በምንጸልይበት ጊዜ አንጎላችን ውስጥ ምን ይፈጠራል?

ፀሎት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታዋቂው ብሪታኒያዊ ፀሐፊ ሲ ኤስ ሉዊስ ጸሎት ለብዙዎች ምን ማለት እንደሆነ በጥሩ መልኩ ገልጾታል።

“ምንም ማድረግ ስለማልችል እጸልያለሁ፤ ልቤ ስለተሰበረ እጸልያለሁ፤ እጸልያለሁ ምክንያቱም ተኝቼም ሆነ ነቅቼ ይህን የማድረግ አስፈላጊነት ሁልጊዜም በውስጤ ይፈሳል። (መጸለይ) ፈጣሪን አይለውጠውም። እኔን ግን ይለውጠኛል” ሲል ደራሲው በአንድ ወቅት ተናግሯል።

የቢቢሲ የሳይንስ ፕሮግራም የሆነው የክራውድሳይንስ አድማጭ የሆነችው ሂላሪ ተቀምጣም ሆነ የእግር ጉዞ ስታደርግ ስትጸልይ ተመሳሳይ ነገር ይሰማታል።

“ስጸልይ ከአምላክ ጋር ግንኙነት እንዳለኝ ይሰማኛል። ነገር ግን ጸሎት ብዙ ልዩነቶች አሉት። በጸጥታ ውስጥ ያለ ቃላት ሊከናወን ይችላል። አንዳንዴም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የቡድን ጸሎት ማድረግ ሊሆን ይችላል።”

“ጸሎት አእምሮን እና የአእምሮ ጤናን የሚወስነው እንዴት ነው?” የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።

የክራውድሳይንስ አዘጋጆች በሚጸልዩ ሰዎች አንጎል ውስጥ ምን እንደሚፈጠር ለመረዳት እና ይህ ዘዴ የግድ ከሃይማኖቶች ጋር የተያያዘ መሆኑን ወይም በተመስጦ ውስጥ ሊኖር እንደሚችል ለማወቅ ከባለሙያዎች ጋር ምክክር አድርገዋል።

ፀሎት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንጎል

በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የቶማስ ጄፈርሰን ዩኒቨርሲቲ የማርከስ ኢንተግሬቲቭ ሕክምና ተቋም የምርምር ዳይሬክተር የሆኑት ኒውሮሳይንቲስቱ አንድሩ ኒውበርግ ጸሎት እና ሌሎች ሃይማኖታዊ ድርጊቶች በታካሚዎቻቸው የአእምሮ ጤና ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ አጥንተዋል።

የኤምአርአይ ምርመራዎችን በመጠቀም ቡድናቸው የሚጸልይ ሰው የትኛው የአንጎል ክፍል እንደሚነቃቃ ለማየት ችሏል።

“የተለመደው የጸሎት መንገድ አንድ ሰው አንድን ጸሎት የማድረግ ልምምዱ ሲደጋግም ነው። እናም አንድ ሰው በዚህ መልኩ ሲጸልይ ከሚነቃቃው የአንጎል ክፍሉ ውስጥ አንደኛው የፊተኛው የአንጎል ክፍል ነው" ሲሉ ባለሙያው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአንድ ጉዳይ ላይ በጥልቀት ስናተኩር የመንቃት ዝንባሌ ያለው የፊተኛው የአእምሮ ክፍል በመሆኑ ይህ አያስገርምም። ኒውበርግን ያስደነቀው ግን ሰዎች “ጥልቅ ጸሎት” ወደሚሉት ተግባር ውስጥ ሲገቡ የሚፈጠረው ነው።

“ግለሰቡ ጸሎቱ እየረዳው እንደሆነ ሲሰማው የፊተኛው የእምሮ ክፍል እንቅስቃሴ ይቀንሳል። ይህ የሚሆነው የግለሰቡ ልምዶቹ የሚያመነጩት ከእሱ ሳይሆኑ ከእነሱ ውጪ በሆነ ኃይል እንደሆነ ሲሰማቸው ነው” ብለዋል ተመራማሪው።

እንደኒውበርግ ከሆነ ጥልቅ ጸሎት በአእምሯቸው የኋለኛው ክፍል በሚገኘው በፓሪዬታል ሎብ ውስጥ እንቅስቃሴን ይቀንሳል። ይህ አካባቢ የስሜት ህዋሳት መረጃን ተቀብሎ ምሥላዊ መግለጫን ይፈጥራል።

እንደኒውበርግ ከሆነ በጥልቅ የሚጸልዩ ሰዎች በፓርዬታል ሎብ ውስጥ ያለው “እንቅስቃሴ እየቀነሰ በሄደ መጠን ለራሳችን ያለን ግንዛቤ እየጠፋ የአንድነት እና የመተሳሰር ስሜት እናገኛለን” ብለዋል።

ፀሎት

የእምነት ጉዳይ?

የኒውበርግ ማብራሪያ ለሂላሪ ውሃ የሚያነሳ ነው። ይህንንም ስትጸልይ ከሚሰማት ነገር ጋር አገናኝታ “የግለሰብን ስሜት የማጣት ሁኔታን እያሰላሰልኩ በምጸልይበት ጊዜ ከፈጣሪ ጋር ከሚሰማኝ ግንኙነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ እገምታለሁ” ብላለች።

ነገር ግን ጸሎት እጅግ የግል ተሞክሮ ነው። ለሂላሪ ተቀምጦ ወይም ጫካ ውስጥ በመራመድ ሊከሰት ይችላል። ለሌሎች ደግሞ በፍፁም ፀጥታ ወይም በዝማሬ ከፈጣሪ ጋር የሚደረግ ንግግር ሊሆን ይችላል።

ከጸሎት ጋር የሚመሳሰሉ ልማዶች ሆነው ነገር ግን ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ መሠረት የሌላቸው ድርጊቶች ሰዎች ላይ ተመሳሳይ ውጤት ሊያስገኙ ይችላሉን?

የተመስጦ (ሜዲቴሽን) ባለሙያ የሆኑት ቴሳ ዋት ይህንን ውጤት በአሁኑ ስዓት እና በምናገኛቸው ስሜቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ማግኘት ይቻላል ይላሉ።

“እኔ እንደማስበው ከሆነ ጸሎት እና ተመስጦ አንድን ሰው ለማረጋጋት ይረዳሉ። ስለዚህ ለራሳቸው ብዙ ጊዜ ይኖራቸዋል። በመሆኑም ተመሳሳይ የነርቭ ሥርዓትን ያንቀሳቅሳሉ” ሲሉ ዋት ያስረዳሉ።

የነርቭ ሥርዓቱ አብዛኞቹን የሰውነት ደመነፍሳዊ ምላሾችን የሚቆጣጠሩ ሁለት የተለያዩ ሥርዓቶችን ያቀፈ ነው።

በአንድ በኩል ሰውነታችን ከፊቱ የሚገጥመውን አደጋ በመታገል ወይንም በመሸሽ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥበት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሰውነታችን “በማረፍ እና በጽሞና” የሚያጋጥሙትን ሁኔታዎች የሚወጠበት ሥርዓቶች አሉት።

"ይህ ማለት ተመስጦን በመለማመድ አስጊ ሁኔታ ሲገጥመን የሚኖረውን ምላሽ ማረጋጋትን ይማራሉ። በዚህም ስሜትዎን ለመቆጣጠር የበለጠ ዝግጁ ያደርግዎታል" ሲሉ ዋት ይናገራሉ።

መፅሐፍ ቅዱስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከፈጣሪ ጋር መገናኘት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሃይማኖታዊ አካባቢ ውስጥ የሚያድጉ አንዳንድ ሰዎች ከፈጣሪ ጋር ያላቸው ግንኙነት በአካባቢያቸው ካሉ ሌሎች ሰዎች ጋር ያላቸውን ስሜታዊ ግንኙነት ሊያንፀባርቅ ይችላል ሲሉ በካሊፎርኒያ የዌስትሞንት ኮሌጅ የሶሺዮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ብሌክ ቪክቶር ኬንት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ጸሎት ጠቃሚ ሊሆን ቢችልም፤ በተለይም በስሜታዊነት ከፈጣሪ ጋር መገናኘትን የመሳሰሉ ከግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ።”

ብሌክ ፓስተር ናቸው። አሁን ሃይማኖት በሰዎች ሕይወት ላይ ያለውን ተጽእኖ እያጠኑ ነው። “ሌሎችን ማመን ከሚከብድበት አካባቢ የመጡ ከሆነ መጸለይ የበለጠ ከባድ ይሆንቦታል” ይላሉ።

ብሌክ ምን እንደሚሉ ለመረዳት በሥነ ልቦና ውስጥ ስላለ የቁርኝት ጽንሰ ሐሳብ መነጋገር ይኖርብናል። የሰው ልጅ በህጻንነት ካሳደጓቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ወደፊት የሚኖራቸውን የግንኙነት ዓይነት የሚገልጽ ጽንሰ ሐሳብ ነው።

በልጅነት ጊዜ አስተማማኝ ተንከባካቢ ካለዎት ትልቅ ሲሆኑ “የጠነከረ” ትስስር ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ፅንሰ-ሀሳቡ ይናገራል። ነገር ግን እንደ ብሌክ ያለ ጥሩ ያልሆነ አሳዳጊ ከነበረዎት እያደጉ ሲሄዱ መተማመንን ማዳበር ከባድ ይሆናል።

ይህ ደግሞ ለእምነት መጠንከር አስቸጋሪ ይሆናል። ይህም አንዳንዶች ከፈጣሪ ጋር የጠበቀ ግንኙነት መመሥረትን በጣም አስቸጋሪ ያደርግባቸዋል።

በተጨማሪም በጣም ሃይማኖተኛ በሆነ አካባቢ የሚኖሩ ከሆነ በዚህ ምክንያት ግንኙነታቸውን ማዳበር ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማቸው ይችላል።

“ጸሎት ለእኔ ባዶ፣ አደገኛ እና እርግጠኝነት የሌለበት ነው” ይላሉ ብሌክ።

ብሌክ ያላቸው ግንኙነት ችግር ያለበት እና በፓስተርነት ሥራቸው ወቅትም በጣም መሰቃየታቸውን ይገልጻሉ። ምክንያቱ ደግሞ ሲጸልዩ ትክክል ያልሆነ ነገር እንዳለ ስለሚሰማቸው ነው።

“እናም በሃይማኖታዊ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች ተመሳሳይ ስሜት የሚሰማቸው እና የሆነ ነገር ሲያደርጉ ወይም ፈጣሪ የተናደደባቸው ሆኖ እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል” ብለዋል።

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ እንደሌሎች በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ሲጸልዩ እና ተመሳሳይ ውጤት እንዳላገኙ ሲገነዘቡ ነው።

ከፈጣሪ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያለመኖሩ ጎጂ ሊሆን ቢችልም፤ ይህ አለመተማመን ከየት እንደመጣ ለመረዳት ሊያግዝ ይችላል ይላሉ ብሌክ። በተጨማሪም ይህ በሳይኮቴራፒ አማካኝነት ሊሻሻል ከመቻሉም በላይ ለአጠቃላይ የአእምሮ ጤናም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

ፀሎት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ምን ይፈጠራል?

ኒውሮሳይንቲስቱ አንድሪው ኒውበርግ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ በጥናታቸው ወቅት የኤምአርአይ ምሥሎች ከጥልቅ ጸሎት ጋር የሚመስሉ ሌሎች ሁኔታዎች እንዳሉ ያሳያሉ ብለዋል።

“በከፍተኛ ደረጃ በሰለጠኑ ሙዚቃ ሙያተኞች ላይ በጣም አስደሳች ጥናቶች ተካሂደዋል። እነሱ ሙዚቃ መለማመድ ሲጀምሩ የፊት የአንጎላቸው ክፍል እንቅስቃሴ ይቀንሳል። አንዳንድ ሰዎች ፈጣሪ እንደደረሰላቸው በሚሰማቸው መንገድ ሙዚቃው ወደ እነሱ የሚደርስ ይመስላል” ብለዋል ሳይንቲስቱ።

ሂላሪ ባለሙያዎቹን ካዳመጠች በኋላ ልምዷን እና እርስ በርስ እንዴት እንደሚገናኙ በደንብ መረዳት እንደቻለች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በእነዚህ ሁሉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተመሳሳይ፣ ነገር ግን የተለየ ልምድ እንዳለኝ መገንዘብ እችላለሁ። ስለዚህ ስጸልይ ከፈጣሪ ጋር ግንኙነት አለኝ። ስዘምር እና ተመሳሳይ ስሜት ሲሰማኝ ከሙዚቃ ጋር ግንኙነት አለው።”

“ከፈጣሪ ጋር ስነጋገርም ሆነ ከመዘምራን ጋር ስዘምር መንፈሳዊ ነገር እንደሆነ ይሰማኛል ብዬ መናገር እችላለሁ” ብላለች።

ፀሎት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images