ይፋ የወጣው በታሊባን አመራሮች መካከል የተፈጠረው ክፍፍል

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የታሊባንን አመራር የበለጠ ያስቀጨነቀው ቢቢሲ ያገኘው የድምጽ ቅጂ ነው።
በ2021 አሜሪካ አፍጋኒስታንን ለቅቃ መውጣቷን ተከትሎ የቀደመው አስተዳደር ከተንኮታኮተ በኋላ ታሊባን መንበረ ሥልጣኑን ተቆጣጥሯል።
ዛሬ ታሊባን የተጋረጠበት አደጋ ከውጪ የመጣ ሳይሆን ከውስጡ የሚነሳ ነው።
ሾልኮ የወጣው ድምጽ "በመንግሥት ውስጥ" እርስ በእርስ ያለ ክፍፍል አገሪቱን የሚያስታድደረውን እስላማዊ ኢሚሬት አደጋ ላይ ጥሎታል ይላል።
በዚህ የድምጽ ቅጂ ላይ የበላይ መሪ የሆኑት ሂባቱላህ አኹንድዛዳ በውስጥ ያለ አለመግባባት ሁሉንም እንደሚያፍረከርካቸው ሲናገሩ ይደመጣል።
"በዚህ ክፍፍል የተነሳ ኢሜሬቱ ተንኮታኩቶ ማብቂያው ይሆናል" ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
በጥር 2025 በደቡባዊ ካንዳሃር ከተማ በሚገኝ ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤት (መድረሳ) ውስጥ ለታሊባን አባላት የተናገሩት ንግግር ለወራት በታሊባን ከፍተኛ አመራሮች መካከል ልዩነት ስለመኖሩ ሲናፈስ የነበረውን ወሬ የበለጠ የሚያቀጣጥል ነበር።
የታሊባን አመራሮች ቢቢሲ በቀጥታ ጥያቄ ባቀረበላቸው ወቅት የክፍፍሉን ወሬ አጣጥለውታል።
ነገር ግን የሚናፈሰው ወሬ የቢቢሲ የአፍጋኒስታን አገልግሎት በጣም ምሥጢራዊ በሆነው ቡድን ላይ አንድ ዓመት የሚፈጅ ምርመራ እንዲጀምር አነሳስቶታል።
አሁን በሥልጣን ላይ ያሉ እንዲሁም የቀድሞ የታሊባን አባላት እንዲሁም ውስጥ አዋቂ ምንጮች፣ ባለሙያዎች እና የቀድሞ ዲፕሎማቶች በአጠቃላይ ከ100 በላይ ቃለመጠይቆችን አድርጓል።
መረጃ የሰጡ በሙሉ ይህ ዘገባ ሊያስከትልባቸው የሚችለውን አደጋ በመስጋታቸው ቢቢሲ ለደኅንነታቸው ሲል ማንነታቸውን ይፋ ላለማድረግ ተስማምቷል።
አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ በታሊባን ቁንጮ ላይ ያሉ ሁለት የተለያዩ ቡድኖችን መለየት ችለናል። እያንዳንዳቸው ለአፍጋኒስታን የሚፎካከሩ ርዕዮችን ያቀርባሉ።
ለአኹንድዛዳ ሙሉ በሙሉ ታማኝ የሆነ እና መቀመጫውን በካንድሃር ያደረገው ቡድን አገሪቱን ወደ ጥብቅ የእስልምና ኢሚሬት ራዕይ እየመራት ነው።
ከዘመናዊው ዓለም ተነጥሎ ለእሱ ታማኝ የሆኑ የሃይማኖት አባቶች የሕብረተሰቡን እያንዳንዱን ገጽታ የሚቆጣጠሩበትን መንገድን ይመራል።
ሁለተኛው ደግሞ በዋና ከተማዋ ካቡል የሚገኙት ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው የታሊባን አባላትን ያቀፈ ነው።
ይህ ቡድንም የእስልምናን ጥብቅ ሥርዓት የሚከተል ቢሆንም፣ ከውጭው ዓለም ጋር የሚገናኝ፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚገነባ፣ ልጃገረዶች እና ሴቶች ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባሻገር በአሁኑ ጊዜ የተከለከሉትን ትምህርት እንዲያገኙ የሚታገል ነው።

የፎቶው ባለመብት, Javid Ashna / Middle East Images / AFP via Getty Images
ይህንን አንድ የውስጥ አዋቂ "የካቡሉ ቡድን ከካንድሃሩ ጋር ያለው ፉክክር" ሲል ገልጾታል።
ነገር ግን ጥያቄው የታሊባን ሚኒስትሮችን፣ ታጣቂዎችን እና በሺዎች የሚቆጠሩ የታሊባን ታማኝ ደጋፊዎች የሚደግፉት ተደማጭነት ያላቸው የሃይማኖት ምሁራን ያቀፈው የካቡሉ ቡድን፣ ተጽዕኖው እየጨመረ የመጣውን የአኹንድዛዳን ቡድን ትርጉም ባለው መንገድ ይፈታተነዋል ወይ የሚለው ነው።
ከሁሉም በላይ እንደ ታሊባን አባባል አኹንድዛዳ የቡድኑ ፍጹም ገዥ፣ ለአላህ ብቻ ተጠያቂ የሆኑ እና ሊገዳደሩት የማይገባ ነው።
በዚህ ወቅት ነው በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ኃያላን ቡድኖች መካከል የፍላጎት ግጭት እንዲከሰት የሚያደርግ ውሳኔ የተሰማው።
በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ሂባቱላህ አኹንድዛዳ ኢንተርኔት እና ስልኮች እንዲዘጉ አዘዙ፤ ይህ ትዕዛዝ አፍጋኒስታንን ከሌላው ዓለም ነጠላት።
ከሦስት ቀናት በኋላ ኢንተርኔት ቢመለስም ስለተቋረጠበት ምክንያቱ ምንም ማብራሪያ አልተሰጠም።
ውስጥ አዋቂዎች ግን ከመጋረጃው በስተጀርባ የተከሰተው መሬት አንቀጥቅጥ ነበር ይላሉ። የካቡሉ ቡድን የአኹንድዛዳን ትዕዛዝ በመቃወም ኢንተርኔትን መልሶ አብርቷል።
"ታሊባን እንደሌሎች የአፍጋኒስታን ፓርቲዎች ወይም አንጃዎች ሁሉ፣ ያለው አንድነት የሚደነቅ ነው። ምንም ዓይነት መከፋፈል፣ ብዙ ተቃውሞ አልገጠመውም" ሲሉ በአፍጋኒስታን ዙሪያ ለረዥም ጊዜ የተመራመሩት ባለሙያ ያብራራሉ።
"በንቅናቄው ስሪት ውስጥ የተለመደው ለበላይ አለቆች እና በመጨረሻም ለአሚር [አኹንድዛዳ] የመታዘዝ መርኅ ነው። ትዕዛዞቹን በመቃወም ኢንተርኔትን መልሶ ማብራት በጣም ያልተጠበቀ እና በጣም አስደናቂ የሆነው ለዚህ ነው" ሲሉ ተመራማሪው ተናግረዋል።
አንድ የታሊባን የውስጥ አዋቂ ሁኔታውን 'ከአመፅ ያልተናነሰ ነበር' ሲል ገልጾታል።
የእምነት ሰው
ሂባቱላህ አኹንድዛዳ ሥልጣናቸውን የጀመሩት በዚህ መልክ አልነበረም።
በእርግጥም ምንጮች እንደሚሉት እአአ በ2016 የታሊባን የበላይ መሪ ሆነው መመረጣቸው በከፊል የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ባደረጉት ጥረት የተነሳ ነው።
የጦር ሜዳ ልምድ ስለሌላቸው፣ እጅግ በሚፈራው ወታደራዊ አዛዥ በሲራጁዲን ሃቃኒ ሥር እንድ ምክትል ሆኖ በመሥራት ጀመሩ።
በወቅቱ በአሜሪካ በጣም ከሚፈለጉ ሰዎች አንዱ የነበሩ ሲሆን ያሉበትን ለጠቆመ 10 ሚሊዮን ዶላር የመያዣ ገንዘብም ተተምኖባቸው ነበር።
ሁለተኛው ምክትል የታሊባን መሥራች ሙላህ ኦማር ልጅ የሆነው ያቁብ ሙጃሂድ ሆኖ ተሾሟል። ወጣት ቢሆንም የታሊባን የዘር ሐረግ እና ንቅናቄውን አንድ የማድረግ አቅም ነበረው።
ወደ ሥልጣን የመጣው በታሊባን ተዋጊዎች እና በአሜሪካ በሚመራው ኃይል መካከል ለ20 ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም በኳታር ድርድር እየተደረገ ባለበት ወቅት ነው።
በመጨረሻም በ2020 የተደረሰው ስምምነት አገሪቱ በታሊባን እጅ በድንገት እንድትወድቅ እና በነሐሴ 2021 የአሜሪካ ወታደሮች በትርምስ ለቅቀው እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል።
ለውጭው ዓለም ሁሉም አንድ ግንባር ነበሩ።
ነገር ግን ሁለቱም ምክትል ባለሥልጣናት ታሊባን በነሐሴ 2021 ወደ ሥልጣን እንደተመለሰ ወዲያውኑ ወደ ሚኒስትርነት ዝቅ እንዲሉ ተደርገው ነበር።
አሁን አኹንድዛዳ ብቸኛ የሥልጣን ማዕከል እንደሆኑ ውስጥ አዋቂዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከአሜሪካ ጋር ድርድርን የመሩት እና ተደማጭነት ያላቸው የታሊባን ተባባሪ መሥራች የሆኑት አብዱል ጋኒ ባራዳር እንኳን ብዙዎች እንደጠበቁት ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ይልቅ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ተሹመዋል።
በምትኩ አኹንድዛዳ የታሊባን ደጋፊዎች መቀመጫ የሆነችውን ካንዳሃር በመምረጥ ለርዕዮተ ዓለማቸው ታማኝ በሆኑ እና በጠንካራ አክራሪዎች መከበብ ጀመሩ።
ሌሎች ታማኝ ሰዎቻቸውም የአገሪቱን የፀጥታ ኃይል፣ የሃይማኖት ፖሊሲዎችን እና የኢኮኖሚውን ክፍሎች እንዲቆጣጠሩ ተደረጉ።
"[አኹንድዛዳ] ከመጀመሪያው ጀምሮ የራሱን ጠንካራ ቡድን ለመመሥረት ፈልጎ ነበር" ሲል የቀድሞ የታሊባን አባል እና በኋላ ላይ በአፍጋኒስታን የአሜሪካ ድጋፍ በነበረው መንግሥት ውስጥ ያገለገለ ግለሰብ ለቢቢሲ ተናግሯል።
"መጀመሪያ ላይ ዕድሉን ቢያጣም፣ መንበሩን ከተቆጣጣረ በኋላ ያለውን ሥልጣን እና ኃላፊነት በመጠቀም ተጽዕኖውን ለማስፋት በብልሃት ተንቀሳቅሷል።"

አዋጆች በካቡል ከሚገኙት የታሊባን ሚኒስትሮች ጋር ምክክር ሳይደረግ መውጣት የጀመሩት ከዚህ በኋላ ነው።
ሥልጣን ከመያዛቸው በፊትም ለሕዝቡ የገቡትን ቃል ቸል አሉ። ከእነዚህም መካከል ሴት ልጆች ትምህርት እንዲያገኙ መፍቀድ አንዱ ነበር።
በትምህርት እንዲሁም ሴቶች እንዳይሠሩ የተጣለው ዕገዳ በሁለቱ ቡድኖች መካከል "ዋና የውጥረት ምንጭ" ሆኖ ቀጥሏል። ይህንንም በታኅሣሥ ወር የተባበሩት መንግሥታት የክትትል አካል የሆነው ለፀጥታው ምክር ቤት በደብዳቤ አሳውቋል።
በ1990ዎቹ በታሊባን የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ውስጥ ዳኛ ሆኖ የሠራ ሌላ ውስጥ አዋቂ አኹንድዛዳ በሃይማኖታዊ አቋሙ "የበለጠ ግትር" እየሆነ መጥቷል ይላል።
አኹድዛዳ ልጁ አጥፍቶ ጠፊ ሲሆን ያውቅ የነበረ ብቻ ሳይሆን ማፅደቁንም እአአ በ2017 ከሞተ በኋላ ሁለት የታሊባን ባለሥልጣናት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
እነዚህ ግለሰቦች ለቢቢሲ 'የተሳሳተ ውሳኔ መወሰን ከሕይወቱ በላይ አንድምታ ሊኖረው እንደሚችል እርግጠኛ ነው' ሲሉ አብራርተዋል።
አሁን በታሊባን መንግሥት ውስጥ ሥልጣን ላይ ያሉ ግለሰብ ደግሞ "የሚወስነው እያንዳንዱ ውሳኔ 'እኔ በፍርድ ቀን በአላህ ዘንድ ተጠያቂ ነኝ፣ ለምን እርምጃ እንዳልወሰድኩ እጠየቃለሁ" የሚል መሆኑን ያስረዳሉ።
ከሂባቱላህ አኹንድዛዳ ጋር ስብሰባ ላይ የነበሩ ሁለት ሰዎች ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ጥቂት የሚናገር በአብዛኛው በአካል እንቅስቃሴ ብቻ መግባባት የሚመርጥ እና በክፍሉ ውስጥ ባሉ አንጋፋ የሃይማኖት አባቶች ቡድን አማካኝነት በማስተርጎም መግባባታቸውን ገልጸዋል።
ሌሎች የዐይን እማኞች ደግሞ በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ፊቱን ማሳየት እንደማይፈልግ ተናግረዋል። ዐይኖቹን በለበሰው ሻርፕ ሸፍኖ፣ እና ብዙ ጊዜ ለተመልካቾች ንግግር ሲያደርግ በሰያፍ እንደሚቆም ያስረዳሉ።
አኹንድዛዳን ፎቶግራፍ ማንሳት ወይም ቪድዮ መቅረጽ የተከለከለ ነው። ሁለት ፎቶዎች ብቻ እንዳሉት ይታወቃል።
ከእርሱ ጋር ለመሰብሰብ በጣም አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል።
ሌላ የታሊባን አባል ለቢቢሲ ከዚህ ቀደም አኹንድዛዳ "መደበኛ ምክክር" ያደርግ እንደነበር ጠቅሶ፣ አሁን ግን "አብዛኞቹ የታሊባን ሚኒስትሮች [ከእርሱ ጋር ለመሰብሰብ] ለቀናት ወይም ለሳምንታት ይጠብቃሉ" ብሏል።
ሌላ ምንጭ እንዲሁ በካቡል የሚገኙት ሚኒስትሮች "ይፋዊ ግብዣ ከደረሳቸው ብቻ ወደ ካንዳሃር እንዲጓዙ ተነግሯቸዋል።"
በተመሳሳይ ጊዜ አኹንድዛዳ ቁልፍ የሆኑ ክፍሎችን ወደ ካንዳሃር አዛውረዋል።
ይህም ቀደም ሲል በቀድሞ ምክትሎቹ ሃቃኒ እና ያቁብ ቁጥጥር ሥር የነበሩትን የጦር መሣሪያዎችን ሥርጭትን ያካተተ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት የክትትል ቡድን በታኅሣሥ ወር በጻፈው ደብዳቤ አኹንድዛዳ "ሥልጣን መጠቅለሉ በካንዳሃር ቀጥተኛ ቁጥጥር ስር የሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች ማደራጀትን ያካትታል" ብሏል።
ዘገባዎች እንደሚያሳዩት አኹንድዛዳ ካቡል ያሉትን ሚኒስትሮች በማለፍ ለአካባቢ ፖሊሶች ቀጥተኛ ትዕዛዞችን ይሰጣሉ።
አንድ ተንታኝ "እውነተኛ ሥልጣን ወደ ካንዳሃር ዞሯል" በማለት ይከራከራሉ። የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ ግን ለቢቢሲ ይህንን አስተባብለዋል።
"ሁሉም ሚኒስትሮች በሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ማዕቀፍ ውስጥ የራሳቸው ሥልጣን አላቸው፤ በዚህም መሠረት የዕለት ሥራዎችን ያከናውናሉ፤ ውሳኔዎችን ይወስናሉ። የሚገባቸው ኃላፊነት ለእነሱ የተሰጠ ሲሆን ተግባራቸውንም በዚያው መሠረት ያከናውናሉ" ብለዋል።
ይሁን እንጂ "ከሸሪዓ ሕግ አንፃር፣ እሱ [አኹንድዛዳ] ፍጹም ኃይል አለው" ሲሉ ሙጃሂድ ተናግረዋል፤ አክለውም "ፈጣሪ የከለከለውን ክፍፍል ለማስወገድ፣ ውሳኔዎቹ የመጨረሻ ናቸው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, AP
'ከሌላ ዓለም ላለመነጠል' የሚሠሩት የታሊባን ሰዎች
በካቡል ቡድን መካከል ቅሬታው እየጨመረ እና ጥምረቶች እየተጠናከሩ ነበር።
"እነሱ [የካቡል ቡድን] ቀሪውን ዓለምን ያዩ ሰዎች ናቸው" ሲሉ አንድ ተንታኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል። "ስለዚህ፣ መንግሥታቸው አሁን ባለው መልኩ ሊቆይ እንደማይችል ያምናሉ።"
የካቡል ቡድን የባሕረ ሰላጤውን መንግሥት አርዓያ በማድረግ የምትሄድ አፍጋኒስታንን ማየት ይፈልጋል።
በካንዳሃር የተከማቸው ሥልጣን፣ የሕጎች አፈጻጸም፣ ታሊባን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና ከሴቶች ትምህርት እና ሥራ ጋር እንዴት መጓዝ እንዳለባቸው ያሳስባቸዋል።
የአፍጋኒስታን ሴቶች ተጨማሪ መብቶች እንዲኖራቸው የሚሟገተው የካቡል ቡድን፣ የታሊባን መሥራች በሆነው በባርዳር የሚመራ ሲሆን "ተራማጅ" ተደርጎ ይቆጠራል።
በ2024 የአሜሪካ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዘመቻ ክርክር ወቅት ዶናልድ ትራምፕ "የታሊባን ራስ" ብለው የጠሩት "አብዱል" እርሱ እንደሆነ ይታሰባል።
ከአሜሪካ ጋር በነበረው ድርድር የቡድኑ ዋነኛ ተደራዳሪ እንደነበር ይታመናል።
የካቡል ቡድን ያሳየው የለውጥ አቋም ግን በብዙዎች ዕይታ ውስጥ ሳይገባ አልቀረም።
"እነሱ [በካቡል የሚገኙት የታሊባን መሪዎች] ቴሌቪዥኖችን ይሰባብሩ እንደነበር እናስታውሳለን፤ አሁን ግን ራሳቸው በቴሌቪዥን ይታያሉ" ሲሉ አንድ ተንታኝ ተናግረዋል።
የማኅበራዊ ሚዲያን አቅምንም ይገነዘባሉ።
የቀድሞው ምክትል ያቁብ፣ ሙዚቃ እና ቴሌቪዥን በታገደበት ወቅት አባቱ የታሊባን ባለሥልጣን ነበር።
ያቁብ በወጣት የታሊባን አባላት እና በአንዳንድ አፍጋኒስታናውያን ዘንድ ተወዳጅነትን እያገኘ ሲሆን፣ በቲኮቶክ ስለ እርሱ ቪዲዮዎች ይሠራሉ ምሥሉም በተለያዩ ቁሳቁሶች ላይ ታትሞ ይገኛል።
ነገር ግን ከቀድሞ ምክትል ባልደረባው ሲራጁዲን ሃቃኒ የበለጠ ውጤታማ በሆነ መልኩ ራሱን የለወጠ ማንም የለም።
እርሱ የሚመራው ቡድን እአአ በ2017 በጀርመን ኤምባሲ አቅራቢያ ከ90 በላይ ሰላማዊ ሰዎችን የገደለውን ጥቃት ያቀነባበረ ነው።
እርሱን ከመያዝ ያመለጠበት መንገድ በደጋፊዎቹ ዘንድ እንደ ምትሃተኛ እንዲታይ አድርጎታል።
በዚህ ጊዜ ውስጥ በቢቢሲ የአፍጋኒስታን ጋዜጠኛ የተነሳ አንድ ፎቶግራፉ ብቻ ተገኝቷል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ነገር ግን አሜሪካ አፍጋኒስታንን ለቅቃ ከወጣች ከስድስት ወራት በኋላ፣ ሃቃኒ በካቡል በተካሄደው የፖሊስ መኮንኖች የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ፊቱ ሳይሸፈን በካሜራዎች ፊት ታየ።
ይህ እርሱን ወደ አዲስ መንገድ የሚወስድ የመጀመሪያው እርምጃ ነበር።
ከእንግዲህ ወታደር ሳይሆን ፖለቲካኛ ነው።
ኒው ዮርክ ታይምስ በ2024 ቃለ መጠይቅ ሲያደርግለት የአፍጋኒስታን የለውጥ ተስፋ ነህ? ሲል ጠይቆት ነበር።
ከጥቂት ወራት በኋላ ኤፍቢአይ ምንም ድምጽ ሳያሰማ አውጥቶበት የነበረውን የ10 ሚሊዮን ዶላር መያዣ ትቶታል።
ሆኖም ተንታኞች እና የውስጥ አዋቂዎች ለቢቢሲ በተደጋጋሚ እንደተናገሩት በየበላይ መሪው አኹንድዛዳ ላይ በግልጽ ማመጽ የማይታሰብ ነው።
የበላይ መሪው የሚያወጧቸውን አዋጆች መቃወም የተጀመረው ቀስ በቀስ ነው።
ለምሳሌ የካቡል ቡድንንን የሚደግፉ ባለሥልጣናት በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ጢምን መላጨት የሚከለክለው ሕግ እንዳይፈጸም ማድረግ አንዱ ነው። ነገር ግን ትላልቅ የአመፅ ድርጊቶች ሁልጊዜ የማይታሰቡ ናቸው።
አንድ የቀድሞ የታሊባን አባል ለቢቢሲ "ለአኹንድዛዳ መታዘዝ ግዴታ እንደሆነ ይቆጠራል" ሲል አጽንኦት ሰጥቷል።
ሃቃኒ ራሱ ከኒውዮርክ ታይምስ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፣ በታሊባን መካከል የሚኖር የመከፋፈል አደጋን አቅልሎ አሳይቷል። "በአሁኑ ጊዜ ለአፍጋኒስታን አንድነት አስፈላጊ ነው፤ ያኔ ነው ሰላማዊ አገር የሚኖረን" ነበር ያለው።
በምትኩ አንድ ተንታኝ የካቡል ቡድን "ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም እንዲሁም ለአፍጋኒስታን ነዋሪዎች" መልዕክቶችን ማስተላለፍ እየሞከረ ነው ይላሉ።
አንደኛው "ስለ ቅሬታዎቻችሁ እና ስጋቶቻችሁ እናውቃለን፤ ግን ምን ማድረግ እንችላለን?" የሚል ነው።
ቢያንስ ኢንተርኔትን እንዲዘጋ ትዕዛዙ ከመሰጠቱ በፊት የነበረው ሁኔታ ይህ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, AP
የልዩነት ነጥብ
የታሊባን የበላይ መሪ በኢንተርኔት ላይ ከፍተኛ እምነት የሌላቸው ሰው ናቸው።
ይዘቱ ከእስልምና ትምህርቶች ጋር የሚቃረን ነው ብለው ያምናሉ። እና በዚህ እምነታቸው ፀንተው አንድ ረዳታቸው በየማለዳው አዳዲስ ዜናዎችን ወይም የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎችን እንደሚያነቡላቸው ቃል አቀባያቸው ለቢቢሲ አስረድተዋል።
የካቡል ቡድን አባላት በተቃራኒው ዘመናዊ አገር ያለኢንተርኔት መኖር እንደማይችል ያምናሉ።
የበላይ መሪው የኢንተርኔት መዘጋት ትዕዛዝ በመላው አገሪቱ ከመስፋፋቱ በፊት የተጀመረው በአኹንድዛዳ አጋሮች ቁጥጥር ስር ባሉ ግዛቶች ነው።
የካቡል ቡድን እና ለታሊባን መንግሥት ቅርበት ያላቸው ምንጮች ቀጥሎ የተከሰተውን ነገር ገልጸዋል።
እንደነርሱ አባባል ይህም በታሊባን ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ጊዜ ነው።
"ብዙ የንቅናቄው አባላትን አስገርሟል" ሲሉ አንድ ምንጭ ተናግረዋል።
በአጭሩ የካቡል ቡድን ሚኒስትሮች አንድ ላይ ተሰባስበው በካቡል የሚገኙትን ጠቅላይ ሚኒስትር ሙላህ ሀሰን አኹንድዛዳ ኢንተርኔቱን እንዲከፍቱ አሳምነዋቸዋል።
እንደ እውነቱ ከሆነ ቡድኑ በመላ አገሪቱ ኢንተርኔት ከመቋረጡ በፊት በአዋጁ አለመደሰቱን አስቀድሞ ገልጿል።
የቡድኑ ገለልተኛ መሪ ባራዳር ወደ ካንዳሃር ተጉዘው ከአኹንድዛዳ በጣም ታማኝ ባለሥልጣናት "አንቁት እንጂ" በማለት ማስጠንቀቁን እና የበላይ መሪው "ታማኝ አገልጋይ" ብቻ መሆን ማቆም እንዳለባቸው መግለጻቸውን ይናገራሉ።
"እውነቱን በግልጽ አትነግሩትም፤ የሚናገረውን ሁሉ ተግባራዊ ታደርጋላችሁ" ማለቱን የካንዳሃር የውስጥ አዋቂ ገልጿል።
ምንጩ አክለውም ከዚህ በኋላ ትዕዛዙ ውድቅ ተደርጓል ብለዋል።
ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ አንዲቋረጥ የበላይ መሪው ወደ ቴሌኮሙኒኬሽን ሚኒስቴር ትዕዛዝ አስተላለፉ። ለሚኒስትሩ ቅርብ የሆኑ ምንጭ ላለመታዘዝ "ምንም ሰበብ አልነበረም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ረቡዕ ጠዋት ባራዳር፣ ሃቃኒ እና ያቁብን ጨምሮ የካቡል የሚኒስትሮች ቡድን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ተሰብስበው የቴሌኮምዩኒኬሽን ሚኒስትሩን ጠሩ።
እዚህ ላይ የካንዳሃር ቡድን ደጋፊ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃላፊነቱን እንዲወስዱ እና ትዕዛዙን እንዲሽሩ ወተወቱ። አንድ ምንጭ እንደገለጹት ሙሉ ኃላፊነቱ እነሱ እንደሚወስዱ ነግረዋቸው አሳምነዋቸዋል ብለዋል።
ይህ ማግባቢያ እና ተማጽኖ ሠርቷል። ኢንተርኔቱ ከተቋረጠ በኋላ ዳግም እንዲከፈት ተደርጓል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ አኹንድዛዳ ከወራት በፊት የተናገሩት የውስጥ አካላት የታሊባንን አንድነት እየተፈታተኑት መሆኑ ታይቷል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ግን ይህ ትዕዛዝ ለምን? አንድ ተንታኝ እንደገለጹት የታሊባን አባላት እንደ ሴት ልጆች ትምህርት ባሉ ድንጋጌዎች ባይስማሙም አኹንድዛዳን ለመከተል ደስተኛ ነበሩ።
ከዚህ በፊት ግን የበላይ መሪውን ግልጽ ተከራክረው የነበሩት ብዙዎቹ ዋጋ ከፍለዋል።
የካቲት 2025፣ በወቅቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ግለሰብ "በ20 ሚሊዮን ሰዎች ላይ ኢፍትሃዊ ድርጊት በመፈጸም ከእግዚአብሔር መንገድ" እየራቁ መሆኑን በይፋ ካስጠነቀቁ በኋላ አገሪቱን ለቀው ተሰድደዋል።
ይህም ንግግራቸው የሴቶችን የትምህርት እገዳ የሚመለከት ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት በሐምሌ እና መስከረም 2025 ላይ የበላይ መሪው አኹንድዛዳ የሴቶችን ትምህርት በተመለከተ ያወጧቸውን ድንጋጌዎች በሚመለከት ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ ቢያንስ ሁለት ሌሎች ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል።
ምንም እንኳ ሃቃኒ አኹንድዛዳ ሥልጣን ጠቅልለው ይዘዋል ብለው ትችት ቢያቀርቡም እርሳቸውን እና መሰሎቻቸውን በቅርብ ለማቆየት የበላይ መሪው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃም አለ።
ቢሆንም ትዕዛዝን በቁርጠኝነት ችላ ማለት እንደ ደፋር እርምጃ ሊታይ ይችላል። አንድ ባለሙያ እንዳስቀመጡት በዚህ ጊዜ አደጋውን መጋፈጥ ተገቢ ይሆናል።
ኢንተርኔት እንደገና ከተከፈተ በኋላ፣ ቀጥሎ ምን እንደሚሆን የተለያዩ መላምቶች ይሰጡ ነበር።
የካቡል ቡድን ቅርበት ያለው ምንጭ ሚኒስትሮቹ ቀስ በቀስ ከሥልጣን እንደሚነሱ ወይም ከደረጃቸው እንደሚወርዱ ጠቁሟል።
ይሁን እንጂ የካንዳሃር የውስጥ አዋቂ የበላይ መሪው "እንዲህ ዓይነት ተቃውሞ ስለሚፈሩ" ጉዳዩን ችላ ያሉ የመሰሉት ራሳቸው ሊሆኑ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ዓመቱ ሊጠናቀቅ ሲል ምንም ነገር እንዳልተለወጠ በይፋ ታየ።
ለተባበሩት መንግሥታት የጸፀታው ምክር ቤት የተላከው ደብዳቤ የድርጅቱ አባል አገራት "በካንዳሃር እና በካቡል መሪዎች መካከል ያለውን ልዩነት ከቤተሰብ አለመግባባት ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ዝቅ አድርገውታል" ሲል ተችቷል።
አክሎም "ይህም ሁኔታውን የማይለውጠው እና ሁሉም ከፍተኛ የታሊባን መሪዎች ለድርጅት ስኬት የሚታትሩ አድርገው ያያሉ" ሲል ገልጿል።
የታሊባን መንግሥት ከፍተኛ ቃል አቀባይ የሆኑት ዛቢላህ ሙጃሂድ ምንም ዓይነት ክፍፍል እንዳልተፈጠረ በግልጽ አስተባብለዋል።
"በፍፁም እንድንከፋፈል አንፈቅድም" ሲሉ በጥር 2026 መጀመሪያ ላይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ሁሉም ባለሥልጣናት እና አመራሮች መከፋፈል በአላህ የተከለከለ መሆኑን ያውቃሉ።"
ይሁን እንጂ፣ በታሊባን አባላት መካከል የ"አመለካከት" ልዩነቶች እንዳሉ አምነዋል። ነገር ግን "በቤተሰብ ውስጥ የአመለካከት ልዩነት ሊኖር ይችላል" በማለት አነጻጽረውታል።
በታኅሣሥ ወር አጋማሽ ላይ እነዚያ "ልዩነቶች" ዳግም ብቅ አሉ።
ሃቃኒ በትውልድ አገሩ በኮስት ግዛት ውስጥ ለአርብ ጸሎት ለተሰበሰቡ ሰዎች ንግግር ሲያደርግ "በአገሪቱ ሕዝብ ታማኝነት፣ ፍቅር እና እምነት ሥልጣን አግኝቶ ወገኑን የሚተው ወይም የሚረሳ ማንኛውም ሰው...መንግሥት አይደለም" ሲል አስጠንቅቋል።
በዚያው ቀን የአኹንድዛዳ ታማኝ የሆኑት የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ኔዳ መሐመድ ናዲም በአጎራባች ግዛት ውስጥ በሚገኝ መድራሳ ውስጥ ለተመረቁ ተማሪዎች ንግግር አድርገዋል።
"አንድ ሰው ሲመራ የተቀረው ደግሞ ትዕዛዝን ይከተላል፤ ይህ እውነተኛ የእስልምና መንግሥት ነው" ብለዋል።
"ብዙ መሪዎች ካሉ ችግሮች ይፈጠራሉ፤ ያለንም መንግሥት ይከስማል" ብለዋል።















