የሰውነት ጠረናችንን ጥሩ ወይም መጥፎ የሚያደርጉ ምግቦች የትኞቹ ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ነጭ ሽንኩርት፣ አልኮል፣ ሥጋ ሌላው ቀርቶ ጾም በሰውነታችን ጠረን ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፤ ጠረናችንን ይለውጣሉ።
ሁላችንም የየራሳችን የሆነ የሰውነት ጠረን አለን - ልክ እንደ ጣት አሻራችን የተለያየ።
ያሉን የተለያዩ ማንነቶች በስሜታችን እና በጤናችን ላይ ተፅዕኖ እንደሚያደርጉት ሁሉ ጠረናችን ላይም ጉልህ ተፅዕኖ ያሳድራሉ።
በስኮትላንድ ስተርሊንግ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ሥነ ልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት ክሬግ ሮበርትስ ፣ የሰውነት ጠረናችን የሚወሰነው በዘር፣ በሆርሞን፣ በጤና ሁኔታ እና ከንጽህና አጠባበቅ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ባለፉት ጥቂት አስርተ ዓመታት ተደርሶበታል ይላሉ።
አብዛኞቹ እነዚሀ ነገሮች እኛ የማንቆጣጠራቸው ቢሆኑም ሁሉም ግን አይደሉም።
የምንመገበው ምግብም በሰውነት ጠረናችን ላይ ወሳኝ ተፅዕኖ አለው።
የሰውነት ጠረናችን ላይ ብቻም ሳይሆን ለሰዎች ማራኪ ሆነን ለመቅረብም እንደሚረዳ ጥናቶች ያሳያሉ።
ትንፋሽ እና ላብ
በኒው ዮርክ ቢንጋምተን ዩኒቨርሲቲ የጤና እና ደኅንነት ጥናት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ሊና ቤግዳች የምንመገባቸው ምግቦች የሰውነታችንን ጠረን የሚቀይሩበት ሁለት መስመሮች አሉ ይላሉ። እነዚህም አንጀታችን እና ቆዳችን ናቸው።
የመጀመሪያው አንጀታችን ሲሆን፣ አንጀት ምግብ በሚፈጭበት ወቅት ምግብ ወደ ኃይል በሚቀየርበትን ሒደት (ሜታቦሊዝም ሥርዓት) ባክቴሪያዎች ሥራ ላይ ናቸው።
በመሆኑም የምግቡ ኬሚካሎች ከባክቴሪያዎቹ ጋር ግንኙነት ሲፈጥሩ ከሰውነታችን ጋዝ እና ቅንጣጢቶች ይወጣሉ። ይህም እንደምንመገበው የምግብ ዓይነት መጥፎ ትንፋሽ ወይም ሃሊቶሲስ ያስከትላል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከምግብ የመፈጨት ሒደት ባሻገር በሌሎች ምክንያቶች በዓለም አንድ ሦስተኛ የሚሆኑ አዋቂዎች ይህ ችግር ያጋጥማቸዋል።
ሁለተኛው ቆዳችን ነው። ከምግብ የምናገኘው ንጥረ ነገሮች ወደ ደም ቧንቧ እና ሌሎች ኅብረ ሕዋሳት ይጓዛሉ። በዚህ ሒደትም የተወሰኑት ወደ ቆዳችን ይገባሉ በዚህ ጊዜ ቆዳችን ላይ ከሚገኙ ባክቴሪያዎች ጋር በመገናኘት ጠረን ይፈጥራሉ።
ላብ በራሱ ጠረን አልባ ነው። ላባችን ጠረን እንዲኖረው የሚያደርገው በላብ አማካኝነት የሚወጡ የቆዳችን ባክቴሪያዎች ናቸው።
የተለያዩ ምግቦች የተለያየ ዓይነት ኬሚካላዊ ውህዶች ያሏቸው ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት የተለያየ መጠን ያለው ጠረን እንዲፈጠር ያደርጋሉ።
መጥፎ ውጤት የሚያስከትሉ ምግቦች አንድ የጋራ ይዘት አላቸው - ሰልፈር።
ሆኖም አንዳንድ ጥናቶች በሚያስገርም ሁኔታ እነዚህ ሽታ ያላቸው ውህዶች ይበልጥ ማራኪ እንድንሆን የሚያደርግ ያልተጠበቀ ውጤት ሊኖራቸው እንደሚችል አመልክተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፍራፍሬ እና አትክልቶች
እንደ ብሮኮሊ፣ ጥቅል ጎመን እና የአበባ ጎመን ያሉ ምግቦች ጤናማ ምግቦች ተደርገው የሚወሰዱ ሲሆን፣ ውስጣቸው ግን በብዛት በሰልፈር ውህዶች ተሞሉ ናቸው።
በዚህም ምክንያት ብዙውን ጊዜ የተበላሸ እንቁላል ሽታን ያስታውሳሉ።
እነዚህ ውህዶች በደም ውስጥ ሲገቡ እና ከቆዳ ባክቴሪያ ጋር ሲገናኙ የሰውነት ላብ ኃይለኛ ሽታ ወዳለው ፈሳሽ ሊለወጥ እንደሚችል የሥነ ምግብ ባለሙያዋ ኬሪ ቢሰን ተናግረዋል።
እንደ ነጭ ሽንኩርት እና ሽንኩርት ያሉ ምግቦችም በተመሳሳይ ምክንያት የላባችን እና ትንፋሻችን ጠረን ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ።
የሚገርመው ግን ነጭ ሽንኩርት የሰዎችን የትንፋሽ ጠረን ቢለውጡም ከብብታቸው የሚወጣውን ላብ የበለጠ ማራኪ እንደሚያደርግ ጥናቶች አሳይተዋል።
ተመራማሪዎች በጥናታቸው ከተሳተፉ 42 ወንዶች መካከል የተወሰኑት ትንሽ ነጭ ሽንኩርት ፣ የተወሰኑት የነጭ ሽንኩርት ሰፕሊመንት (በመድኃኒት መልክ የተዘጋጀ አጋዥ ምግብ)፣ ሌሎች ደግሞ ብዙ ነጭ ሽንኩርት እንዲመገቡ በማድረግ እና የብብት ፓድ እንዲያደርጉ በማድረግ ከ12 ሰዓታት በኋላ ሰብስበዋል።
ከዚያም 82 ሴቶች የብብት ፓዶቹን በማሽተት በአስደሳች፣ በማራኪነት፣ በወንዳወንድነት፣ በጠረኑ ጥንካሬ ደረጃ እንዲሰጡ ተጠይቀው ነበር።
በዚህም መሠረት ትንሽ ነጭ ሽንኩርት የተመገቡ ወንዶች ብዙ ምላሽ ያላገኙ ሲሆን፣ ብዙ ነጭ ሽንኩርት የተመገቡት ማራኪ እንደሆኑ፣ ነጭ ሽንኩርትን የሚተካ አጋዥ መድኃኒት የወሰዱት ደግሞ በጣም ማራኪ እንደሆኑ ለይተዋል።
ከዚህ ሙከራ ጀርባ ያሉትና በቼክ ሪፐብሊክ ቻርልስ ዩኒቨርሲቲ የሰው አካል እና ኬሚካላዊ ግንኙነት ተመራማሪ ጃን ሃቭሊችክ በጥናቱ ውጤት እጅጉን በመገረማቸው ይህንን ጥናት ሦስት ጊዜ ደግመው ማካሄዳቸውን ተናግረዋል።
ነጭ ሽንኩርት ፀረ መርዛማ እና ፀረ ተህዋስያን ስላለው የሰዎችን ጤና ያሻሽላል፤ የእነዚህን ወንዶች ጠረን በሴቶች ዘንድ ማራኪ ያደረግውም ይህ ሊሆን እንደሚችል መላ ምታቸውን ሰጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሌሎች አትክልቶችም በሰውነታችን ጠረን ላይ በጣም የተለየ ውጤት ያስከትላሉ።
አስፓራገስ የሚባለው እፅዋት አስፓራገሲስ የተባለ አሲድ ይዘት አለው። በመሆኑም ከሰውነታችን ጋር ሲዋሃድ ሰልፈር ውህድ ይለቃል።
እነዚህ ውህዶች 'ሜታኔቲኖል' እና 'ዳይሜትይል ሰልፋይድ' የተባሉ ንጥረ ነገሮች ያላቸው ሲሆን፣ ይህም ላባችን እና ሽንታችን በተወሰነ ደረጃ እንዲሸት ያደርጋሉ።
የሰልፈር ውህዶች በጣም ተለዋዋጭ ናቸው። በመሆኑም በቀላሉ አየር ውስጥ ይበተናሉ። ለዚያም ነው የመጸዳጃ ቤት ሳህኖች በቀላሉ የሚሸቱት። ይህ ጠረን ብዙውን ጊዜ ከአምስት ሰዓታት በላይ ይቆያል።
ምንም እንኳን በዚህ ላይ የተሠሩ ጥናቶች የተለያየ ግኝት ይዘው እየወጡ ቢሆንም ሁሉም ሰው ይህንን ጠረን አያመነጭም።
በአውሮፓውያኑ 1950ዎቹ የተሠራ አንድ ጥናት ከ50 በመቶ የሚያንሱ ሰዎች የአስፓራገስ ጠረን ያለው ሽታ እንደሚያወጡ የገለጸ ሲሆን፣ በ2010 ደግሞ ተመራማሪዎች ከ90 በመቶ በላይ በሆኑ የጥናቱ ተሳታፊዎች ላይ እንደታየ አሳይተዋል።
በመሆኑም በዚህ ላይ የተደረሰ ቁርጥ ያለ ድምዳሜ የለም። ከዚህም ባሻገር ከዘር ጋር እንደሚገናኝ ተጠቁሟል።
ነገር ግን በአጠቃላይ ወደ ፍራፍሬ እና አትክልት ስንመጣ እነዚህን ምግቦች በብዛት መመገብ የበለጠ ማራኪ ጠረን እንዲኖረን ያደርገናል።
በ2017 በአውስትራሊያ በተካሄደ ጥናት በብዛት ፍራፍሬ እና አትክልቶችን የሚመገቡ ወንዶች ጠረን ከፍራፍሬ፣ ከአበባ እና ከጣፋጭ መዓዛዎች ጋር ተገናኝቷል።
ጥናቱ ጨምሮም የሰዎችን ፊት ደረጃ እንዲሰጥ ያደረገ ሲሆን ከካሮት በሚገኘው ንጥረ ነገር 'ካረቴኖድ' የበለጸገ፣ ዱባ፣ ቲማቲም፣ ፓፓያ እና ሌሎች ምግቦችን የሚመገቡ የበለጠ ማራኪ ሆነው ተገኝተዋል።
ነገር ግን ተመሳሳይ ጥናት አነስተኛ መጠን ያለው ስብ፣ ሥጋ፣ እንቁላል እና ቶፉ የሚመገቡ ሰዎች የበለጠ ጥሩ የላብ ጠረን እንዳላቸው አሳይቷል።
ካርቦሃይድሬት የበዛባቸው ምግቦች መመገብ ደግሞ ዝቅተኛ ማራኪ ጠረን እንድንወጣ ያደርጋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሥጋ እና ዓሳ
ሥጋ እና ዓሳ የተለየ የሰውነት ጠረን እንዲመነጭ ያደርጋሉ። የእንስሳቱ ፕሮቲን ተሰባብሮ ወደ አሚኖአሲድ እና ስብ ተለውጦ በሰውነት ቆዳ ላይ ከሚገኙ ባክቴሪያዎች ጋር ሲገናኙ የተለየ ጠረን ይፈጥራል።
ለምሳሌ ዓሳ እና ጥራጥሬዎች 'ትራይሚታይላሚን' በተባለ በጣም ጠንካራ የጠረን ውህድ የተሞሉ በመሆናቸው የሰውነት ጠረን ያመጣሉ።
'የዓሳ ጠረን ሲንድረም' በመባል የሚታወቅ 'ትራይማታይላሚኑሪያ' የተባለ የጤና እክል አለ። ይህ በሽታ ሰውነታችን ትራይማታይላሚን የተባለውን ንጥረ ነገር ሽታ ወደ ሌላ ውህድ መቀየር ሳይችል ሲቀር የሚከሰት እንደሆነ ቢሰን ያስረዳሉ።
ይህም በጣም ጠንካራ ወደሆነ የሰውነት ጠረን ሊያመራ ይችላል የሚሉት ቢንሰን፣ ነገረ ግን አልፎ አልፎ የሚከሰት እና እምብዛም ያልተለመደ እንደሆነ ገልጸዋል።
ለምሳሌ በ2025 የወጣ አንድ ዘገባ እንዳመለከተው የአስር ወር ሕጻን ልጅ ዓሳ ከበላ በኋላ ትራይሚታይላሚኑሪያ አጋጥሞት እንደ የተበላሸ ዓሳ መሽተት ጀምሮ ነበር።
ሆኖም ያጋጠመው የጤና እክል ጊዜያዊ የነበረ ሲሆን፣ በተደረገለት ክትትል ምልክቶቹ ሳይታዩ ዓሳ መመገብ ችሏል።
በ2006 በሃቭሊችክ ቡድን በአዋቂ ወንዶች ላይ የተሠራ ሌላ ጥናት ሥጋ የበለጠ ማራኪ ያደርግ እንደሆነ ተመልክቷል።
ተመራማሪዎቹ 30 አዋቂ ወንዶችን ለሁለት ሳምንት ሥጋ እና ከሥጋ ውጭ ያሉ ምግቦችን እንዲመገቡ በማድረግ ሴቶችም ለጠረናቸው ደረጃ እንዲሰጡ ጠይቀው ነበር። በዚህም ሥጋ ያልተመገቡ ሰዎች በአማካኝ ማራኪ፣ በጣም ጥሩ እና ጠረናቸው ያልተጋነነ ሆኖ አግኝተውታል።
"በአስገራሚ ሁኔታ ሥጋ የሚመገቡ ሰዎች ከማይመገቡት ጋር ሲነጻጸር በትንሹም ቢሆን የከፋ ጠረን ነበራቸው" ብለዋል ሃቭሊችክ።
ሥጋ በሰው ልጅ የአመጋገብ ሥርዓት ውስጥ ወሳኝ የምግብ አካል ቢሆንም "ቀደምት የሰው ልጆች አሁን ላይ ውስብስብ እና የምግብ ኢንደስትሪ በተስፋፋበት ዘመን እንደሚኖር ሰው ብዙ ሥጋ አይመገቡም ነበር" የሚሉት ሃቭሊችክ፣ በሰው ልጅ አመጣጥ ታሪክ ውስጥ በየቀኑ ሥጋ መመገብ የተለመደ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አልኮል እና ቡና
አልኮል በብዛት እና መደበኛ በሆነ ሁኔታ ሲጠጣ አንጀት እና ላብ የሚያመነጩ ዕጢዎች መጥፎ ጠረን እንዲወጡ ያደርጋሉ።
ሰውነታችን የአልኮል መጠጥ ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮችን ጉበት ውስጥ ሲሰባብር 'አሴታልዲህይድ' የተባለ መርዛማ እና ተለዋዋጭ ውህድ ይለቃል። ይህም ጠንካራ እና በቀላሉ የሚለይ ጠረንን ይፈጥራል።
አንድ ጥናት የፖሊስ መኮንኖች ሰዎች የአልኮል መጠጥ እንደጠጡ ከ60 እስከ 85 በመቶ በትንፋሽ ጠረናቸው መለየት ይችላሉ። የአልኮል መጠጥ በቂ ፈሳሽ እንዳይኖረን እና የምራቅ መጠንን በመቀነስ በርካታ ባክቴሪዎች አፋችን ውስጥ እንዲቆዩ በማድረግ መጥፎ የአፍ ጠረንን ያስከትላሉ።
አንድ ሌላ ጥናትም በየቀኑ አልኮል መጠጥ ከሚጠጡ 235 ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ስለ በመጥፎ የአፍ ጠረን ይቸገራሉ። በትንፋሻቸው ውስጥም ከፍተኛ መጠን ያለው ተለዋዋጭ የሆነው የሰልፈር ውህድ ተገኝቶባቸዋል።
በ2010 የተሠራ ሌላ ጥናትም ቢራ የጠጡ ወንዶች እና በአልኮል ፋንታ ውሃ እንዲጠጡ በማድረግ በተካሄደ ሙከራ ቢራ የጠጡት ማራኪ ጠረን እንደሌላቸው አሳይቷል።
ሌላው ከሰውነት ጠረን ጋር የሚነሱት መጠጦች ደግሞ ቡና እና ሻይ ናቸው።
ካፌን ተባለው ንጥረ ነገር በቡና እና በሻይ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ላብ የሚያመነጩትን አፖክሪን ዕጢዎችን ያነቃቃሉ።
በዚህም ምክንያት የላብ መጠን የሚጨምር ሲሆን፣ ባክቴሪያዎች እንዲያድጉ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ። ይህም ጠንካራ የሰውነት ጠረን እንዲኖረን ያደርጋል ይላሉ ቢንሰን።
በተጨማሪም አንድ ጥናት የካፌን ቅንጣጢቶች በላብ ውስጥ ሊገኙ እንደሚችሉ ያሳየ ሲሆን፣ ሆኖም ካፌን ራሱ የሰውነት ጠረናችን ላይ ተፅዕኖ ያደርስ እንደሆን የሚያሳይ መረጃ የለም።
"አጥቢዎች ነን፤ በመሆኑም የሁሉም አጥቢዎች ጠረን ለማኅበራዊ መስተጋብር ወሳኝ ነው" ይላሉ የሰውነት መዓዛ እና ማኅበራዊ መስተጋብር ላይ ጥናት የሰሩት ሮበርትስ።
ሰዎች ማራኪ ሆነን እንዲያገኙን ከሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የሰውነት ጠረን ነው። እንደ ሰዎች መልክ ፣ ባሕርይ እና ንግግር ካሉ ሌሎች ወሳኝ ማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ "የጠረንን ተፅዕኖ መነጠል ካልተቻ ከባድ ነው" ይላሉ ሮበርትስ።
ሆኖም አሁንም ጠረንን የተመለከቱ የተለያዩ የንጽጽር ጥናቶች እየወጡ ነው።
ለምሳሌ ሃቭሊሴች ሴቶች መደበኛ አመጋገብ እንዲከተሉ እና ለ48 ሰዓታት እንዲጾሙ በማድረግ ወንዶች ደግሞ ለጠረናቸው ደረጃ እንዲሰጡ አድርገው ነበር።
በቡድኑ ውስጥ ሰፋ ልዩነት ባይታይም የጾሙ ሴቶች ካልጾሙት በጣም ማራኪ ጠረን ነበራቸው ። "ይህም ያልጠበቅነው ነው" ብለዋል ሃቭሊችክ።
ጾም ላባችን የተሻለ ጥሩ ጠረን እንዲኖረው እንደሚያደርግ ጥናት ቢያመለክትም በ2018 በስዊትዘርላንድ በተሠራ አንድ ጥናት ጾም የሰዎችን የትንፋሽ ጠረን አስከፊ እንደሚያደርገው አመልክቷል።
በተለያዩ ጊዜ የሚወጡ አስገራሚ የጥናት ውጤቶች እንደ ሮበርት እና ሃቭሊችክ ያሉ ተመራማሪዎችን ምግብ የሰውነታችንን ጠረን እና መልክ ለመለወጣቸው ግልጽ የሆነ ቀመር እንደሌለ እንዲረዱ አድርጓቸዋል። ብዙ ተለዋዋጭ ነገሮችም አሉ።
"በጣም ብዙ ጠረን ያላቸው ውህዶች አሉ። በአብዛኞቹ ውስጥ ያሉት ውህዶች የሰውነታችን ጠረን ላይ እንዴት ተፅእኖ እንደሚያደርጉ አናውቅም፤ ሆኖም የማድረግ ከፍተኛ ዕድል አላቸው" ብለዋል ሃቭሊችክ።















