ምርጫ 2013፡ ፌስቡክ ከኢትዮጵያ ምርጫ ጋር በተያያዘ ዝግጅት አድርጊያለሁ አለ

ወደ ድምጽ መስጫ ሳጥን የምርጫ ካርድ የሚከት መራጭ

የፎቶው ባለመብት, Mustafa Ferhat Beksen

ፌስቡክ በመጪው ሳምንት የሚደረገውን ምርጫ አስቀድሞና ተከትሎ ሰላማዊ አከባቢን ለመፍጠር ጥብቅ የይዘት ቁጥጥር እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

ፌስቡክ በኢትዮጵያ የሚደረገውን ምርጫ አስመልክቶ እየተሠሩ ያሉ ሁኔታዎችን ባወሳበት ጽሑፉ እንዳለው፤ የማኅበራዊ ትስስር መድረኩ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውልና ለጥላቻ ንግግሮች መናኸሪያ እንዳይሆን የሚረዱ ሁሉን አቀፍ ዝግጅቶችን ስለማድረጉ በድረ ገጹ አውስቷል፡፡

ዝግጅቱ በኢትዮጵያ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ምርጫው ቀን ድረስ የሚዘልቅ፣ ብሎም በምርጫው ቀንና ከምርጫው መከናወን ባሻገር ባሉ ቀናት ተፈጻሚ የሚሆኑ አዳዲስ ሁኔታዎችን ይዘረዝራል፡፡

ምን ዝግጅት ተደረገ?

ይህ ዝግጅት በተለይም የጥላቻ ንግግሮች፣ ነውጥ ቀስቃሽ የሆኑ ይዘቶች እና በኅቡዕ የፖለቲካ ቅስቀሳዎች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር ፌስቡክ የሐሰተኛ መረጃን ሥርጭት ለመገደብ፣ የዲጂታል ግንዛቤን ለመጨመር እና የፖለቲካ ቅስቀሳዎች በአሻጥር ሳይሆን ግልጽ በሆነ መልኩ ለማስተላለፍ የሚረዱ ሁኔታዎችን ለማረጋገጥ አንደሚሠራ አስታውቋል፡፡

ፌስቡክ በዚህ ረገድ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ከሰብአዊ መብት ድርጅቶች፣ ከአገር ውስጥ ሲቪል ማኅበረሰብ፣ እና በፌስቡክ የአካባቢው ተጠሪዎች እንዲሁም በፌስቡክ መሥሪያ ቤት የሚገኙ የጉዳዩ አዋቂዎች ጋር ምክክር ማድረጉን ይገልጻል፡፡

የአገሬውን ሁኔታ በቅጡ ለመረዳት በሚልም የፌስቡክ ድርጅት በኢትዮጵያ ከሚኖሩና ከኢትዮጵያዊያን አዋቂዎች በተለይም በሐሰተኛ መረጃ ስርጭት፣ በጥላቻ ንግግርና ተያያዝ ጉዳዮች ጋር ከሚመለከታቸው ጋር መረዳዳት እንዳደረገ አስታውቋል፡፡

ፌስቡክ ለምርጫው ዝግጅት አዲስ ካቋቋማቸው ማዕከላት አንዱ የምርጫ ማዕከል (ኢሌክሽን ኦፕሬሽን ሴንተር) ይገኝበታል፡፡

ፌስቡክ ለመጀመርያ ጊዜ የምርጫ ማዕከል የከፈተው በፈንጆች 2018 በብራዚል እና በአሜሪካ የሚደረጉ ምርጫዎችን መሠረት አድርጎ ነበር፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአገራት የሚደረጉ ጉልህ ፖለቲካ ምርጫዎችን አስቀድሞ ይህን የምርጫ ማዕከል የመክፈት ተግባር ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

ይህ ማዕከል የተለያዩ ባለሞያዎችን የያዘ ሲሆን፤ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሰጪዎችን፣ የዳታ ሳይንስን፣ የፖሊሲንና የሕግን ጉዳዮች አዋቂዎችን እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን ያጣመረ ነው፡፡

ይህም በኢትዮጵያ ድንገት ሊቀሰቀስ የሚችልን በፌስቡክ የሚዛመት ሁሉን አቀፍ አደጋን ወይም የአጠቃቀም ችግርን በአስቸኳይ ለማዳፈንና ምላሽ ለመስጠት የሚረዳ ነው ተብሏል፡፡

የጥላቻ ንግግርን መቆጣጠር

ፌስቡክ በጥላቻ ንግግር ዙርያም ጥብቅ ክትትል ለማድረግ እንደተዘጋጀ አስታውቋል፡፡

ነውጥን ሊቀሰቅሱ የሚችሉ በሰዎች ማንነትና እምነት ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ ንግግሮችን በተመለከተ ጊዜ በፍጥነት በመንቀሳቀስ ከገጾች እንደሚያወርድም አስጠንቅቋል፡፡

ሰዎች የጥላቻ ንግግሮችን በተመለከቱ ጊዜ እንዴት ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸው ለማስተማር በርካታ ስልጠናዎችን መስጠቱን አስታውቋል፡፡

ይህን ግንዛቤ ለመጨመርም በተለያዩ መገናኛ ቡዙኃን ማስታወቂያ ከማስነገር ጀምሮ ከሚመለከታቸው የሲቪል ማኅበርና ሌሎች ጋር በጉዳዩ ዙርያ ስልጠና መስጠቱንም አውስቷል፡፡

የጥላቻ ንግግሮች በሰዎች ሪፖርት ከመደረጋቸው አስቀድሞ መንጥሮ ሊለይ የሚችል የተለያየ ቴክኖሎጂ እየሞከረ እንደሆነ ፌስቡክ አስታውቋል፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ ተገቢ ያልሆኑ ይዘቶችን በራሱ መመንጠር የሚችል ሲሆን ኦሮምኛ እና አማርኛን ጨምሮ በ40 የዓለም ቋንቋዎችም አገልግሎት እየሰጠ ነው ተብሏል፡፡

ፌስቡክ ይህንን ቴክኖሎጂ ይበልጥ ለማገዝና የቁጥጥር ሂደቱን ለማጥበቅ ይዘትን የሚመረምሩ ከ35 ሺህ በላይ ሰዎችን በመላው ዓለም መቅጠሩንና ከነዚህም መሀል የአማርኛ፣ የኦሮምኛ፣ የሶማሊኛና የትግርኛ ተናጋሪዎች እንደሚገኙበት አውስቷል፡፡

ከመጋቢት 2020 እስከ መጋቢት 2021 ብቻ 87 ሺህ የጥላቻ ንግግሮችን በኢትዮጵያ እንዳስወገደ ፌስቡክ አውስቷል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 89 እጅ የሚሆኑት የጥላቻ ንግግሮች ተነቅሰው እንዲወጡ የሆነው በቴክኖሎጂ ድጋፍ ነው፡፡

በጥላቻ ንግግር የተጠመዱ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን አካውንት መዝጋትን ጨምሮ በተደጋጋሚ በዚህ ረገድ የሚጠረጠሩ ተጠቃሚዎች የሚደርሱትን ኅብረተሰብ መጠንና ስፋት በአያሌው ማሳነስ እንደጀመረ ፌስቡክ ገልጿል፡፡

ሐሰተኛ መረጃን መቆጣጠር

ፌስቡክ ከምርጫው ጋር ተያይዞ ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመዋጋት ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉን ገልጾ፤ ምርጫውን ሊያስተጓጉሉ የሚችሉ ይዘቶችን ወይም የአመጽ ጥሪዎችን አልያም ሰዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ የሚያነሳሱ ይዘቶችን በፍጥነት አነሳለሁ ብሏል፡፡

እነዚህን የማያሟሉ ነገር ግን ሐሰተኛ የሆኑ መረጃዎችን ስርጭት ለመግታት ፔሳቼክ እና ኤኤፍፒን ከመሰሉ አጋሮች ጋር እንደሚሠራም ፌስቡክ ተናግሯል፡፡

እነዚህ የመረጃ ማጥለያዎች አንድን ዜና ሐሰተኛ እንደሆነ በተረዱ ጊዜ ይዘቱ የሚደርስበት ርቀት እንደሚገደብ ተነግራል፡፡

ከዚህም ባሻገር ተጠቃሚዎች ጊዜው ያለፈባቸውን ወይም ከሌላ ቦታ የተወሰዱ ምስሎችን በሚጠቀሙ ጊዜ ይህንኑ የሚያሳውቅ ምልክት ለተጠቃሚዎች እንደሚያደርስም ቃል ገብቷል፡፡

አንድ ዓመትና ከዚያ በላይ ያለፋቸውን ፎቶዎች የሚያጋሩ ተጠቃሚዎችም ይህ እንደሚነገራቸው ፌስቡክ አስታውቋል፡፡

ፌስቡክ ጤናማ የፖለቲካ ቅስቀሳዎችና ክርክሮችን እንደሚያበረታታ ገልጾ፤ ነገር ግን በፌስቡክና በኢኒስታግራም ላይ የሚለቀቁ የፖለቲካ ቅስቀሳ ማስታወቂያዎች ግልጽነት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

የፖለቲካ ቅስቀሳን በፌስቡክ ለሚያደርጉ በይፋ ማንነታቸውን እንዲያሳውቁና ይህን ቅስቀሳም እያደረጉ እንደሆነ በግልጽ እንዲጽፉ የሚያስገደዱ ሂደቶች እንዳሉትም አስታውቋል፡፡

ፌስቡክ በኢትዮጵያ የዲጂታል ሚዲያ መሀይምነትን ለማጥፋት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በስፋት እየሠራ እንደሆነና የግንዛቤ ማስጨበጫ ቅስቀሳዎችም እያከናወነ መሆኑን አውስቷል፡፡