'ሲጋራ አላጨስም፤ ነገር ግን የሳንባ ካንሰር ይዞኛል -ለምን?'

የተጨሰ ሲጋራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አቶ ላቀው ገብረሥላሴ በደብረ ብርሃን፣ የጭራሮ ደብር ገበሬ ማኅበር ነዋሪ ናቸው።

እድሜያቸው ስልሳዎቹ ውስጥ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ላቀው፣ የሁለት ወንዶች እና የአንዲት ሴት አባት ናቸው።

አቶ ላቀው እንደ ቀልድ የጀመራቸው ሳል እየበረታ ሲመጣ ወደ ደብረ ብርሃን ሆስፒታል አምርተዋል።

የሕክምና ባለሙያዎቹም የሳንባ በሽታ [ቲቢ] ነው በሚል መድኃኒት አዘውላቸው ሲወስዱ ቆዩ።

ነገር ግን ሕመማቸው ከመሻሻል ይልቅ እየባሰበት መሄዱን ያስታውሳሉ።

“በተደጋጋሚ ታይቸዋለሁ፤ ነገር ግን ምንም ሕመሜን የሚያውቅልኝ አልነበረም። ያስለኛል . . .አክታዬ ደም ነበረው” ይላሉ በወቅቱ ሆስፒታል የሄዱበትን ምክንያት ሲያስታውሱ።

በወቅቱ ደብረ ብርሃን ሆስፒታል የሚገኙ እና አቶ ላቀውን የመረመሩ የሕክምና ባለሙያዎችም ከቲቢ የተለየ ነገር ይኖራል ብለው አላሰቡም።

የአቶ ላቀው ጤና ግን ከመሻሻል ይልቅ እያሽቆለቆለ መጣ።

ያኔ ነው ለተሻለ ሕክምና በሚል ወደ አዲስ አበባ፣ ዘውዲቱ ሆስፒታል የተላኩት።

ሲጋራ ያጨሳሉ እንዴ አቶ ላቀው? ስንል ጠይቀናቸው “አረ ገበሬ ነኝ አላጨስም” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል።

ይህን ጥያቄ ግን አዲስ አበባ ከመጡ በኋላም የሕክምና ባለሙያዎቹም ጠየቀዋቸዋል።

አስፈላጊው ምርመራ ሁሉ ከተደረገላቸው በኋላ በሳንባ ካንሰር መያዛቸው ስለተረጋገጠ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተልከዋል።

አቶ ላቀው 'ሲጋራ ሳላጨስ እንዴት ሳንባ ካንሰር ያዘኝ' የሚለው ጥያቄያቸው ግን እስካሁን መልስ ያላገኙለት ነው።

የካንሰር ስፔሻሊስት እና በበሽታው ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን በመስራት ላይ የሚገኙት ዶ/ር ጂልቻ ድሪባ፣ “በካንሰር ላለመያዝ መፍትሄው አለመወለድ ነው የሚባል ነገር አለ” ይላሉ።

ብዙ ዓይነት ካንሰሮች ከተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች ይነሳሉ የሚሉት ዶ/ር ጂልቻ፣ የሳንባ ካንሰርም በዓለም ላይ ከቆዳ ካንሰር ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚከሰት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ወደ ሰሜን ዋልታ አካባቢ ከፀሐይ ጨረር የተነሳ የቆዳ ካንሰር በስፋት በመከሰቱ ቀዳሚው ነው።

ያንን ተከትሎም በሁለተኛ ደረጃ ላይ ያለው የሳንባ ካንሰር ነው።

በመከሰት ደረጃ ሁለተኛ ይሁን እንጂ በገዳይነቱ ደግሞ በዓለም ላይ ቀዳሚው የካንሰር ዓይነት ነው።

በኢትዮጵያም የሳንባ ካንሰር በወንዶች ላይ በመከሰት ዘጠነኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የካንሰር ዓይነት ነው።

ሕይወትን በማጥፋት ግን በወንድም በሴትም ላይ ሲታይ በስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የሳንባ ካንሰር በዋነኛው የመተንፈሻ አካላችን ላይ የሚነሳ የካንሰር ዓይነት ነው።

የሳንባ ካንሰር የሚያሳይ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

መንስኤው ምን ይሆን?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከሳንባ ካንሰር ጋር ተያይዞ በቀዳሚነት የሚነሳው ሲጋራ ማጨስ ነው። ለዚህም ነው አቶ ላቀው ከእኛም ሆነ ከሕክምና ባለሙያዎቹ “ያጨሳሉ እንዴ?” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው።

ከማጨስ ጋር ተያይዞ ደግሞ ሲጋራን ከሚያዘወትሩ ሰዎች ጋር አብረው የሚኖሩ ወይንም በቅርበት የሚሰሩ ሰዎች (ፓሲቭ ስሞከርስ) የሚባሉ መኖራቸወን ዶ/ር ጂልቻ ድሪባ ይናገራሉ።

አጫሾች በጣም ጎጂ የሚባለውን የሲጋራውን ጭስ ወደ ውጪ ነው የሚተነፍሱት።

በዚህ መሀል በጣም ተጎጂ የሚሆኑት በአቅራቢያቸው የሚገኙና ያንን ጭስ ወደውስጣቸው የሚያስገቡ ሰዎች ናቸው።

የዓለም ጤና ድርጅት ሁሉም ዓይነት ሲጋራዎች ጎጂ እንደሆኑ ሁሌም ያሳስባል።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በማንኛውም የጤንነት ሁኔታ ላይ የሚገኙ ለጭሱ የሚጋለጡ ሰዎችም ተጎጂዎች ይሆናሉ።

በዓለም ጤና ድርጅት የአውሮፓ ቢሮ የትንባሆ ቁጥጥር ባለሙያ የሆኑት አንጄላ ቺባኑ እንደሚሉት፣ የማያጨሱ ሰዎች ለአንድ ሰዓት ያህል ለሲጋራ ጭስ ቢጋለጡ በተለይ በጉሮሯቸው አካባቢ ቀላል የማይባል ጉዳት ይደርስባቸዋል።

አክለውም “ከሌሎች ሰዎች ለሚመጣ የሲጋራ ጭስ የሚጋለጡ ሰዎች ከ700 በላይ ኬሚካሎችን ወደ ውስጣቸው ያስገባሉ። ከእነዚህ ኬሚካሎች መካከል ደግሞ 70 የሚሆኑት ለካንሰር የሚያጋልጡ ናቸው። እነዚህ ሰዎች በሳንባ ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ከ20 እስከ 30 በመቶ ከፍ ያለ ነው” ይላሉ ባለሙያዋ።

የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ 65 ሺህ የሚሆኑ ህጻናት በየዓመቱ በሲጋራ ምክንያት ህይወታቸው እንደሚያልፍ ይገልጻል።

ዶ/ር ጂልቻም በቤት ውስጥ የሚያጤስ ሰው ካለ ልጆች እና የትዳር አጋር ለሳንባ ካንሰር እንደሚጋለጡ ይናገራሉ።

በሥራ ቦታ ደግሞ የሥራ አጋር የሚያጤስ ከሆነ በአካባቢው አዘወትረው የሚገኙ ሰዎች በሳንባ ካንሰር የመያዘ ዕድል አላቸው።

ከዚያ ውጪ ይላሉ ዶ/ር ጂልቻ የተለያዩ ኬሚካሎች ከሳንባ ካንሰር ጋር በቀጥታ የሚገናኙ አሉ።

“በተለይም አስቤስቶስ የሚባል ኬሚካል አለ፣ ራደን፤ እነዚህ ለብዙ ዓመታት ሲፈታተኑን የኖሩ ናቸው፤ አሁንም በዚያው ደረጃ ነው ያሉት። በተለይ ራደን ከዚህ ቀደም ሰዎች ባለማወቅ ለማዕድን ማውጣት ይጠቀሙት ስለነበር ተጋላጭ ሆነው ቆይተዋል።”

ስለዚህ በቤት ግንባታ እና በማዕድን ማውጣት ላይ የተሰማሩ ሰዎች ለእነዚህ ኬሚካሎች በመጋለጣቸው የተነሳ ተጠቂ ይሆናሉ።

ይህ ብቻ ሳይሆን ከእነዚህ ኬሚካል ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎችም ለሳንባ ካንሰር ይጋለጣሉ።

የተለያዩ ፋብሪካዎች ውስጥ የሚገኙ እንደ ሲልካ (silica)፣ ካድሚየም (cadmium)፣ አርሰሚክ (Arsenic)፣ ቤንዚደን (benzidine) . . .የድንጋይ ከሰል ለሳንባ ካንሰር በብዛት ተጋላጭ የሚያደርጉ ኬሚካሎች ናቸው።

የማያጨሱ ወንዶች እና ሴቶች ላይ የሳንባ ካንሰር እንደሚከሰት የገለፁት ባለሙያው ይህም የሚሆነው ከዘረመል እክል (ጄኔቲክ ሚውቴሽን) ጋር ተያይዞ መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህ ውጪ የሳንባ በሽታ በተደጋጋሚ የሚያጠቃቸው ሰዎች፣ ጠባሳ ሳንባቸው ላይ ትቶ ስለሚያልፍ ለሳንባ ካንሰር ይጋለጣሉ።

በዓለም ዙርያ ትምቧሆ አጠቃቀም

የሳንባ ካንሰር ምልክቶች የትኞቹ ናቸው?

ዶ/ር ጂልቻ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ በሚሰሩበት ወቅት የሳንባ ካንሰር ተይዘው የሚመጡ በርካታ ሰዎች የቲቢ መድኃኒት ሲወስዱ ቆይተው እንደሚመጡ አስተውለዋል።

“ይህ ማለት ምንድን ነው፣ ቲቢ ሳይሆን ቲቢ ነው ተብለው በአካባቢያቸው የታከሙበት ሁኔታ መኖሩን ነው። ወይንም ደግሞ እንደ ኒሞኒያ ያሉ ቀላል ሕመሞች ነው በሚል ሲታከሙ ቆይተዋል ማለት ነው።”

የሳንባ ካንሰር የያዘው ሰው በዋናነት የሚያሳየው ምልክት ሳል ሲሆን፣ የትንፋሽ መቆራረጥ፣ ማፈን ስሜቶች ይስተዋላሉ።

የሳንባ ካንሰር እንደ ተከሰተ ሳሉ እንደማይጀምር ዶ/ር ጂልቻ ያስረዳሉ።

  • ከአክታ ጋር የተቀላቀለ አልያም ንፁህ ደም መትፋት
  • የደረት ህመም
  • የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ የሰውነት ክብደት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ
  • የዕለት ተዕለት ሥራቸውን በአግባቡ መከወን አለመቻል ከሚስተዋሉ ምልክቶች መካከል ናቸው።
  • ·የሳንባ ካነሰር ደረጃው ከፍ እያለ በሚመጣበት ወቅት ደግሞ ድምጽ የመቀየር፣ የመጎርነን ምልክት ይኖራቸዋል።

ሳንባ ካንሰር ወደ አድሪናል እጢ፣ ወደ አንጎል፣ ወደ አጥንት የመሰራጨት ዝንባሌ ስላለው፣ እንደ ተሰራጨበት የአካል ክፍል ተጨማሪ ምልክቶችም ይስተዋላሉ።

ሲጋራ ሚያጤስ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሳንባ ካንሰርን ለመከላከል

ከተለያዩ የካንሰር ዓይነቶች በተለየ የሳንባ እና የማሕፀን በር ካንሰር አምጪ ነገሮች ተለይተው ይታወቃሉ።

በዚህ የተነሳ የሳንባ ካንሰርን ለመከላከል ሲጋራ የሚያጤሱ ሰዎች እንዲያቆሙ ይመከራሉ።

ሲጋራ የሚያጤስ ሰው አካባቢ አለመኖር፣ ወደ ፋብሪካዎች እና ወደ ቤት የምናመጣቸውን ኬሚካሎች ይዘት ማንበብ ተገቢ ነው።

በቤት ውስጥ፣ በአካባቢ እንዲሁም በፋብሪካ ውስጥ የሚገኙ ኬሚካሎች ከሳንባ ካንሰር ጋር ተዛማጅነት ስላላቸው ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

ዶ/ር ጂልቻ በሕክምና ላይ ያጋጠሟቸውን ሕሙማን በማስታወስ ኢትዮጵያ ውስጥ ፋብሪካዎች ምን ዓይነት የኬሚካል ግብዓት እንደሚጠቀሙ እንዲከታተል፣ ሠራተኞችም ራሳቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ እንዲያነብቡ ይመክራሉ።

በፋብሪካ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችም፣ ከፋብሪካ የሚወጡ ፍሳሾች ለጤናቸው አደጋ ስለሚኖራቸው በንቃት መከታተል እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

ሳንባን ብዙ ሕመም ሲያጠቃው ጠባሳ ከፈጠረ ወደ ካንሰር ሊቀየር ስለሚችል በተገቢው ጊዜ የሕክምና ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ነው።

‘ካንሰር መዳን የሚችል በሽታ ነው’

አቶ ላቀው ገብረ ሥላሴ ከደብረ ብርሃን አዲስ አበባ እየተመላለሱ ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ነው።

እስካሁን ድረስ ለስድስት ጊዜ ያህል ኬሞቴራፒ ወስደዋል፤ አሁን ደግሞ ጨረር ሕክምና እየወሰዱ ነው።

የካንሰር ሕክምናውን ከጀመሩ በኋላም ጤናቸው እየተሻሻለ መሆኑን ይገልጻሉ።

“ካንሰርም መታከም ይችላል፤ የሳንባ ካንሰርም መታከም ይችላል” ያሉት ደግሞ ዶ/ር ጂልቻ ናቸው።

ዶ/ር ጂልቻ አሁን ባለው ቴክኖሎጂ ካንሰር መዳን የሚችል በሽታ ነው ይላሉ።

በርካታ ሰዎች ስለካንሰር ሲነሳ ገዳይነቱ ብቻ ነው የሚመጣለት የሚሉት ባለሙያው፣ በዓለም ደረጃ ሁለት ሦስተኛውን ካንሰር ሙሉ በሙሉ ማዳን ይቻላል ይላሉ።

በእኛ አገር ደረጃ ግን እዚህ ደረጃ ላይ አለመድረሳችንን ዶ/ር ጂልቻ ያነሳሉ።

የሕክምና መስጫ ስፍራዎች እድገት፣ የባለሙያዎች ብቃት፣ የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት፣ የመድኃኒት አቅርቦት ክፍተት መኖራቸውን ይዘረዝራሉ።

የሳንባ ካንሰር ሕክምና የመጀመሪያ፣ መካከለኛ እና በጣም ደረጃው ከፍ ያለ በሚል እንደሚለያይም ይናገራሉ።

በመጀመሪያ ደረጃ ያለ የሳንባ ካንሰር በቀዶ ሕክምና ካንሰሩን ቆርጦ በማውጣት ሙሉ በሙሉ ማዳን ይቻላል።

ቀዶ ሕክምና ማድረግ በማይቻልበት ሁኔታ ላይ ደግሞ የጨረር ሕክምና መኖሩን ዶ/ር ጂልቻ ገልፀዋል።

በመካከለኛ ደረጃ ያለ የካንሰር ዓይነት ደግሞ በኬሞ ቴራፒ፣ በቀዶ ሕክምና እንዲሁም ጨረር መጠቀም መከምና ማዳን ይቻላል።