እየተስፋፋ የመጣውን የካንሰር በሽታን በአመጋገብ መከላከል እና መፈወስ ይቻላል?

እርድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እርድ እንደ አማራጭ ሕክምና ከሚወሰዱ አንዱ ነው

የአመጋገብ ለውጥ በማድረግ እና ከመደበኛው ሕክምና ውጪ ያሉ አማራጭ ሕክምናዎችን በመጠቀም ከካንሰር ማገገማቸውን የሚናገሩ አሉ።

የካንሰር ሕክምና ባለሙያዎች ግን ለካንሰር አማራጭ የሚባል ሕክምና መኖሩን የሚያሳይ መረጃ የለም ሲሉ ይከራከራሉ።

ለመሆኑ አማራጭ የካንሰር ሕክምና የሚባሉት የትኞቹ ናቸው? ለሕመሙ መፍትሄስ ይሰጣሉ?

ሕንዳዊው የክሪኬት ስረተኛ እና ፖለቲከኛ ናቭጆት ሲንግ ሲድሁ ባለቤቱ ከካንሰር ነጻ መሆኗን ተናግሯል።

ባለቤቱ የሎሚ ውሃ በመጠጣት፣ እርድ በመመገብ፣ አፕል ሳይደር፣ ኮምጣጤ በመጠጣት፣ የኒም ቅጠል በመመገብ እንዲሁም ዱባ፣ የሮማን ፍሬ፣ እንኮይ፣ ቀይ ሥር እና ለውዝ በመመገብ ከካንሰር ነጻ እንደሆነች ነው የተናገረው።

ይህን የሚናገርበት ተንቀሳቃሽ ምሥል በበርካቶች ታይቷል።

በሕንድ የሚገኙ 200 የካንሰር ሕክምና ባለሙያዎች በሰጡት ምላሽ፣ በእነዚህ ፍራፍሬዎች እና ምግቦች ላይ ጥናት እየተደረገ ቢሆንም ከካንሰር ፈዋሽ ስለመሆናቸው ማስረጃ የለም።

"ያልተረጋገጡ መድኃኒቶችን" ኅብረተሰቡ እንዳይጠቀም እና የካንሰር መደበኛ ሕክምና ሳያገኝ እንዳይዘገይም አስጠንቅቀዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አውስትራሊያዊቷ ሞዴል ኤሊ ማክፈርሰን የጡት ካንሰር እንዳለባት ከሰባት ዓመት በፊት እንደተነገራት እና ከካንሰር ሕክምና (ኬሞቴራፒ) ይልቅ "ልብና ቀልብን ያማከለ ሁሉን አቀፍ ሕክምና" ማግኘቷን ተናግራለች።

እንደ አኩፓንክቸር፣ ዮጋ እና ሜዲቴሽን ያሉ አማራጭ ሕክምናዎች እንደ ኬሞቴራፒ ካለ የጡት ካንሰር መደበኛ ሕክምና ጎን ለጎን ይወሰዳሉ።

አማራጭ ሕክምናዎቹ ሕመምን የሚቀንሱ እና የሰውነት ጤናን የሚጠብቁ መሆናቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ሚኒራል እና ቫይታሚን ያላቸው ምግቦችን ማዘውተር ከሚመከሩ መካከል ናቸው።

ባለሙያዎች እንደሚሉት አንዳንድ አማራጭ ሕክምናዎች የጎንዮሽ ጉዳት ያስከትላሉ። በመደበኛ ሕክምና ውስጥ ጣልቃ ሊገቡም ይችላሉ።

በአውሮፓውያኑ 2018 በ'ጀማ አንኮሎጂ' የተሠራው ጥናት እንደሚለው፣ አማራጭ ሕክምና ከካንሰር የመትረፍ ዕድልን ሊቀንስ ይችላል።

ሆኖም ግን የካንሰር አማራጭ ሕክምና መንገዶች ዕውቅናቸው እየጨመረ ነው።

'ዋን አሜሪካን ሶሳይቲ ኦፍ ክሊኒካል ኦንኮሎጂ ካንሰር ኦፒንየንስ' በሚል የተሠራ የዳሰሳ ጥናት እንደሚጠቁመው፣ በአሜሪካ 40 በመቶ ጎልማሶች ካንሰር በአማራጭ ሕክምና ብቻ እንደሚድን ያምናሉ።

ከካንሰር መዳን የሚቻልባቸውን መንገዶች የሚጠቁሙ ድረ ገጾች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተመልካቾች አሏቸው።

የካንሰር ሕሙማን ምን መመገብ እንዳለባቸው የሚጠቁሙ መጻሕፍትም በተለያዩ መድረኮች ላይ በስፋት ይሸጣሉ።

ካንሰርን አመጋገብን በመለወጥ "በተፈጥሯዊ መንገድ" መከላከል ይቻላል በሚል በኤክስ ላይ የተለጠፈ አንድ ጽሑፍ በ40 ሰዓታት ውስጥ 200,000 'ላይክ' አግኝቷል።

የካንሰር ሕዋስን "ለማስራብ" መጾም አስፈላጊ እንደሆነ የሚመክሩ ገጾች ያሉ ሲሆን፣ "ዘረ መላችሁን አስተካክሉ" የሚሉና "የደም ሕዋሳችሁን አቅም አሳድጉ" የሚሉ ምክሮችም ይደመጣሉ።

በካንሰር ላይ የሚሠራው ማክሚላን ተቋምም አማራጭ ሕክምናን ለመጀመር ማሰቡን አስታውቋል። ሕሙማን ከሐኪሞቻቸው ጋር እንዲመካከሩም ያሳስባል።

አማራጭ ሕክምና ለምን ታዋቂ ሆነ?

አማራጭ ሕክምናን እንደ 'ተዓምራዊ ፈውስ' በማስተዋወቅ ረገድ የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ዋነኛውን ሚና ይጫወታል።

የካንሰር ቀዶ ሕክምና ባለሙያ ዶ/ር ሊዝ ኦሪዮዳን "ካንሰር አስፈሪ ነው። ሕሙማን መስማት የሚፈልጉት የመዳን ተስፋ የሚሰጥ መረጃ ነው። መደበኛ ሐኪሞች ያንን ማድረግ አንችልም። እኛ የምንናገረው ስለሚኖረው ጉዳት ነው" ትላለች።

'መድኃኒት' ተብለው የሚተዋወቁት ሕመም እንደማያስከትሉ እና ተፈጥሯዊ እንደሆኑ ይገለጻል።

ይህም ተስፋ ለሚሹ ሕሙማን ከመደበኛው ሕክምናው በተሻለ አሳማኝ ይመስላል።

በተለያዩ አገራት የሚኖሩ የካንሰር ሕሙማን ሕክምናን በቀላሉ ማግኘት አይችሉም። ማግኘት ቢችሉም ዋጋው ውድ ነው። ስለዚህም ስለ አማራጭ ሕክምና መስማት ይመርጣሉ።

ዶ/ር ሊዝ "ገንዘብ ለሌለው ሰው ርካሽ የሕክምና አማራጭ መጠቀም ይቀላል። ሆኖም ግን አጣብቂኝ ውስጥ ለገቡ ሰዎች የማያስፈልጋቸውን ነገር በመሸጥ የሚያተርፉ መኖራቸው ያሳስበኛል" ስትል ታስረዳለች።

በአፍሪካ ስለ ካንሰርና መደበኛ ሕክምናው ያለው ግንዛቤ ውስን ነው። ባህላዊ እና አማራጭ ሕክምናዎች በስፋት የሚስተዋሉትም ለዚህ ነው።

በአህጉሪቱ ያሉ ውስን ሕክምና ሰጪዎችና ሐኪሞች እንዲሁም የጤና መድኅን ማጣትም ይጠቀሳሉ።

አማራጭ ሕክምናን መከተል ከባህል ጋር የተሳሰረም ነው።

አመጋገብን በመለወጥ ከካንሰር መዳን ይቻል የሚል ዕሳቤ አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አመጋገብን በመለወጥ ከካንሰር መዳን ይቻል የሚል ዕሳቤ አለ

ዋነኛ አማራጭ ሕክምናዎች የትኞቹ ናቸው?

በአፍሪካ፣ በእስያ እና በሕንድ ጥንታዊ ሕክምናዎች እንዲሁም ፍልስፍናዎች ታማኝነት አላቸው።

የሕንድ ባህላዊ ሕክምና (አዩርቬዳ) እንዲሁም የቻይና ባህላዊ ሕክምና ለአንዳንድ ሕመሞች ፍቱን ቢሆኑም ካንሰርን ስለማዳናቸው የሚጠቁም ማስረጃ የለም።

አዩርቬዳ

በሕንድ እርድ እንደ አማራጭ የካንሰር ሕክምና ይወሰዳል።

ጥንታዊ የሕንድ ባህላዊ ሕክምና ቅጠላ ቅጠል እና ሰውነት ማሸት (ማሳጅ) ላይ የተመረኮዘ ነው።

'ማርኬት ሪሰርች ፊውቸር' በሠራው ጥናት መሠረት፣ በአውሮፓውያኑ 2028 የአዩርቬዳ ሕክምና ንግድ በሦስት እጥፍ እንደሚጨምር ይታመናል።

በሕንድ ገጠራማ አካባቢዎች አማራጭ ሕክምና ተደርገው ከሚወሰዱ መካከል አመጋገብ ላይ ያተኮረው ናቹሮቴራፒ፣ የአንድን ሕመም ምልክቶች በማስመሰል የሚሰጥ ሕክምና (ሆሜዮፓቲ)፣ የስንዴ ሳርን በመጠቀም የሚሰጥ ሕክምና ይጠቀሳሉ።

በተጨማሪም የውሃ ሕክም (ሃይድሮቴራፒ)፣ መርፌ ሰውነት ላይ በመሰካት የሚሰጥ ሕክምና (አኩፓንክቸር)፣ ሽንትን በመጠቀም የሚሰጥ ሕክምና (አውቶዩሪን ቴራፒ)፣ አጥንትና ጅማትን በማሳሳብ የሚሰጥ ሕክምና (ኦስቲዮፓቲ) እና በተመስጦ ወይም ሜዲቴሽን የሚሰጥ ሕክምናም (ቪፓሳና) በዚሁ ዘርፍ የሚካተቱ ናቸው።

ዶ/ር ሊዝ እንደምትለው፣ ከመደበኛ የካንሰር ሕክምና ጎን ለጎን ሕመምን ለማስታገስ የሚውሉ ሕክምናዎች ቢኖሩም አንዳንዶቹ አማራጭ ሕክምናዎች ግን መደበኛ ሕክምናን ያደናቅፋሉ።

'ካንሰር ሪሰርች ዩኬ' እንደሚለው፣ በእርድ ውስጥ የሚገኘው ኩርኩሚን የተባለው ንጥረ ነገር በአንዳንድ የካንሰር ዓይነቶች ላይ የካንሰር ሕዋስን መግደል ይችላል። ሆኖም ግን ተጨማሪ ጥናት ያስፈልጋል።

እርድም ይሁን ኩርኩሚን ካንሰርን መከላከል ወይም ማከም ስለመቻሉ ማስረጃ እንደሌለም ያስረዳል።

ዮጋ እንደ አማራጭ ሕክምና ይወሰዳል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዮጋ እንደ አማራጭ ሕክምና ይወሰዳል

የቻይና ባህላዊ ሕክምና

በምሥራቁ እና በምዕራቡ ዓለም የካንሰር ሕሙማን የቻይና ባህላዊ ሕክምናን እንደ አማራጭ ይወስዳሉ።

በ'ክሊኒካል ኦንኮሎጂ' መጽሔታ የታተመ ዘገባ እንደሚጠቁመው ግን ውጤታማነታቸው እና ሳይንሳዊነታቸው ላይ የካንሰር ሐኪሞች ጥያቄ ያነሳሉ።

መርፌ ሰውነት ላይ በመሰካት የሚሰጥ ሕክምና (አኩፓንክቸር)፣ ሰውነትን በማሸት የሚሰጥ ሕክምና (ማሳጅ ቴራፒ)፣ ቅጠላ ቅጠልን በመጠቀም የሚሰጥ ሕክምና እንዲሁም የቻይናውን ማርሻል አርት ታይ ቺ በመጠቀም የሚሰጥ ሕክምና በዋናነት ይጠቀሳሉ።

በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዕጽዋትም ለአማራጭ ሕክምና ይውላሉ።

ዶ/ር ሊዝ እንደምትለው የቻይና ባህላዊ ሕክምና ሐኪሞችን በማማከር ከመደበኛ የካንሰር ሕክምና ጎን ለጎን ጥቅም ላይ ሊውል ቢችልም፣ አንዳንድ የዕጽዋት መድኃኒቶች መደበኛ ሕክምናን ሊያደናቅፉ ይችላሉ።

አመጋገብን መለወጥ

አትክልት ብቻ መመገብ እና ካርቦሃይድሬትን ቀንሶ በምትኩ ስብ ያለባቸው ምግቦች መውሰድ (ኪቶ) እንደ አማራጭ ሕክምና ይቀርባሉ።

አመጋገብ ላይ የሚደረገው ገደብ 'የካንሰር ሕዋስን' ለመግደል ነው በሚል በዓለም ታዋቂ ሆኗል።

የካንሰር ተመራማሪው ዶ/ር ዴቪድ ሮበርት "ካንሰርን ምግብ በመከልከል መግደል አይቻልም። ካንሰር ያለበት ሰው ክብደቱ ከቀነሰ አደገኛ ሊሆን ይችላል" ይላል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚያይዋቸው መረጃዎች ምክንያት በካንሰር ለመያዛቸው ወይም ሕመሙ ለመባባሱ ራሳቸውን ተጠያቂ የሚያደርጉ ብዙዎች መሆናቸውን ያክላል።

እነዚህ የአመጋገብ ለውጦች የሚያስከትሉትን ጉዳት ባለመገንዘብ የሚከተሏቸው አሉ።

የካንሰር ሐኪሙ ዶ/ር ካንፑርያ ባሂታ እንደሚለው፣ በሕንድ ሕሙማን በማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ሥር ይወድቃሉ።

"በራስ ፈቃድ ተነሳስቶ ማንኛውንም ነገር መመገብ ወይም መጠጣት ጉዳት ያስከትላል" ሲል ያስጠነቅቃል።

ሕክምና

የፎቶው ባለመብት, EPA

ፌንቤንዛዶል

ፌንቤንዛዶል ጥገኛ ተዋህሲ ወይም ፓራሳይቶች በእንስሳት ላይ የሚፈጥሩትን ኢንፌክሽን ለማከም የሚውል መድኃኒት ነው።

ይህንን መድኃኒት ከሌሎች አማራጭ ሕክምናዎች ጎን ለጎን በመውሰድ ከካንሰር መፈወሱን አንድ አሜሪካዊ ነጋዴ ከተናገረ በኋላ መድኃኒቱን ለካንሰር ሕክምና የማዋል ሐሳብ ታዋቂ ሆኗል።

ነጋዴው መደበኛ የካንሰር ሕክምና ምርምር ውስጥ ተካቶ እንደነበር ግን አልተናገረም።

መድኃኒቱ በደቡብ ኮሪያ በአንዴ ተሽጦ አለቀ። ብዙዎች 'የሕክምና' ጉዟቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩም ጀመር።

የሳምባ ካንሰር ያለበት ኮሜድያን እና ድምጻዊ መድኃኒቱን መውሰዱን ሲናገር የበለጠ መድኃኒቱ ታወቀ። መድኃኒቱ ውጤት ስላላመጣ ማቋረጡን ኋላ ላይ ተናግሯል።

'ካንሰር ሪሰርች ዩኬ' እንደሚለው፣ ይህ መድኃኒት ምርምር አልተደረገበትም።

ጊሽጣ

በእንግሊዘኛው ግራቪዮላ የሚባለው የጊሽጣ ፍሬ እንዲሁም ቅጠሉ እና የዛፉ ልጣጭ በአፍሪካ እንዲሁም በደቡብ አሜሪካ ለተለያዩ ሕክምናዎች ይውላል።

ለአንዳንድ ኢንፌክሽኖችም መድኃኒት ነው።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለካንሰር መድኃኒት እንደሆነ ይነገራል። ከኬሞቴራፒ 10 ሺህ እጥፍ ሊያድን ይችላል ብለው የሚናገሩም አሉ።

ሆኖም ግን ስለ ካንሰር የሚመራመው 'ፍሬንች ናሽናል ካንሰር ኢንስቲትዩት' ካንሰርን የሚያድን 'ተዓምራዊ ምግብ' የለም ይላል።

ሐኪሞች ምን ይመክራሉ?

አማራጭ ሕክምናን መጠቀም ሊያስከትል ስለሚችለው ጉዳት ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

አወዛጋቢ የሆኑ መንገዶችን በመከተል ከካንሰር የመትረፍ ዕድላቸውን የሚቀንሱም እየተበራከቱ ነው።

ዶ/ር ሊዝ እንደምትለው፣ አንዳንዶቹ አማራጭ ሕክምናዎች ከመደበኛ ሕክምና ጎን ለጎን መሄድ ይችላሉ።

"አማራጭ ሕክምናን ብቻ ለመከተል ሰዎች ሲወስኑ ችግር ይፈጠራል። አማራጭ ሕክምናን ብቻ መከተል የመሞት ዕድልን በሁለት ከግማሽ እንደሚጨምር እናውቃለን" ትላለች።

ዶ/ር ዴቪድ እንደሚለው፣ የካንሰር ሕክምና ሳይንሳዊ ጥናትን መነሻ ያደረገ ነው።

"ከካንሰር የመዳን ዕድል ሰፊ እየሆነ መጥቷል። በሳይንቲስቶችና ሐኪሞች አማይነት አሁን ካለውም በላይ ከፍ ሊል ይችላል። ይህ በአማራጭ ሕክምና አይገኝም" ሲል ያስረዳል።

'ኢንዴክስ ማክስ ኢንስትቲትዩት ኦፍ ካንሰር ኬር' ኃላፊ ዶ/ር ሀሪት ቻቱቬዲ እንደምትለው፣ ካንሰር "አንድ ተዓምራዊ ቀመር ያለው" አንድ ዓይነት ሕመም ብቻ አይደለም።

መደበኛ ሕክምና እያንዳዱ ታካሚ በሚያስፈልገው መንገድ የሚሰጥ እንዲሁም ባለው የካንሰር ሕዋስ ዓይነት የሚወሰን መሆኑን ታስረዳለች።

ሕመሙ የት አካባቢ ተነሳ፣ ወዴት አካባቢ በምን ያህል ፍጥነት ተሠራጨ የሚለውን መነሻ በማድረግ መደበኛ ሕክምና ይሰጣል።

ታካሚዎች ሕመማቸውን ለማስታገስ አማራጭ ሕክምና መውሰዳቸውን ሐኪሞች አይቃረኑም።

ሆኖም ግን መደበኛ ሕክምናን በመተው የሚደረግ አማራጭ ሕክምናን አይደግፉም።