ዩናይትድ አረብ ኤሜሬቶች እና ሶማሊያን ያጋጫቸው ምንድነው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል ለራስ ገዟ ሶማሊላንድ የሰጠችውን የሀገርነት እውቅና ተከትሎ ሶማሊያ ላለፉት ሳምንታት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ ለማግኘት ስትጥር ቆይታለች።
የሶማሊያ መንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቱን ተከትሎ ከበርካታ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ድጋፍ ቢያገኝም ከአንዲት ሀገር ጋር ያለው ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ሻክሯል።
የሶማሊያ እና የሞቃዲሾ አስተዳደር የረዥም ጊዜ አጋር የሆኑት ዩናይትድ አረብ ኤሜሬቶች (ዩኤኢ) የለየት ቁርሾ ውስጥ ገብተዋል።
በነዳጅ የበለፀገችው የባሕረ-ሰላጤው ሀገር በሶማሊያ ፀጥታ፣ ምጣኔ ሀብት እና ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ሚና እንዳላት ይታወቃል።
በኤደን ባሕረ-ሰላጤ እና በሕንድ ውቅያኖስ 3 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚረዝም የባሕር ጠረፍ ያላት ሶማሊያ፤ በባሕር ላይ ወንበዴዎች እና በሕገ-ወጥ መሣሪያ ዝውውር ምክንያት በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚፈጠር አለመረጋጋት ምክንያት እንደሆነች ይነገራል።
ኤምሬቶች ከሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት እና ከክልል መንግሥታት ጋር ባላት ስምምነት መሠረት በቦሳሶ፣ በኪስማዮ እና በበርበራ ወደቦች የልማት ሥራዎች ስታከናውን ቆይታለች።
ነገር ግን ባለፈው ሰኞ የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ከዩኤኢ ጋር የገባውን የወደብ ማልማት እና የፀጥታ ስምምነት ሙሉ በሙሉ መሰረዙን አስታውቋል። ሶማሊያ ይህን ያደረገችው ዩኤኢ ልዑላዊነቴን ጥሳለች በሚል ነው።
"ከዩኤኢ ጋር መልካም ግንኙነት ነበረን። ነገር ግን አለመታደል ሆኖ እንደ ነፃ እና ሉዓላዊ ሀገር ሊያዩን አልቻሉም። ሁኔታውን በፅኑ ካጤንነው በኋላ እዚህ ውሳኔ ላይ ደርሰናል" ሲሉ የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሼክ ሞሐሙድ በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው አቋማቸውን ገልፀዋል።
ዩኤኢ የሶማሊያን ውሳኔ በተለመከተ እስካሁን የሰጠችው አስተያየት የለም።
በዓለም አቀፉ ክራይሲስ ግሩፕ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ኦማር ማህሙድ እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው እውቅና ለዚህ ውሳኔ መሠረት ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ሶማሊያ ይህን ዕውቅና የግዛት አንድነቷን የሚሸረሽር አድርጋ ነው የምትቆጥረው። ዩኤኢ ከጀርባ ትልቅ ሚና ተጫውታለች ብላም ታስባለች" ይላሉ ማህሙድ።
ባለፈው ታኅሣሥ እስራኤል ለሶማሊላንድ እውቅና የሰጠች የመጀመሪያዋ የዓለማችን ሀገር ሆናለች። ይህ ዜና በሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሐገርጌሳ የደስታ ፈንጠዝያ ፈጥሯል።
ከሶማሊያ ተነጥላ ነጻ ሀገርነቷን አውጃ ከ30 ዓመታት በላይ ለዘለቀችው፤ በራሷ መንግሥት ለምትመራው፣ ፓስፖርት እና መገበያያ ገንዘብ ላላት ሶማሊላንድ ይህ ትልቅ ድል ነው።
ሶማሊላንድ በምትኩ በ2020 ተግባራዊ የተደረገውን የአብርሃም ስምምነት (አብራሃም አኮርድ) አካል እንደምትሆን አስታውቃለች።
ዩኤኢ፣ ባህሬይን እና ሞሮኮ የዚህ ስምምነት አባል ሲሆኑ፣ ከእስራኤል ጋር ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው። ይህ በጋዛ ጦርነት ምክንያት ጫና ለበረታባቸው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ እፎይታ ነው።
"ቀጣናው በተለያዩ የውጭ ኃይሎች የተከፋፈለ ሆኗል። ዩኤኢ እና አስራኤል በአንድ በኩል ሳዑዲ፣ ቱርክ እና ሌሎች በሌላ በኩል ይዘውታል" ይላሉ ማህሙድ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ባለፈው ሰኞ 'ሚድል ኢስት አይ' የተባለው የመገናኛ ብዙኃን ይዞ የወጣው ዘገባ እንደሚጠቁመው በሁለቱ ሀገራት መካከል በተፈጠረው ዲፕሎማሲያዊ ቁርሾ ምክንያት ዩኤኢ ከቦሳሶ አየር ማረፊያ በርካታ ወታደሮቿን እና ከባድ የጦር መሣሪያዎቿን አስወጥታለች።
ማህሙድ፤ የዩኢኤ የቅርብ አጋር የሆነችው ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የመግባቢያ ሰነድ ከፈረሙ ጊዜ ጀምሮ ሶማሊያ ከኤሜሬቶች ጋር ያላት ግንኙነት እየላሸቀ መጥቷል ይላሉ።
"ሶማሊያ ከዩኤኢ ጋር ያላት አለመግባባት የጀመረው አዲስ አበባ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ከፈረመች ጊዜ ጀምሮ ነው። ሶማሊያ ይህን ስምምነት በፅኑ ብታወግዝም ዩኤኢ ግን እንደደገፈች ይሰማታል። ኢትዮጵያ ቃል ብትገባም ተግባራዊ አላደረገችውም። እስራኤል ግን አድርጋዋለች።"
ተንታኙ እንደሚሉት ዩኤኢ የየመን ተገንጣይ ቡድን መሪ የሆኑት አይድሩስ አል-ዙባይዲን የሶማሊያ ግዛትን ተጠቅማ ከሀገር እንዲወጡ ማድረጓ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ቁርሾ የለየት እንዲሆን አድርጎታል።
"የሶማሊያን የአየር ክልል እና አየር ማረፊያ በመጠቀም በሕግ የሚፈለግ ሰውን ማስወጣት ሶማሊያ የምትቀበለው ጉዳይ አይደለም" ሲሉ የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ኦማር ለአል ጀዚራ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት ሳዑዲ አረቢያ ተመሳሳይ ወቀሳ አሰምታለች። የየመን ተንጣይ ቡድን መሪው አል-ዙባይዲ ወደ በርበራ በመርከብ ቀጥሎ ደግሞ በሞቃዲሾ በኩል ወደ አቡ ዳቢ ተጉዟል በማለት የዩኤኢ መኮንኖች ይህን "አቀነባብረዋል" ስትል ወቅሳለች።
ነገር ግን ዩኤኢ በየመን ተንገጣይ ቡድኖችን መደገፏን ታስተባብላለች።
በሶማሊያ እና በዩኤኢ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያ ግንኙነት አደጋ ሲያጠላበት ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
በአውሮፓውያኑ 2018 የወቅቱ የሶማሊያ ፕሬዝደንት የነበሩት ሞሐመድ ፎርማጆ ዩኤኢ በሞቃዲሹ የውስጥ ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ እየገባች ነው በማለት መወንጀላቸው ይታወሳል።
በጊዜው ተቃዋሚ የነበሩት ሼክ ማህሙድ ዩኤኢ በሶማሊያ ያላትን ተሳትፎ ደግፈው ነበር። በየመን ባለው ጦርነት ምክንያት በዩኤኢ እና በሳዑዲ መካከል ያለውን ልዩነት ለግል ጥቅማቸው እያዋሉት ነው ሲሉ የሶማሊያውን ፕሬዝደንት የሚወቅሱ አሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ነገር ግን የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ውሳኔውን ለማስፈጸም አቅም የለውም ሲሉ ማህሙድ ይከራከራሉ።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ማዕከላዊው መንግሥት በሶማሊላንድ ሥልጣኑን ለመተግበር የሚያስችል አቅም ስሌለው ነው።
ከፊል ራስ ገዝ ክልሎች በሆኑት በፑንትላንድ እና በጁባላንድም ላይ ማዕከላዊው መንግሥት ሥልጣን የለውም።
"የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት በእነዚህ ግዛቶች ላይ የበላይነት የለውም። አልፎም ከግዛቶቹ አስተዳዳሪዎች ጋር የሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ ነው" ይላሉ ማህሙድ።
መቀመጫውን ዱባይ ያደረገው ዲፒ ዎርልድ የተሰኘው የሎጂስቲክ ኩባንያ በበርበራ ወደብ ሥራውን እየሠራ የሚገኝ ሲሆን፣ በሶማሊያ መንግሥት ውሳኔ የተበገረ አይመስልም።
"ዲፒ ዎርልድ ትኩረቱ ለሶማሊላንድ እና ለመላው የአፍሪካ ቀንድ የተሳለጠ ንግድ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም ማምጣት ነው።
"ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን፣ የመንግሥት ውይይቶችን እና ዲፕሎማሲያ ግንኙነቶችን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ለሚመለከታቸው ወገኖች ቢቀርቡ ጥሩ ነው" ብሏል ለሮይተርስ የዜና ወኪል በላከው መግለጫ።
ሶማሊላንድ ከዩኤኢ ጋር የገባቻቸው ሁሉም ስምምነቶች "ሕጋዊ እና ተግባራዊ" መሆናቸውን ይቀጥላሉ ብላለች።
ጁባላንድ ደግሞ የፌዴራል መንግሥቱን ውሳኔ "ትርጉም የሌለው" ስትል፣ ፑንትላንድ "ከሕገ-መንግሥታዊ አስተዳደር መርሆዎች ጋር የማይጣጣም" ስትል ኮንናዋለች።
ነገር ግን ማህሙድ እንደሚሉት ሶማሊያ አሁንም ቢሆን ያላትን ተፅዕኖ ተጠቅማ ዩኤኢ እና አጋሮቿ ላይ ጫና ማሳደር ትችላለች።
"የአየር ክልሉን የምትቆጣጠረው ሞቃዲሶ ናት። ይህንን እና ሌሎች ዲፕሎማሲያዎ ጫናዎችን በማሳደር ዩኤኢ እና ክልላዊ ግዛቶች ላይ መጠቀም ትችላለች። ምናልባትም አጋሮቿ የሆኑት ቱርክ እና ሳዑዲን ልታስተባብር ትችላለች" ይላሉ።
ማህሙድ በዩኤኢ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረው ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባት በቅርቡ ይሻሻላል ብለው አይገምቱም።
"መሰል ዲፕሎማሲያዊ ውጥረቶችን ለማረግብ ትልቅ እርምጃ መራመድ ይጠይቃል" ይላሉ።















