ከልክ ያለፈ ውፍረት (ኦቤሲቲ) ምንድነው? ትርጉሙስ እንደገና ሊጤን ይገባል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለማችን ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሚሆነው ሕዝብ ከመጠን በላይ የሆነ ውፍረት (ኦቤሲቲ) አለባችሁ መባላቸውን ተከትሎ ይህ የክብደት አገላለጽ አዲስ ትርጉም እንደሚያስፈልገው ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች የተሳተፉበት አዲስ ሪፖርት አጽንኦት ሰጠ።
ከልክ ያለፈ ውፍረት (ኦቤሲቲ) "የበለጠ ትክክለኛ" እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ የሚያስገባ ትርጉም ያስፈልገዋል ተብሏል።
ዶክተሮች የሰዎችን ክብደት መዝነው ከቁመት አንጻር በማስላት (ቢኤምአይ) ውፍረትን ከሚለኩበት በበለጠ በሰውነት ውስጥ ያለውን ከመጠን በላይ ያለፈ የስብ መጠን (ፋት) ከግምት ውስጥ ሊያስገቡት ይገባል ተብሏል።
በውፍረታቸው ሳቢያ ስር የሰደደ ህመም ያዳበሩ ግለሰቦች ከመጠን በላይ የሆነ ውፍረት (ክሊኒካል ኦቤሲቲ) አለባችሁ ተብለው ሊለዩ ቢገባም፣ ነገር ግን ምንም ዓይነት ህመም የሌለባቸው፣ ቅድመ ክሊኒካል ኦቤሲቲ መባል አለባቸው ተብሏል።
በዓለማችን ዙሪያ ከአንድ ቢሊዮን የሚበልጡ ነዋሪዎች ከመጠን በላይ የሆነ ውፍረት (ኦቤሲቲ) አለባቸው ተብሎ የሚገመት ሲሆን፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ ውፍረትን ለመቀነስ የሚያግዙ በህክምና ባለሙያዎች የሚታዘዙ መድኃኒቶች ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
ታዋዊው የህክምና ጉዳዮች መጽሔት (The Lancet Diabetes & Endocrinology journal) ላይ የታተመው ይህ ሪፖርት በዓለም ዙሪያ ከ50 በሚበልጡ የህክምና ባለሙያዎች የተደገፈ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አቤሲቲን እንደገና ማጤን
ከመጠን በላይ የሆነ ውፍረት (ኦቤሲቲ) ተብሎ የተፈረጀው ውፍረት ሰፋ ያሉ ሁኔታዎችን የሚያካትት እንደሆነ የዚህን ባለሙያዎች ቡድን የመሩት የለንደኑ የኪንግስ ኮሌጅ ባልደረባ ፕሮፌሰር ፍራንቼስኮ ሩቢኖ ያስረዳሉ።
"አንዳንዶች ከመጠን በላይ ውፍረት ቢኖራቸውም ሕይወታቸውን በተለመደው መልኩ እየኖሩ ሥራቸውን ያከናውናሉ" የሚሉት ፕሮፌሰሩ "ሌሎች ደግሞ በአንጻሩ በደንብ መራመድም ሆነ መተንፈስ አይችሉም፤ ወይም በዊልቸር ብቻ ተወስነው ከከባድ የጤና ተግዳሮቶች ጋር የሚኖሩ ናቸው" ይላሉ።
በውፍረታቸው ምክንያት በበሽታዎች የተጠቁ ታማሚዎች እና በአሁኑ ወቅት ጤናማ የሆኑ እና ለወደፊቱ ለበሽታ ሊጋለጡ የሚችሉትን ለመለየት ከመጠን በላይ የሆነ ውፍረት (ኦቤሲቲ) እንደገና ሊጤን ይገባል ይላል ሪፖርቱ።
የሰውነት የስብ መጠን (ፋት) ከቁመት እና ከክብደት አንጻር በሚያሰላው (ቢኤም አይ) ዘዴ መሠረት በበርካታ አገሮች ከመጠን ያለፈ ውፍረት (ኦቤሲቲ) የሚባለው ከ30 በላይ ሲሆን ነው።
እንደ ዌጎቪ እና ሞንጃሮ ያሉ ውፍረትን ለመቀነስ የሚያገለግሉ መድኃኒቶች በዚህ የቢኤምአይ መጠናቸው ከ30 በላይ ምድብ ውስጥ ላሉ ሰዎች ብቻ የተገደበ ነው።
በበርካታ የዩናይድትድ ኪንግደም ግዛቶች እነዚህን መድኃኒቶች ለመጠቀም የአገሪቱ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ከውፍረት ጋር የተያያዙ የጤና እክሎችን እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል።
ሪፖርቱ በበኩሉ ይህ ቁመት እና ክብደትን አስልቶ ውፍረትን የሚለካው ቢኤምአይ ስለ ህመምተኞች አጠቃላይ ጤና ምንም ነገር አይገልጽም ይላል።
በተለይም በጡንቻ እና በአጠቃላይ ሰውነት ውስጥ በሚገኘው የስብ መጠን መካከል ያለውን ልዩነት መለየት የማይችል እንዲሁም በተለይም በሆድ አካባቢ እና በሰውነት ክፍሎት ውስጥ የተከማቸውን አደገኛ የሚባለውን የስብ መጠን ከግምት ውስጥ እንደማያስገባ ሪፖርቱ ያትታል።
ባለሙያዎቹ ከመጠን ያለፈ ውፍረት የሰውነት ክፍሎት ላይ የሚያስከትሏቸው እንደ የልብ ህመም፣ የመተንፈስ ችግር፣ የስኳር ህመም ዓይነት ሁለት እና የመገጣጠሚያ ህመም እንዲሁም በአጠቃላይ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የሚያስከትላቸውን ተጽእኖዎች የሚያጤን አዲስ ሞዴል አስፈላጊ ነው ሲሉ ይከራከራሉ።
ይህም የሚያሳየው ከመጠን ያለፈ ውፍረት በህክምና መታገዝ ያለበት ህመም እና ከበሽታው ለመዳንም መድኃኒቶች ያስፈልገዋል ብለዋል።
ሆኖም ህመሞች የሌለባቸው ከመጠን በላይ ውፍረት አለባችሁ የተባሉ ግለሰቦች ግን ከመድኃኒት እና ከቀዶ ህክምና ይልቅ ክብደታቸውን ለመቀነስ ምክር እና ለበሽታዎች የሚያጋልጧቸውን ዕድሎች ለመቀነስ የክትትል ፕሮግራሞች ሊነደፍላቸው እንደሚገባ ሪፖርቱ ይመክራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አላስፈላጊ ህክምና
"ከመጠን ያለፈ ውፍረት ለጤና ጠንቅ ነው። ልዩነቱ ግን ለአንዳንዶች በሽታ ነው" ይላሉ ፕሮፌሰር ሩቢኖ።
ይህ ትልቅ ቁጥር ሕዝብ ውስጥ ያለውን የአደጋ ደረጃ ለመረዳት ከመጠን በላይ ላለፈ ውፍረት እንደገና ትርጓሜ መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሰው አሁን ያለውን የኦቤሲቲ ትርጉም ያጠራዋል ይላሉ።
በወገብ ውፍረት እና ቁመት መካከል ያለውን ልዩነት ስሌት መጠቀም፣ ወይም ቀጥታ የሰውነት የስብ መጠንን መለካት እና የግለሰቦችን የህክምና ታሪክ ማካተት ከቢኤምአይ በበለጠ ግልጽ ያለ ምስል እንደሚሰጥ ሪፖርቱ ጠቁሟል።
ለሪፖርቱ አስተዋጽኦ ያደረጉት በህጻናት ከመጠን በላይ ያለፈ ውፍረት ባለሙያ እና የሲድኒ ዩኒቨርስቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ሉዊዝ ባኡት በበኩላቸው አዲሱ ምልከታ ከመጠን በላይ ውፍረት ያለባቸውን ማንኛውንም ሰዎች "የሚሆናቸውን የጤና እንክብካቤ እንዲያገኙ" ያስችላቸዋል ይላሉ።
ይህም ከመጠን ያለፈ ውፍረት አለባችሁ የሚባሉ ሰዎችን ቁጥር እንዲሁም አላስፈላጊ ህክምናን እንደሚቀንስ አክለው ያስረዳሉ።
የሰውነት ውፍረትን እስከ 20 በመቶ የሚቀንሱ መድኃኒቶች በከፍተኛ ደረጃ እየታዘዙ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ከመጠን በላይ ያለፈ ውፍረትን እንደገና ማጤን የበለጠ ትክክለኛነት ያለው ውጤት ላይ ለመድረስ የበለጠ ጠቃሚ እንደሆነ ሪፖርቱ አጽንኦት ሰጥቷል።
የሮያል ኮሌጅ የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ሪፖርቱ "ከመጠን በላይ ያለፈ ውፍረት ልክ እንደ ሌሎች ስር የሰደዱ በሽታዎች በሚታከሙበት ረገድ እንዲታይ እና የበለጠ ህክምና እንደሚያስፈልገው" ጠንካራ መሠረት ጥሏል ብለዋል።
ውፍረታቸው ህመም ባስከተለባቸው እና ህመም በሌለባቸው ከመጠን በላይ ውፍረት አለባችሁ የተባሉትን ሰዎች መለየት ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ፣ ውፍረታቸው ከፍተኛ የጤና ጉድለቶች ላስከተለባቸው ህሙማን ቀደም ብሎ ተገቢውን እንክብካቤ መስጠት ያስችላል ብሏል ኮሌጁ።















