ለ20 ደቂቃ በመናፈሻዎች ውስጥ መንሸራሸር ለጤና ያለው ጥቅም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በመናፈሻ ውስጥ ወይም በጫካ ውስጥ ከተንሸራሸሩ በኋላ መረጋጋት ከተሰማዎት፣ ይህ በሃሳብዎ የፈጠሩት አይደለም ፤ ሥነ ሕይወት ነው።
ከቤት ውጭ መሆን የጭንቀት ሆርሞኖችን በመቀነስ፣ የደም ግፊትን ከማቃለል አልፎ ተርፎም የሆድ እቃ ጤናን በማሻሻል በሰውነትዎ ውስጥ ሊታይ የሚችል ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።
እነዚህን ጥቅሞች ለማግኘት ለሰዓታት የእግር ጉዞ ማድረግ አያስፈልግም፤ የቀንዎን 20 ደቂቃ ለዚህ ተግባር ቢያውሉ ለውጡን ያዩታል።
ስለዚህ በምሳ ሰዓት ወደ መናፈሻ ቦታ በመሄድ ለ20 ደቂቃ ያህል ዞር ዞር ማለት ሰውነትዎን እና አእምሮዎን ሊጠቅም ይችላል።
በተፈጥሮ መካከል በመሆን ጤናዎን ለማሻሻል የሚረዱ አራት መንገዶች እነሆ።
1. ሳይታወቅዎ ዘና ይላሉ
አረንጓዴ ዛፎችን ሲመለከቱ፣ የባሕር ዛፍ ሽታ እና የሚንኮሻኮሹ ቅጠሎች ወይም የወፎች ዝማሬ ድምፅ ሲሰሙ ኢ-ንቁ የሆነውን የአእምሮ ሂደቶች የሚቆጣጠረው የአውቶኖሚክ የነርቭ ስርዓትዎ ወዲያውኑ ምላሽ ይሰጣል።
ይህ በአካባቢው በሚገኝ መናፈሻ ስፍራ ጉብኝት እያደረጉ ባለበት ወቅት ሊከሰት ይችላል።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የብዝሃ ሕይወት ፕሮፌሰር የሆኑት ባሮነስ ካቲ ዊሊስ "እንደ የደም ግፊት መቀነስ እና የልብ ምት መለዋወጥ የመሳሰሉ በሰውነት ላይ ለውጦችን እናያለን፤ ስለዚህ ልብዎ ቀስ ብሎ ይመታል ማለት ነው" ብለዋል።
ወደ 20,000 የሚጠጉ ሰዎችን ያሳተፈ አንድ የዩናይትድ ኪንግደም ጥናት እንዳመለከተው በየሳምንቱ ቢያንስ 120 ደቂቃዎችን በአረንጓዴ ሥፍራዎች ያሳለፉ ሰዎች ጥሩ ጤንነት እና ከፍተኛ የሥነ ልቦና ደህንነትን የማሳየት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።
በአረንጓዴ ሥፍራ በተፈጥሮ ተከብቦ ጊዜን ማሳለፍ የሚያስገኘው ጥቅም ላይ አሳማኝ እና በቂ ማስረጃ በመኖሩ የተነሳ አንዳንዶች 'አረንጓዴ አካባቢ ማሳለፍን' እንደ መፍትሄ እያዘዙ ነው።
ይህም ማለት ሰዎችን ከተፈጥሮ ጋር በማገናኘት አካላዊ እና አእምሮአዊ ጤንነታቸው እንዲሻሻል እና በደስታቸው እና ደህንነታቸው ላይ አዎንታዊ ተፅእኖ እንዲያመጣ ማድረግ ነው።
2. ሆርሞንዎ ይጨምራል
በመዝናናት ሂደት ውስጥ የሰውነትዎ የሆርሞን ስርዓትም መሻሻል ያሳያል።
ዊሊስ ከቤት ውጭ ጊዜ ማሳለፍ በጭንቀት ወይም ውጥረት ጊዜ የሚበዙ ሆርሞኖች የኮርቲሶል እና አድሬናሊን መጠን ይቀንሳል ይላሉ።
"በሆቴል ክፍል ውስጥ ለሦስት ቀናት ያህል ሂኖኪ (ጃፓን ሳይፕረስ የሚገኝ) ዘይት እየተነፈሱ የተቀመጡ ሰዎች በአድሬናሊን ሆርሞናቸው ላይ ትልቅ መሻሻል እና በተፈጥሮ በሽታን ለመከላከል የሚያግዙ ሴሎቻቸው ውስጥ ትልቅ ጭማሪ እንዳሳዩ አንድ ጥናት አረጋግጧል።"
በተፈጥሮ በሽታ የሚከላከሉ ሴሎች በሰውነት ውስጥ ቫይረሶችን የሚቋቋሙ ሴሎች ናቸው።
የጥናቱ ተሳታፊዎች ከዛፉ የተወሰደን ሽታ ካሸተቱ ከሁለት ሳምንታት በኋላ በሰውነታቸው ውስጥ የእነዚህ ሴሎች ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር ጨምሯል።
በመሠረቱ ተፈጥሮ "ማረጋጋት የምትፈልገውን ታረጋጋለች እና ማጠናከር የሚያስፈልገውን ደግሞ ታጠናክራለች" ሲሉ የኢሊኖይ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ሚንግ ኩኦ ለቢቢሲ ጠቅለል አድርገውታል ።
"በመናፈሻዎች እና በጫካ ውስጥ የሳምንቱ የመጨረሻ ቀናትን ማሳለፍ በቫይረስ መከላከያ መንገዶቻችን ላይ ትልቅ ተፅእኖ አለው። እናም ከአንድ ወር በኋላ እንኳን ከመሠረታዊ ደረጃ 24 በመቶ በላይ ሊሆን ይችላል።"
በእነዚህ ስፍራዎች ለአጭር ጊዜያት ያሳለፉ ሰዎችም ቢሆኑ ጥናቶች አነስተኛ ግን ቀጣይ የሆነ ተፅእኖ መኖሩን ያሳያሉ ብለዋል።
3. ማሽተት ያለው ጠንካራ ጉልበት
ተፈጥሮን ማሽተት እንደማየት እና እንደመስማት ኃይለኛ ነው።
የዛፎች እና የአፈር ጠረን ከእጽዋት በሚለቀቁ ኦርጋኒክ ውህዶች የተሞላ እና "ሲተነፍሷቸው፣ አንዳንድ ሞለኪውሎች ወደ ደም ውስጥ ይገባሉ።"
ዊሊስ የጥድ ሽታን በ20 ሰከንድ ውስጥ መረጋጋት የሚያስገኝ ሲሆን ውጤቱ ለ10 ደቂቃ ያህል ይቆያል ሲሉ በመልካም አስረጅነት ይጠቅሱታል።
ተፈጥሮ ዘና የምታደርግበት መንገድ በአእምሯችን ውስጥ እንዳለ ልናስብ እንችላለን።
ነገር ግን ሌላ ጥናት እንዳመለከተው ከልዩ ሽታ ጋር ተያያዥነት ያለው ትዝታ የሌላቸው በጣም ጨቅላ ሕፃናት እንኳን ባሉበት ክፍል ውስጥ የጥድ ጠረን ሲረጭ መረጋጋት ታይቶባቸዋል።
4. ወደ ሆድ እቃችን ጥሩ ባክቴሪያ አንዲገባ ያግዛል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አእምሮዎን ከማረጋጋት በተጨማሪ አፈር እና ተክሎች በጥሩ ባክቴሪያዎች የተሞሉ በመሆናቸው የማይክሮብስ ስብስብዎን ከፍ ለማድረግ ይረዳሉ።
ዊሊስ "በፕሮቢዮቲክስ ወይም በመጠጥ ከፍለን የምናገኛቸው ዓይነት ጥሩ ባክቴሪያዎች ናቸው" ሲሉ ይገልጿቸዋል።
ፕሮፌሰር ሚንግ ኩዎ እንደ የኢንፌክሽን ተጋላጭነት እና የአእምሮ ጤና ባሉ ሁኔታዎች ላይ ያለውን ተጽእኖ ያጠኑ ሲሆን የተወሰኑትን ወደ ውስጥ መተንፈስ ስሜትን ከፍ የማድረግ አቅም አለው ብለዋል።
እንዲሁም በእጽዋት የሚለቀቁ ፀረ-ተህዋሲያን ኬሚካሎች (phytoncides) በሽታን ለመቋቋም ይረዳሉ።
ዶ/ር ክሪስ ቫን ቱሌከን እንደ ኢንፌክሽኑ ሳይንቲስት ሁሉ ተፈጥሮን እንደ አዎንታዊ አካባቢ ይመለከቷታል። "የሰውነታችን በሽታ የመከላከል ስርዓትን የሚኮረኩሩ" ናቸው ሲሉ ይገልጹታል።
ልጆቻቸውን በጫካ ውስጥ በቆሻሻ እንዲጫወቱ በማድረግ በመተንፈሻ አካል ስርዓታቸው እነዚህን መልካም ባክቴሪያዎች እንዲስቡ እንደሚያደርጉም የግል ልምዳቸውን ጠቅሰው ይናገራሉ።
ተፈጥሮን ወደ ራስዎ ይጥሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እያንዳንዱ ሰው ወደ ጫካ መሄድ አይችልም። መልካሙ ዜና የግድ መሄድ አያስፈልግዎም የሚለው ነው።
እንደ ዊሊስ አባባል በቤት ውስጥ ያለ ትንሽ ከተፈጥሮ ጋር ንክኪ እንኳን ለውጥ ያመጣል።
እንደ ነጭ ወይም ቢጫ ጽጌረዳ አበባዎች ማየት በአንጎል እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛውን የመረጋጋት ስሜት ይፈጥራሉ።
ወደ ማሽተት ሲመጣ ደግሞ፣ እንደ ላቬንደር ያሉ ዘይቶች ቤት ውስጥ መንፋት፤ ማጨስ ዘና ለማለት ይረዳል።
ይህ ሁሉም ካልተሳካ ግን፣ የጫካ ፎቶ ሊረዳ ይችላል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት የተፈጥሮን ምስሎች በላፕቶፕዎ ላይ መመልከት ወይም በቀላሉ አረንጓዴ ነገር መመልከት ተመሳሳይ የሚያረጋጋ የአዕምሮ ሞገድ ለውጥ እንደሚያመጣ እና ጭንቀትን እንደሚቀንስ ያሳያል።
ፕሮፌሰር ሚንግ ኩኦ "እያንዳንዱ ትንሽ ነገር የሚረዳ ይመስላል" ብለዋል።















