ አገራት ጥሪ ቀርቧል።

በመግለጫው ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ በትግራይ ክልል የሚያደርገውን የእርዳታ መጠን እንዲሳድግ እና የሰዎችን ሕይወት እንዲያድን ጥሪ ቀርቧል።

የአሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ትናንት ባደረጉት የውይይት መድረክ ላይ "በአሥርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ብሎም ለማስቀረት የሚቻል የሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል የሚያሳዩ መረጃዎች ከትግራይ እየወጡ ነው" ሲሉ የአውሮፓ ሕብረት የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌነርቼክ ተናግረው ነበር።

"ንጹሀንን ለጦርነት አላማ ብሎ ማስራብ ትልቅ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው" ሲሉም አክለዋል።