የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የፕሬስ ኃላፊ መታሰራቸውን ቢቢሲ አረጋገጠ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ የሆኑት ገብሩ ካህሳይ

የፎቶው ባለመብት, Gebru Kahsay Kiflu/Facebook

የምስሉ መግለጫ, የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ የሆኑት ገብሩ ካህሳይ
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ የሆኑት ገብሩ ካህሳይ (ዶ/ር) በቁጥጥር በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተሰማ።

የፕሬስ ኃላፊው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰኞ ግንቦት 3/2018 ዓ.ም. ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ መሆኑን ቢቢሲ ከቤተሰቦቻቸው ማረጋገጥ ችሏል።

በመቀለ ከተማ ሃድነት ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው የሚገኙት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የፕሬስ ኃላፊ በቁጥጥር ስር የዋሉት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሠረት መሆኑ ተነግሯል።

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት የፈረሰው የትግራይ ክልል የቀድሞ ምክር ቤት ከተመረጠ ከስድስት ዓመት በኋላ ተሰብስቦ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በፕሬዝዳንትነት መሰየሙ ይታወሳል።

በዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ካቢኔ ስብሰባ ማድረግ የጀመረ ሲሆን፣ ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ የጊዜያዊ አስተዳደሩ "ሥልጣን በጉልበት እየተያዘ" መሆኑን በመግለጽ ድርጊቱን ኮንነዋል።

ገብሩ ካህሳይ (ዶ/ር) ባለቤት ወ/ሮ ወርቃለም አረጋው አራት የፖሊስ አባላት ሰኞ ምሽት 2 ሰዓት አካባቢ ወደ ቤታቸው በመምጣት ፍተሻ ማካሄዳቸው ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ባለቤታቸውን የክልሉ ፖሊስ ለምን በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው እንደማያውቁ ገልጸው "እኔ ምንም የማውቀው ተዓምር የለም። አሁን በሃድነት ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ ይገኛል። እዚያ እንደወሰዱት ዛሬ ነው ያወቅኩት። ትናንት [ሰኞ ዕለት] ሊያናግሩኝም አልቻሉም ነበር። ምን አጥፍቶ ነው የፈለጋችሁት ስላቸው 'እናጃባትሽ' ብለው ሲሰድቡኝ ነበር" ብለዋል።

የፕሬስ ኃላፊው በቁጥጥር ሥር የዋሉት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋሩት ጽሑፍ የተነሳ መሆኑንም ፖሊስ አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ነገር ግን ኃላፊው በቁጥጥር ሥር የዋሉት በግል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባጋሩት መረጃ ይሁን ወይንም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ገጽ ላይ በወጣ ልጥፍ ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም።

ፖሊስ አጋርተውታል ስለተባለው መረጃ ይዘትም በይፋ ያለው ነገር የለም።

ነገር ግን የተመሠረተባቸው ክስ "በማኅበራዊ ሚዲያ ሐሰተኛ መረጃን በማሠራጨት" የሚል እንደሆነ የፖሊስ ሰነድ ያመለክታል።

የዶ/ር ገብሩ ወዳጆች እና ቤተሰቦች ዛሬ እስር ቤት ሄደው አንደጠየቋቸው እና ምግብ እና ውሃ እንዳቀበሏቸው ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።

አስተየየታቸውን የሰጡ አንድ ስማቸው አንዳይገለጽ የጠየቁ የቤተሰብ አባል ፖሊስ ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር ያዋለው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋሩት ጽሑፍ የተነሳ መሆኑን እንደነገሯቸው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ከቅርብ ቀናት ወዲህ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በጊዜያዊ አስተዳደሩ እና በፕሬስ ኃላፊው ላይ ህወሓት የተለያዩ እርምጃዎችን እንዲወስድ የሚቀሰቅሱ ጽሑፎች ሲጋሩ ነበር።

ቢቢሲ የፕሬስ ኃላፊው ገብሩ ካህሳይ በሃድነት ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን እና ረቡዕ ዕለት ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ማረጋገጥ ችሏል።

አቶ ገብሩ ከዚህ ቀደም በትግራይ ኤፍኤም 104 የሬዲዮ ጣቢያው ኃላፊ እንዲሁም የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ በመሆን ሠርተዋል።

በህወሓት እና ሥልጣናቸው ለአንድ ዓመት በተራዘመላቸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች መካከል ከፍተኛ ውጥረት ተቀስቅሷል።

ህወሓት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥልጣን መራዘምን የፕሪቶሪያ ስምምነትን የጣሰ ነው በማለት መቃወሙ ይታወሳል።

የፌደራል መንግሥት ሕገ ወጥ በሚል ውድቅ ባደረገው ምርጫ የተመረጠውን የትግራይ ክልል ምክር ቤት ወደ ሥራ የመለሰው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፤ ዶ/ር ደብረፂዮንን የክልሉ ፕሬዝዳንት አድርጎ መርጧል።

ከስድስት ዓመት በፊት በተደረገው እና ፌደራል መንግሥት ሕገ ወጥ ባለው ምርጫ የተቋቋመው ምክር ቤት ስብሰባዎችን ማድረግ ጀምሯል።

በክልሉ አዲስ ርዕሰ መስተዳደር የተሾመው የፌደራል መንግሥት ለአንድ ዓመት ሥልጣናቸውን ያራዘመላቸው ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ በመሪነት ሥፍራቸው እንዳሉ ነው።

ይህም በትግራይ ክልል ውስጥ በሌ/ጄነራል ታደሰ የሚመራ በፌደራል መንግሥቱ ዕውቅና ያለው ጊዜያዊ አስተዳደር እና በዶ/ር ደብረ ጽዮን የሚመራ አስተዳደር እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

የህወወሓት መሪዎች እንዲፈርስ የተደረገውን ምክር ቤት መልሰው በመሰብሰብ ፕሬዝዳንት መምረጣቸውን በተመለከተ እስካሁን በይፋ ያለው ነገር የለም።

ሕጋዊ ዕውቅናው በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰረዘበት ህወሓት በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ ምዝገባ የሌለው ሲሆን፣ ከፓርቲው ከፍተኛ አመራሮቹን ጨምሮ አባላቱ በመውጣት የተለያዩ ፓርቲዎችን አቋቁመዋል።