በአማኑኤል ግድያ ጥፋተኞች እንዲጠየቁ ሂዩማን ራይትስ ዋች ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Social Media
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች በደምቢ ዶሎ ከተማ በአደባባይ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተገድሏል ላለው ወጣት ተጠያቂ የሆኑ የመንግሥት ባለስልጣናት እና የጸጥታ ኃይሎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠየቀ።
የ17 ዓመት ወጣት የነበረው አማኑኤል ወንድሙ ከበደ ግንቦት 3/2013 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ደምቢ ዶሎ ከተማ ሕዝብ በተሰበሰበበት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መገደሉን የመብት ተሟጋቹ ድርጅት አስታወቋል።
በተመሳሳይ በወቅቱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአማኑኤል ወላጅ አባት እና የዓይን እማኞች ወጣቱ በጸጥታ ኃይሎች በአደባባይ መገደሉን አረጋግጠው ነበር።
ሂዩማን ራይትስ ዋች እንዳለው የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ታዳጊውን በአደባባይ ከገደሉት በኋላ የታዳጊውን የቤተሰብ አባላት ጨምሮ ሌሎች ነዋሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን በመግለጫው አስታውቋል።
አማኑኤል እንዴት ተገደለ?
የአካባቢው ባለስልጣናት ወጣቱ ባለስልጣናትን በመግደል የሚታወቀው 'አባ ቶርቤ' የተባለ ቡድን አባል ነው በማለት መገደሉን አረጋግጠው በአደባባይ ግን አልተገደለም ሲሉ አስተባብለዋል።
የአማኑኤል ወንድሙን ግድያ በተመለከተ የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ በክልሉ ሕዝብን እያሸበሩ ነው የሚሏቸው አካላት ላይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ በአፅንኦት ተናግረዋል።
"በከተሞች ሰውን እየገደሉ ሕዝብን ማሸበር የእነሱ የእለት ተእለት ተግባር ነው። እነሱ የሚያደርጉት መግደል ነው። ሰላምን ለማስከበር የሚሄደው ኃይል እነዚህ አካላትን አጋልጦ እርምጃ ወስዶ ሊቆጣጠር ይገባል የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህ የተወሰደው እርምጃ የትኛውም አይነት ይሁን ሕዝብን አሸብሮ፣ አስፈራርቶ እቆጣጠራለሁ በሚል ኃይል ላይ መወሰድ አለበት" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
የደምቢ ዶሎ ከተማ ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት እንዲሁ ሰዎችን ሲገድል በነበረው እና 'የአባ ቶርቤ' ቡድን አባል በሆነው ግለሰብ ላይ እርምጃ ተወሰደ ሲልም በፌስቡክ ገጹ በተንቀሳቃሽ ምስል ጋር አስደግፎ አስፍሮ ነበር።
በዚህ የፌስቡክ ገጽ ላይ ወጣቱ ከመገደሉ በፊት ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጥ እጁ ወደ ኋላ ታስሮ የነበረ ሲሆን አንገቱ ላይ ሽጉጥ ተንጠልጥሎ ይታያል።
በወጣቱ እግር ላይ እና በዙሪያው ደም የሚታይ ሲሆን ልብሱም በጭቃ ተለውሷል። አደባባይ ፊትለፊት የቆመው ወጣት ስሙ አማኑኤል ወንድሙ ከበደ እንደሚባል እና ትውልዱ ደምቢ ዶሎ ከተማ 07 ተብሎ በሚጠራ ስፍራ እንደሆነ ይናገራል።
በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የደንብ ልብስ በለበሱ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎ ተከቦ ይታያል።
'ግድያው ለሰው ልጅ ሕይወት ያለን ቸልተኝነት ያሳያል'
የሂዩማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ሌቲሻ ባደር፤ ""ባለስልጣንት ወጣቱን መግደላቸው ለሰው ልጅ ሕይወት ያለውን ቸልተኝነት ያሳያል" ብለዋል።
የአካከባቢው ባለስልጣናትም ወጣቱን በአደባባይ መግደላቸው እና ቪዲዮ መቅረጻቸው ከሕግ በላይ እንደሆኑ እምነት እንዳላቸው ያሳያል ብለዋል።
ሂዩማን ራይትሰ ዋች የደምቢ ዶሎ ከተማ ነዋሪዎች ወጣቱ ግንቦት 3 ጠዋት 2 ሰዓት አካባቢ በኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት መኖሪያ ቤቱ አቅራቢያ በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ነግረውኛል ብሏል።
ሂዩማን ራይትስ ዋች የዓይን እማኞች እንደነገሩት ከሆነ የልዩ ኃይል አባላቱ ወጣቱን በቁጥጥር ሥር ካዋሉት በኋላ በእርግጫ፣ በዱላ እና በሰደፍ ሲመቱት ነበር።
አማኑኤል ቀበሌ 05 ተብሎ የሚጠራ ቦታ ሲደርሱ ለማምለጥ ሲሞክር የፖሊስ አባላቱ እግሩን በጥይት መትተው እንደያዙት የዓይን እማኞች ለሰብዓዊ መበት ተሟጋቹ ተናግረዋል።
ሂዩማን ራይትስ ዋች፤ አማኑኤል በመንገድ ላይ በመንግሥት የጸጥታ ኃይል አባላት ተከቦ እየሄደ፤ "እኔ የአባ ቶርቤ አባል ነኝ። እኔ ያደረኩትን አታድርጉ። ከእኔ ተማሩ" እያለ ሲናገር የሚያሳይ ምስል ተመልክቻለሁ ብሏል።
የዓይማ እማኞች ባለስልጣናት አማኑኤል ፊቷን እንዲያዞር ከነገሩት በኋላ ቢያንስ ሁለት ጊዜ ሕዝብ በተሰበሰበበት በጥይት መትተው መግደላቸውን ለሂዩማን ራይትስ ዋች ተናግረዋል።
የጸጥታ ኃይሎች አማኑኤልን ገደሉት በኋላ ነዋሪዎች ወደ አስክሬኑ እንዳይጠጉ መከልከላቸውን እና በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የነበሩት የአማኑኤል ወላጆች የልጃቸው አስክሬን ወዳለበት እንደሚመጡ ማድረጋቸውን ሂዩማን ራይትስ ዋች ገልጿል።
የአማኑኤል እናት የልጃቸውን አስክሬን አይተው ማልቀስ ሲጀምሩ በምላሹ የፖሊስ አባላቱ የአማኑኤል እናትና አባትን መደብደባቸውን ከዓይን እማኞች መስማቱን ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Dembi Dolo City Administration Communucation
"የልጄን አስክሬን እጁ ወደ ኋላ እንደታሰረ አየሁት"
አቶ ወንድሙ ከበደ የልጃቸውን መገደል ሳይሰሙ አስክሬኑን አደባባይ ላይ ማየታቸው በእርሳቸው እና በባለቤታቸው ላይ ድንጋጤን እንደፈጠረ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
"የልጄን አስክሬን እጁ ወደ ኋላ እንደታሰረ አየሁት" ብለዋል አቶ ወንድሙ።
የልጃቸው አስክሬን ካለበት አደባባይ ከደረሱ በኋላ የአማኑኤል እናት ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው እንደነበረ ይናገራሉ።
"እሷ እራሷን መቆጣጠር አልቻለችም። ትንከባለላለች፤ ትጮሃለች። በጣም እየጮኃች 'እኔንም ግደሉኝ' ስትል አትረብሹ ብለው ደበደቡን" ይላሉ።
የአማኑኤል አባት የልጃቸውን አስክሬን ለማንሳት ስላልተፈቀደላቸው "ወደ ቤት ተመልሰን ማልቀስ ጀመርን" ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ያስረዳሉ።
ከቆይታ በኋላ የአገር ሽማግሌዎች አስክሬኑን አንስተው ወደ መኖሪያ ቤት ካመጡላቸው በኋላ ቀብር መፈጸሙን ይናገራሉ።
አባ ቶርቤ ማነው?
"አባ ቶርቤ" የኦሮምኛ ቃል ሲሆን ትርጉሙም "ባለ ሳምንት" ማለት ነው። ይህ ቡድን በኦሮሚያ የተለያዩ ስፍራዎች ታጥቆ ከሚንቀሳቀሰው በቅርቡ አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳለው የክልሉ ባለስልጣናት ይናገራሉ።
ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ጅብሪል መሐመድ "አባ ቶርቤ ማለት የአሸባሪው ሸኔ የከተማ ውስጥ ክንፍ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
በከተማ ደግሞ 'አባ ቶርቤ' እና 'ሶንሳ' ተብሎ የሚጠራ ቡድን አለው። እነዚህ ቡድኖች በተቻላቸው መጠን ግድያ በመፈጸም ሽብር ለመፍጠር የሚሞክሩ ናቸው ሲሉም ተናግረው ነበር።













