የሶማሌ ክልልን ጭምሮ በ54 የምርጫ ክልሎች ሰኔ 14 ምርጫ አይካሄድም ተባለ

የፎቶው ባለመብት, NEBE
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ የሶማሌ ክልልን ጨምሮ በ54 የምርጫ ክልሎች ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ምርጫ እንደማይካሄድ አስታወቀ።
ቦርዱ ከዚህ በተጨማሪም ከ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ጋር በተመሳሳይ ዕለት እንዲካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ለመመሠረት ይደረግ የነበረው ሕዝበ ውሳኔም ወደ ሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መደረጉ ተገልጿል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሶማሌ ክልል ሊደረግ የነበረው ምርጫ እና የደቡብ ምዕራብ ሕዝበ ውሳኔ እንዲተላለፍ የተደረገው በተለያዩ የምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ጉድለቶች መገኘታቸውን ተከትሎ ነው ብሏል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የሶማሌ ክልል እንዲሁም የምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልነት ሕዝበ ውሳኔ ጳጉሜ 1/2013 ዓ.ም. ይካሄዳል ስለማለታቸው የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ምርጫ ቦርድ ትናንት በሰጠው መግለጫ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ የተለያዩ ጉድለቶች መገኘታቸውን አስታውቆ ነበር። ቦርዱ 54 የምርጫ ክልሎች ድምጽ መስጫ ወረቀቶች ድጋሚ ህትመት የሚያስፈልጋቸው ሆነው ተገኝተዋል ብሏል።
ቦርዱ ይህን ችግር ለመቅረፍ ሁለት አማራጮች አሉ ብሎ ነበር ትናንት ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በነበረው ወይይት። የመጀመሪው አማራጭ የድምፅ መስጫ ወረቀቱ ህትመት አገር ውስጥ ማከናወን ሲሆን ሁለተኛው አማራጭ ብሎ ያቀረበው ሃሳብ ደግሞ በ54 የምርጫ ክልሎች በጸጥታ ችግር የተነሳ ሰኔ 14 ቀን ድምጽ ከማይሰጥባቸው የምርጫ ክልሎች ጋር በጋራ ማከናውን ይሆናል ብሎ ነበር።
በዛሬው መግለጫ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ ክፍተት የተገኘባቸው የምርጫ ክልሎች የጸጥታ ችግር አለባቸው ተብለው ሰኔ 14 ድምጽ ከማይሰጥባቸው የምርጫ ክልሎች ጋር ድምጽ ይሰጥባቸዋል ብለዋል።
በዚህም መሠረት ምርጫው በሁለት ዙር እንደሚካሄድ የተወሰነ ሲሆን የመጀመሪያ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሰኔ 14 የሚካሄድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በዓመቱ መጠናቀቂያ ላይ ጳጉሜ 01 ይካሄዳል።
በትናንቱ የምርጫ ቦርድ መግለጫ ላይ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ድጋሚ ህትመት ያስፈልጋቸዋል ተብለው የተለዩት 54ቱ የምርጫ ክልሎች በሚከተሉት ክልሎች የሚገኙ ናቸው።
- ሶማሌ- 14 (የክልል ምክር ቤት)
- አፋር - 6 ምርጫ ክልል (1ዱ የተወካዮች ምክር ቤት)
- አማራ- 11 ምርጫ ክልል (3ቱ የተወካዮች ምክር ቤት)
- ቤኒሻንጉል ጉሙዝ - 2 ምርጫ ክልሎች ( የክልል ምክር ቤት)
- ጋምቤላ - 3 ምርጫ ክልሎች (የክልል ምክር ቤት)
- ኦሮሚያ - 2 ምርጫ ክልል (የክልል ምክር ቤት)
- ደ/ብ/ብ/ህ- 15 ምርጫ ክልሎች (1 ለተወካዮች ምክር ቤት)
- ድሬዳዋ - 1 (የከተማ ምክር ቤት) ድጋሚ ህትመት የሚያስፈልጋቸው ምርጫ ክልሎች ያሏቸው ናቸው።
በዚህ ዓመት የሚካሄደው ምርጫ በመደበኛ የጊዜ ሰሌዳው መካሄድ የነበረበት ባለፈው ዓመት የነበረ ቢሆንም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፉ ይታወቃል።
ምርጫው በዚህ ዓመት በግንቦት ወር ሊካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም አስፈላጊ የምርጫ ቁሳቁሶች በተያዘላቸው ጊዜ ተዘጋጅተው ባለመጠናቀቃቸው በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም እንዲካሄድ ተወስኖ እንደነበር ይታወሳል።












