በእርግጥ ጉንዳኖች በሰዎች ላይ ያለ የካንሰር በሽታን መለየት ይችላሉ?

ጉንዳን

ጉንዳኖች ወደፊት ካንሰርን አነፍንፈው ሊደርሱበት የሚችሉ ነፍሳት እንደሚሆኑ አንድ ጥናት ጠቁሟል።

ይህ የሆነው ጉንዳኖች ከፍተኛ የሆነ የማሽተት ጸጋ ስለተሰጣቸው ነው ይላል ይኸው ጥናት።

ሳይንቲስቶች ባደረጉት የቅርብ ጊዜ ምርምር ጉንዳኖች በአይጦች ላይ ያለ በሽታን አነፍንፈው እንደደረሱበት አስተውለዋል።

“ጉንዳኖች በአይጥ ላይ ያለ ካንሰርን ከ10 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ አነፍንፈው መለየት ችለዋል” ይላሉ የጥናት ቡድኑ መሪ ባፕቲስቴ ፒኩሬት።

ባፕቲስቴ በጉንዳኖች ላይ ጥናታቸውን የጀመሩት በፈረንጆቹ 2017 ነበር።

መጀመሪያ ያደረጉት በላብራቶሪ የተዘጋጁ ጤናማ ሴሎች እና ካንሰር ሴሎች ለይቶ በማስቀመጥ ጉንዳኖች በሽታ እንዲለዩት ማሠልጠን ነበር።

አሁን ግን የጥናት ቡድናቸው ምርምሩን አንድ ደረጃ ከፍ በማድረግ በጉንዳኖች ላይ ሰፊ ጥናት ካደረጉ በኋላ፣ በአይጦች ላይ የሚገኝን የጭንቅላት ካንሰር እጢን ጉንዳኖቹ በፍጥነት አሽትተው መለየት ችለዋል።

የጥናት ቡድኑ ዜኖድራፍቲንግ (xenografting) የሚባል ዘዴን ለዚህ ጥናት ተጠቅሟል።

ይህም ከሰዎች ላይ የጡት ካንሰር ህዋሳትን ወደ አይጦች ሆን ብሎ እንዲዛመት በማድረግ ካንሰሩ በአይጦቹ ውስጥ እንዲስፋፋ ማድረግ ነው።

ከዚያ በኋላ ከጤነኛ አይጦች እና በካንሰር እንዲያዙ ከተደረጉ አይጦች የሽንት ናሙና ወሰዱ።

“ጉንዳኖቹን በማሰልጠኑ ሂደት በክብ ቱቦ ውስጥ በካንሰር ህዋሳት የተጠቁ አይጦችን ካሸተቱ በኋላ ለትጋታቸው ጉንዳኖቹ ምግብ እንዲሸለሙ አደረግን” ይላሉ ተመራማሪው።

በዚህ ዘዴ ጉንዳኖቹ የምግብ ስጦታውን ከካንሰር ህዋስ ጠረን ጋር ስላያያዙት በቀላሉ ካንሰርን መለየት ችለዋል።

“ህዋሳት ልክ እንደ ፋብሪካ ናቸው። ለመኖር አንዳች ግብአት ይፈልጋሉ፤ ከዚያ ደግሞ ዝቃጫቸውን ማስወገድ አለባቸው። የካንሰር ህዋሳት ደግሞ ዝቃጭ በጠረኑ ሊለይ የሚችል ነው” ይላሉ ፓቢቲስቴ።

ይህ ጥናት እንዳመላከተው የካንሰር ህዋሳት ስሪት ውህድ በትንፋሽ እና በሽንት መለየት የሚችል ነው።

ጉንዳኖቹ ታዲያ ይህን የካንሰር ጠረንን የመለየት አቅማቸው የመጣው ሴሉን ተከትሎ የሚበሉት ነገር ስለተቀመጠላቸው ብቻ አይደለም።

እንደ ምንዳ የሚሰጣቸው ምግብ ከቦታው ከተነሳ በኋላም በጠረን ካንሰር ሴልን የመለየት ሥራቸው አልቆመም።

ጉንዳን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ካንሰር ያለበትን ሰው በጠረኑ እንዴት ይለዩታል?

በእርግጥ ካንሰር ያለበትን ሰው ጉንዳኖች በጠረን መለየት ይችላሉ?

ተመራማሪው “ለጊዜው መለየት አይችሉም” ሲሉ ያስረዳሉ። “ለምን?” ሲባሉ ምክንያቶችን አፍታተው ያስረዳሉ።

ይህ የሆነበት ምክንያት አንደኛው የሰዎች ጠረን ሚሊዮን ዓይነት በመሆኑ ነው።

እያንዳንዱ ሰው ያለው ጠረን እንደ አሻራው ሁሉ የተለያየ ነው።

ሁለተኛ የሰው ሽንት እንደ አይጥ ሽንት ቀላል አይደለም። ውስጡ ብዙ ውህዶች አሉት። ይህ ደግሞ ነገሩን ለጉንዳኖች ውስብስብ ያደርግባቸዋል።

ጉንዳኖች በሰው ልጅ የካንሰር ህዋስን በጠረኑ እንዲያውቁት አዳጋች የሚያደርግባቸው ሌላው ጉዳይ የሰው እድሜ፣ ጾታ፣ የአመጋገብ ባህል መለያየት እና መሰባጠር ነው።

እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ጉንዳኖች ከሰው ልጅ የካንሰር ሴሎችን ነጥለው መለየት ይችላሉ ወይ የሚለው ነገር ገና ሰፊ ጥናት የሚሻ እንዲሆን አደርገውታል።

“ለጊዜው ማወቅ የቻልነው...” ይላሉ መሪ ተመራማሪው፣ “...ጉንዳኖች ከፍተኛ የሆነ ጠረንን የመለየት ልዩ ተሰጥኦን መታደላቸውን ነው።”

ይህ ደግሞ ጉንዳኖች በትንሽ ወጪ፣ በቀላል ሥልጠና ወደፊት የሰውን ጠረን አሽትተው የካንሰር ህዋሳትን መንጥረው መለየት እንዲችሉ ያደርጋል።

ሌላው መልካም ነገር ጉንዳኖች በጋራ የሚኖሩ እና መረጃን በፍጥነት የሚለዋወጡ መሆናቸው ነው።

“የሚደንቀው 10 ከመቶ የሚሆነውን የጉንዳን ሠራዊት በማሰልጠን ብቻ መላውን ጉንዳን ማዳረስ ይቻላል፤ ይህን የሚያስችለው ደግሞ ጉንዳኖች መረጃ መለዋወጥ ባህላቸው ስለሆነና እርስ በርሳቸው መረጃውን ለተቀሩት 90 ከመቶ ለሚሆኑት ጉንዳኖች ስለሚያዳርሱት ነው።”

ጉንዳን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የትኞቹ እንሰሳት እና ነፍሳት ካንሰር ህዋስን በጠረን ይለያሉ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከ10 ዓመት በፊት በሚቺጋን ዩኒቨርስቲ በተደረገ ጥናት አንበጣዎች ይህ አቅም እንዳላቸው ተደርሶበታል።

ይሁንና እንደ ጉንዳን ሰልጥነው ወይም ተገርተው አይደለም አንበጣዎች የካንሰር ህዋስን የሚለዩት።

አንበጣዎች ከጭንቅላታቸው ክፍል ህዋሱን እንዲለዩ ያስቻላቸውን ንዑስ ክፍል በመለየት ተመሳሳይ መሣሪያ ለመሥራት ሙከራዎች ነበሩ።

ይሁንና አንበጦች ብቻ አይደሉም ለዚህ ሙከራ የታጩት።

በዩናይትድ ኪንግደም ከፍተኛ የማሽተት አቅም ያላቸው የውሻ ዝርያዎችም የፕሮስቴት ካንሰርን የሚለይ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ተገጥሞላቸው የካንሰር ህዋስን እንዲለዩ በሙከራ ደረጃ እየተሠራበት ይገኛል።

የዚህ ጥናት መሪ የሆኑት ሶፊ አዚዝ እንዳሉት ውሾቹ የፊኛ ካንሰርን የሚለዩበት ሁኔታ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች አሉ።

ከካንሰር በሽተኞች የተገኙ የሽንት ናሙናዎችን መለየት ችልዋልም ብለዋል ለቢቢሲ።

ሌላ ጥናት ደግሞ የተወሰኑ የውሻ ዝርያዎች የማኅጸን ካንሰርን ከደም ናሙናዎች ውስጥ መለየት እንደቻሉ አመላክቷል።

አሁን ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ ኤሌክትሮኒክ አፍንጫዎች ውሾች ላይ በመግጠም ሙከራዎች እየተደረጉ ነው።

ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን መግጠም ያስፈለገበት ምክንያት ናሙና ውስጥ በርካታ ውህዶች ስላሉ የአነፍናፊ ውሾቹን አቅም በውህዱ ብዛት የተነሳ ወደተሳሳተ አቅጣጫ እንዳይሄድ ነው።

ውሾችን የካንሰር ህዋስ አነፍንፈው እንዲለዩ ለማስቻል ግን ሰፊ የሥልጠና ጊዜ እና ገንዘብ የሚፈልግ ሆኗል። ጉንዳኖች ተመራጭ የሆኑት ወጪው ዝቅተኛ ስለሆነም ጭምር ነው።

አዚዝ እንደሚሉት በሽታን በተመለከተ አንድ ሰው ሲታመም ጠረኑም እየተቀየረና እየተለየ ይመጣል፤ ይህም የታማሚው የተለያዩ ህዋሳት እና የበሽታ መከላካያ አቅም ርብርብ የሚፈጥረው ውህድ ጠረኑን ውስብስብ እንዲሆን ስለሚያደርገው ነው።

ምናልባት ወደፊት ጉንዳን፣ አንበጣ እና አነፍናፊ ውሾች በኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ታግዘው የካንሰር ህዋሳትን ልክ እንደ ኮኬይን ያለምንም የስህተት ሕዳግ መንጥረው ያወጡ ይሆናል።