የሽንታችን ቀለም ስለጤናችን ምን ይነግረናል? ምን ዓይነት ቀለም ሲኖረው ነው ሊያስጨንቀን የሚገባው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቀይ፣ ቢጫ፣ ሮዝ እና አረንጓዴ። አንዳንድ ጊዜ ሽንታችን ሐምራዊ ቀለም ሊኖረው ይችላል።
ወይን ጠጅ ቀለምም ሊሆን ይችላል ብንልዎ ይገርምዎታል? ኧረ እንዲያውም ብርቱካናማ እና ሰማያዊም ይሆናል። ሌሎችም ቀለማትን በሽንታችን ላይ ልናይ እንችለን።
ሸንት ማለት ሰውነታችን አላስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ፈሳሾች የሚያወጣበት መንገድ ነው። ፕሮቲን ተሰባብሮ ናይትሮጂን ሲወገድ በሽንት መልክ ነው።
ጥቅም ላይ የዋሉ እንደ ቪታሚን እና ሌሎች መድኃኒቶች፣ አንዳንድ ለሰውነት ምግብ የሚሆኑ ፈሳሾች ከሰውነታችን ውልቅ የሚሉት በሽንት በኩል ነው።
የሸንታችን ቀለም ስለጤናችን ብዙ ይነግረናል። ለዚህ ነው የጤና ባለሙያዎች “የሽንታችሁ ቀለም እንዴት ያለ ነው?” ብለው የሚጠይቁት።
እኛም የጤናችንን ሁኔታ በቅርበት ለመከታተል የሽንታችንን ቀለም ልብ ብለን መመልከት እና ለሐኪም ማሳወቅ ያስፈልጋል።
እስቲ ዋና ዋና የሚባሉት በሽንታችን ላይ የሚከሰቱ ቀለማት እና የምን ምልክት ሊሆኑ እንደሚችሉ እንመልከት።
ቀይ
ቀይ የሽንት ቀለም መድማትን የሚጠቁም ነው። ይህ ደም ከሽንት ቧንቧ፣ ከኩላሊት እና ከሌሎች ከሽንት መተለላፊያ ክፍሎች ጋር ከሚገናኙ ቀዳዳዎች ሊፈስ ይችላል።
የደማችን ቀለም እንደ ብዛቱ እና ትኩሰነቱ ይቀያየራል። የተለያዩ የቀይ ቀለም መደቦች የሚይዘውም ለዚሁ ነው።
ለምሳሌ ከፍተኛ መድማት ካለ ደማችን ቀይ ወይን ይመስላል።
ከኩላሊት ጠጠር ጀምሮ እስከ ካንሰር እና የሽንት ቧንቧ ቁስለት መድማትን ያስከትላሉ። ነገር ግን አብዝተው ቀይ ሥር የተመገቡ ሰዎችን ቀይ ሽንት ሊያዩ ይችላሉ።
ብርቱካናማ እና ቢጫ
ብዙውን ጊዜ ጤናማ ሽንት የሚባለው የቢጫ ቀለም መደባትን ሲይዝ ነው። ይህ ምን ያክል ፈሳሽ ጠጥተናል የሚለው ላይ ይወሰናል።
የፈሳሽ እጥረት ካለብን ጠቆር ያለ ቢጫ ሽንት እንሸናለን። አንዳንድ ጊዜ ወደ ብርቱካናማ ሊጠጋ ይችላል። ሰውነታችን በበቂ ሁኔታ ውሃ ካገኘ ደግሞ ሽንታችን ነጣ ያለ ቢጫ ይሆናል ማለት ነው።
ሽንታችን ቢጫ የሚሆነው አገልግሎታቸውን የጨረሱ ቀይ የደም ሴሎች ከሰውነታችን ሲወገዱ ነው።
ይህ ሒደት በሳይንሱ አጠራር ቢሊሩቢን ይባላል። ግማሹ በሽንት፣ ግማሹ ደግሞ በአንጀት በኩል ይወገዳል። ጉበታችን ባይል የተባለ ስብ የሚያፈራርስ እና ለምግብ መፈጨት ጠቃሚ የሆነ ነገር ያመርታል።
ቢሊሩቢን ወደ ደም ባንቧ ተቀላቅሎ በሽንት መልክ ሲወጣ ነው ጠቆር ያለ የሚሆነው። ቢሊሩቢን ሲጠራቀም ቆዳችንን ቢጫ ሊያደርገው ይችላል።
በርካታ መድኃኒቶችን ሽንታችንን ብርቱካናማ ሊያደርጉት ይችላሉ።
አረንጓዴ እና ሰማያዊ
አረንጓዴ እና ሰማያዊ የሽንት ቀለማት እምብዛም የማይታዩ ሲሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ስናያቸው ልንደነግጥ እንችላለን።
ሽንታችን እነዚህን ሁለት ቀለማት መሰለ ማለት አንዳች ከበድ ያለ ምክንያት አለው ማለት ነው።
አንዳንድ ጊዜ አረንጓዴ አሊያም ሰማያዊ ቀለም ያለው ምግብ ወይም መጠጥ አብዝተን ስንወስድ ይህ ሊከሰት ይችላል። አኔስቴቲክ እና አንታይስታሚን የተባሉ መድኃኒቶች እና ቪታሚንም ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ።
ከብዙ አንድ ጊዜ ደግሞ የሽንት ቧንቧ መቁሰል ምልክት ሊሆን ይችላል። ታድያ ሽንታችን ቀለሙ አረንጓዴ አሊያም ሰማያዊ ሆኖ የሚያቃጥለን ከሆነ ችግር አለ ማለት ነው።
ስለዚህ ሳይዘገዩ ሐኪም በማማከር ምክንያቱን ማወቅ እና መፍትሄውን መፈለግ ያሻል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወይን ጠጅ
የወይን ጠጅ ቀለም ያለው ሽንት የተለመደ አይደለም። አንደኛው ምክንያት ሊሆን የሚችለው በዘር የሚተላለፍ ፖርፊሪያ ነው። ፖርፊሪያ ቆዳን እና የነርቭ ሥርዓትን የሚያጠቃ የጤና ዕክል ነው።
ሌላኛውም ምክንያት ፐርፕል ባግ ሲንድረም ይባላል። ይህ ደግሞ በባክቴሪያ አማካይነት የሚሰከት የጤና ችግር ነው።
ካቴረር የተባለው የሽንት ድርቀት ያለበት ሰው በባክቴሪያ አማካይነት የወይን ጠጅ ቀለም ያለው ሽንት ሊያይ ይችላል።
ሮዝ
ቀይ ሥር በመጠኑ መመገብ ሽንታችን ሮዝ ቀለም እንዲኖረው የማድረግ አቅም አለው።
የዘርፉ የጤና ሙያተኞች ሽንታችን ከሮዝ ወይን [መጠጥ] ጋር ሊመሳሰል ይችላል ይላሉ። ቀይ ሥር አብዝቶ መመገብ በተቃራኒው ሽንታችንን የበለጠ ሊያቀላው ይችላል።
ሌሎች ቀለማት
ከቀስተ-ደመና ቀለማት በተጨማሪ ሌሎች ቀለማት ሊታዩ ይችላሉ።
አንዳንድ ጊዜ ጠየም ብለው ቡናማ ወይም ጥቁር ይሆናሉ። የጤና ባለሙያዎች ከኮካ-ኮላ ቀለም ጋር ያመሳስሉታል።
ይህ ማዮግሎቢን ከተባለው ንጥረ ነገር ይወጣል። ከባድ ህመም ያለባቸው ሰዎች በርካታ መድኃኒት ሲወስዱ የመከሰት ዕድል አለው።
አንዳንድ ጊዜ ከቢሊሩቢን ይመነጫል። ቢሊሩቢን ሽንትን ጠቆር የማድረግ አዝማሚያ ያሳያል።
የኩላሊት ቁስለት እና ሌሎች በሽታዎች ሽንታችን ወደ ጥቁር ቀለም እንዲቀይር የማድረግ ኃይል አላቸው።
ቀለም አልባ የሚባለው ሽንት ደግሞ በሽታን እንዳለብን ሊጠቁም ይችላል። የስኳር ህመም አሊያም አልኮል መጠጥ አብዝቶ መጠቀም ቀለም አልባ ሽንት ያስከትላል።
ከላይ የተጠቀሱት የሽንት ቀለማት ጤናማነት አሊያም በሽታን ሙሉ በሙሉ ይጠቁማሉ ማለት አይደለም። ነገር ግን ሽንታችን ከተለመደው ዓይነት ወጣ ያለ ቀለም ሲኖረው ሐኪም ማማከሩ አይከፋም።












