የካንሰር ህዋስን የሚገድለው ቫይረስ ለካንሰር ሕሙማን ተስፋ እንደሚሰጥ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቫይረስ በመጠቀም የካንሰር ሕዋሳትን የሚገድለው ሕክምና ለካንሰር ሕሙማን ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ተገለጸ።
የዩናይትድ ኪንግደም ሳይንቲስቶች እንደሚሉት፣ በዚህ ሕክምና አንድ ካንሰር ታማሚ ሲፈወስ ሌላ ታማሚ ደግሞ ከፍተኛ ማገገም አሳይቷል።
ለሕክምና የዋለው ቫይረስ በዋናነት የጉሮሮ መከርከር የሚያስከትለው ኸርፕስ ሲምፕሊክስ ሲሆን፣ ቫይረሱ እንዲዳከም ተደርጎ ነው ጥቅም ላይ የዋለው።
በሕክምናው ዙሪያ ተጨማሪ ጥናቶች ቢያስፈልጉም፣ ለካንሰር ሕሙማን ተጨማሪ ዕድሜ የመስጠት ተስፋ እንዳለው ሳይንቲስቶች ገልጸዋል።
የ39 ዓመቱ ክሪስቶፍ ዎጂኮስኪ በሕክምናው የሙከራ ደረጃ ከተሳተፉ አንዱ ነው።
ምዕራብ ለንደን የሚኖረው ክሪስቶፍ በሮያል ማርስደን ኤንኤችኤስ ፋውንዴሽን ትረስት በሚገኘው የካንሰር ምርምር ማዕከል ለምርምር በጎ ፈቃደኛ ሆኗል።
እአአ በ2017 ነበር የምራቅ አመንጪ ሕዋስ ካንሰር እንዳለበት የተነገረው።
ቀዶ ሕክምና ቢደረግለትም አልተሻለውም።
“የመኖር ተስፋ የለህም ተብዬ ነበር። የሕይወት ማገባደጃ እንክብካቤ እየተደረገልኝ ነበር። እጅግ ልብ ይሰብራል። አሁን ግን ተስፋ የሚሰጥ ምርምር ውስጥ መግባቴ ተስፋ አጭሮብኛል” ብሏል።
የካንሰር ሕዋሳትን የሚገድለው ቫይረስ ሙከራ ከተደረገለት በኋላ ክሪስቶፍ ካንሰሩ ጠፍቶለታል።
ለተከታታይ አምስት ሳምንታት በየሁለት ሳምንቱ መርፌ ይሰጠው ነበር።
ሰውነቱ ውስጥ ያለው በካንሰር የተጎዳ ሕዋስ ላይ አነጣጥሮ ነው ቫይረሱ የሚሠራው።
ይህም በሽታ የመከላከል አቅሙ እንዲዳብር አግዟል።
በሙከራ ደረጃ አርፒ2 የተባለውን ቫይረስ በመርፌ ይወስዱ የነበሩት 40 ሰዎች ናቸው።
ከመካከላቸው ከመርፌው በተጨማሪ ኒቮሎማብ የተባለ የካንሰር መድኃኒት በተጨማሪ ሲሰጣቸው የነበሩም ይገኙበታል።
ክሪስቶፍን ጨምሮ አርፒ2 ከተሰጣቸው ዘጠኝ ሕሙማን ሦስቱ ሰውነታቸው ውስጥ ያለው ካንሰር ተመናምኗል።
አርፒ2 መርፌን ከኒቮሎማብ መድኃኒት ጋር አጣምረው ከወሰዱ 30 ሰዎች ሰባቱም አገግመዋል።
እንደ ድካም ያሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች ውስን ነበሩ።
ዋና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ኬቨን ሀሪንግተን ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ የምርምሩ ውጤት “እጅግ አስደናቂ” ነው።
በተለያየ የካንሰር ደረጃ ላይ ላሉ ሕሙማን ተስፋ ሰጭ እንደሆነ አክለዋል።
ሕክምናው እምብዛም ለማይታየው የዐይን ካንሰር እና የኢሶፎገስ ካንሰር እንደሚውልም ተመራማሪው ተናግረዋል።
“በሕክምና ምርምር የመጀመሪያ ደረጃ እንዲህ ያለ ተስፋ ሰጭ ውጤት ማግኘት አልተለመደም። በርካታ የካንሰር ሕሙማንን ማከም ስንጀምር ምን ውጤት ልናገኝ እንደምንችል እስከማይ ጓጉቻለሁ” ብለዋል።
ዶ/ር ማሪን ቤከር የተባሉት የካንሰር ተመራማሪ፣ የካንሰር ሕክምና አንድ ደረጃ ከፍ እንዲል ያገዘ ጥናት መሆኑን ተናግረዋል።
“ሳይንቲስቶች ቫይረስን ተጠቅመው ካንሰርን መዋጋት እንደሚችሉ የደረሱበት ከ100 ዓመታት በፊት ነበር። ነገር ግን ደኅንነቱ በተጠበቀና በውጤታማ መንገድ ሕክምናውን ማስኬድ ቀላል አልሆነም። ይህ አዲሱ ሕክምና በጥቂት ሰዎች ሲመረመር ተስፋ ፈንጥቋል። ወደ ሰፊ ምርምር ማደግ አለበት” ሲሉ አስረድተዋል።
ሳይንቲስቶች ቫይረስ ተጠቅመው ካንሰርን ለመዋጋት ሲሞክሩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።
ከዚህ ቀደም የቆዳ ካንሰርን ለማከም ቫይረስ ጥቅም ላይ የሚውልበት ሕክምና ፈቃድ ተሰጥቶታል።












