ልጣጫቸውን ልንመገባቸው ሲገባ የምንጥላቸው ፍራፍሬዎች

የሙዝ ልጣጭ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሳይንሱ እንዲህ ይላል። የሙዝ እና የብርቱካን ልጣጭ ሊጣል አይገባም። ሌሎችም ፍራፍሬዎች እና አትክልቶች ልጣጫቸው ጥቅሙ ያመዝናል።

እርግጥ ነው የሙዝ ልጣጭ መብላት የተለመደ አይደለም። ነገር ግን ብዙዎቻችን ይህን ነው የምናደርገው። የሙዝ ልጣጫ አንድ ሦስተኛው ክፍሉ ነው።

የሙዝ ልጣጭ ልክ እንደ አብዛኛዎቹ ፍራፍሬዎች እና አትክልት የሚበላ ብቻ ሳይሆን ጠቃሚ ንጥረ ነገር የያዘ ነው። ለምሳሌ የአንድ ብርቱካን 20 በመቶው ልጣጩ ነው።

አንድ በአውሮፓውያኑ 2018 የተሠራ ጥናት እንደሚጠቁመው 15.1 ሚሊዮን ቶን የሚመዝን የብርቱካን ልጣጭ ምግብ መሆን ሲገባው ቆሻሻ ሆኖ ተጥሏል።

ኪዊ የተባለው ፍሬ 13 በመቶ ያክሉ ልጣጩ ነው። ሮማን የሚባለው ፍሬም እንዲሁ ልጣጩ ጠቃሚ ነው።

በዓለማችን ጥቅም ላይ መዋል የሚገባው አንድ ሦስተኛ የሚሆን ምግብ ይጣላል። ይህ በዓመት 1.3 ቢሊዮን ቶን ይሆናል።

የምግብ ብክነት ለግሪንሐውስ ጋዝ ልቀት 8 በመቶ ድርሻ አለው። ይህ አውሮፕላኖች ከሚያመነጩት ጭስ ሦስት እጥፍ ነው።

ቆሻሻ ማከማቻ የሚጣሉ ምግቦች በቆይታ ብዛ ሜቴን የተባለ ከካርበን ዳይኦክሳይድ 80 እጥፍ መርዛማ የሆነ ጋዝ ያመነጫሉ። ምግብን ቆሻሻ መጣያ ከመጣል ይልቅ ለማዳበሪያነት መጠቀም የሜቴን ልቀትን ይቀንሳል።

ነገር ግን ቆሻሻ ነው ብለን የምንጥለው አብዛኛው ምግብ ሊበላ የሚገባው ነው። የምግብ ኢንዱስትሪው ልጣጭን ከመጣል ይልቅ ለሌሎች ዓላማዎች ማዋል ጀምሯል። እኛስ በቤታችን ልጣጭ እንዳይባክን ምን ማድረግ እንችላለን።

እነሆ ቆሻሻ ተብለው የሚጣሉ ፍራፍሬዎች እና አትክልቶችን ጥቅም ላይ የምናውልባቸው መንገዶች።

አናናስ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ብርቱካን ልጣጭ

የብርቱካን ልጣጭ ተከትፎ ለ10 ደቂቃ ያክል ይቀቀላል። ከዚያ በኋላ ልጣጩን በቀዝቃዛ ውሀ ማጥለል። ይህን ሦስት ጊዜ መደጋገም የብርቱካን ልጣጩን መራራ ጣዕም ያጠፋዋል። ቀጥሎ በውሀ እና በስኳር መቀላቀል።

በዚህ መልኩ ከብርቱካን ልጣጭ እንደ ማርማራታ ያለ የሚቀባ 'ሲረፕ' መሥራት ይቻላል።

ከብርቱካን ልጣጭ ማርማሌድም መሥራት ይቻላል። በተጨማሪም ጭማቂ እና ሲረፕ ይሠራበታል። ኩችናችን ብርቱካን ብርቱካን መሽተቱም አንድ ጥቅም ነው።

የአናናስ ልጣጭ

ብዙዎቻችን አናናስ ስንበላ የምንጥለው ይበዛል። እንዴት የአናናስ ልጣጭን ጥቅም ላይ ልናውለው እንችላለን።

ቴፓሽ የተባለው የሜክሲኮ የተብላላ መጠጥ በጣም ጥንታዊ መጠጥ ነው። ይህ መጠጥ የአናናስ ልጣጭ ከመጠቀሙም በላይ የፕሮባዮቲክ ምንጭ ነው።

ይህን መጠጥ መሥራት ከባድ አይደለም። ነገር ግን አልኮል ለማይጠቀሙ ሰዎች አይመከረም። ምክንያቱም መጠጡ ሲብላላ ወደ አልኮልነት ይቀየራል። ቢሆንም የአልኮል ይዘቱ ብዙውን ጊዜ 1 በመቶ ነው። እየተብላላ ብዙ ቀናት ከቆየ የአልኮል መጠኑ ከፍ ይላል።

መጀመሪያ ለመጥመቂያ የሚሆን 4 ሊትር የሚይዝ ዕቃ ያዘጋጁ። ዕቃውን መሸፈኛ ጨርቅ እና 'ላስቲክ' ያስፈልጋል። አናናሱን አጥቦ ማዘጋጀት። ፀረ-ተባይ ያልተረጨበት ፍራፍሬ መጠቀም ሁሌም ይመከራል።

ውሀውን ከቡናማ ስኳር ጋር በማደባለቅ ትንሽ ሞቅ ባለ እሳት ስኳሩ እስኪቀልጥ መጠበቅ። ቀጥሎ የአናናስ ልጣጩን ከቀለጠው ስኳር እና ውሀ ጋር ወደ ዕቃው ጨምሮ መዝጋት።

ከ24-36 ሰዓታት ባለው ጊዜ ውስጥ ውሀው ነጭ አረፋ ያመነጫል። ይህ ማለት እየተብላላ ነው ማለት ነው። ከ36 ሰዓታት በላይ የሚቆይ ከሆነ ጣዕሙና የአልኮል መጠኑ ይጨምራል። በፈለጉት ወቅት አጥልሎ ከተቻለ አቀዝቅዞ መጠቀም ይቻላል። ዝንጅብል፣ ሎሚ እና ሌሎች ፍራፍሬዎች መጨመር የበለጠ ጣዕሙ እንዲጨምር ሊያደርገው ይችላል።

ዝንጅብ ልጣጭ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዝንጅብ ልጣጭ

የዝንጅብል ልጣጭም እንደ ቀልድ የምንጥለው ነገር ግን ጥቅም ያለው ነገር ነው።

የዝንጅብል ልጣጭ አንቲዶክሳንት፣አንቲማይክሮቢያል እና አንቲካንሰር የተባሉ ለጤናችን እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮች አዝሏል። የፋይበር እና የቫይታሚን ሲ፣ ካልሺየም እና አየረን ምንጭም ነው።

ዝንጅብሉን አጥቦ ሳይልጡ መጠቀም ይቻላል። ሾርባ ሲሰራ ቢጨመር ጣዕም ያክላል። ነገር ግን ከማቅረብዎ በፊት ቢያወጡት ይመረጣል። በውሀ ቀቅሎ አስቀምጦ ጭማቂ እና ሌሎች መጠጥ ውስጥ ማከልም ይቻላል።

ልጣጩን ፍቆ በዝግታ በመጥበስ ፈጭቶ ዱቄት ማድረግ እጅግ ተመራጭ ነው። በዱቄቱ የዝንጅብል ሻይ ማፍላት ይችላሉ። ወጥ ስንሰራ ዱቄቱን እንደ ቅመም መጠቀምም የምግባችን ጣዕም ከፍ እንዲል ያደርገዋል።

ዝንጅብሉን በመላጫ ከመላጥ ይልቅ በማንኪያ መፋቅ ይመከራል።

የሽንኩርት ልጣጭም ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሽንኩርት ልጣጭ ለሽሮና በርበሬ መቀመሚያ የሚጠቀሙ ሰዎች አሉ።

ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የምናያቸው በርካታ ሰዎች የሽንኩርት ልጣጭ አድርቀው ዱቄት በማድረግ እንደ ቅመም ሲጠቀሙትም ይስተዋላል።