አሜሪካ፤ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ለ75 አገራት ዜጎች የስደተኝነት ቪዛ መስጠት አቆመች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ጨምሮ ከ75 አገራት ለሚመጡ ሰዎች የስደተኝነት ቪዛ የሚሰጥበትን ሂደት ላልተወሰነ ጊዜ አገደ።
ስደተኞች ወደ አሜሪካ የሚገቡባቸውን ሕጋዊ መንገዶች ይበልጥ እያጠበቀ ያለው የትራምፕ አስተዳደር፤ ይህ አዲስ ውሳኔ ከሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ጥር 13/2018 ዓ.ም. ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምር አስታውቋል።
የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ትናንት ረቡዕ ጥር 6 ቀን ባወጣው መግለጫ፤ ውሳኔው የተላለፈው በመንግሥት ድጋፍ የሚኖሩ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ እንደሆነ ጠቁሟል።
በዚህ ውሳኔ፤ መንግሥት የሚሰጠውን ድጋፍ እና ጥቅማ ጥቅም በመጠቀም፤ "ከአሜሪካ ሕዝብ ሀብት የሚቀንሱ ሰዎች" ስርዓቱ ላይ የሚፈጽሙትን "ብዝበዛ ማስቆም" እንደተፈለገ መስሪያ ቤቱ ገልጿል።
ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ተፈጻሚ የሚሆነው ውሳኔ፤ 75 አገራትን እንደሚመለከት ተገልጿል። የዜና ወኪሉ አሶሺየትድ ፕሬስ ያወጣው አገራት ዝርዝር እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ከእነዚህ አገራት አንዷ ነች። ከኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት መካከል ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን እገዳ ከተጣለባቸው አገራት መካከል ተካትተዋል።
ዩጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎም ውሳኔው የሚመለከታቸው የምስራቅ አፍሪካ አገራት ናቸው። ሩሲያ፣ ኢራን፣ ግብጽ፣ ሊቢያ፣ የመን እና ሶርያም ከ75 አገራት መካከል ተጠቅሰዋል።
በአዲሱ ውሳኔ መሰረት ከእነዚህ አገራት የሚመጡ ሰዎች የሚያቀርቡት ስደተኝነት ቪዛ ተቀባይነት አይኖረውም። ይህ እገዳ የተላለፈው በጊዜያዊነት እንደሆነ ቢጠቆምም ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ አልተገለጸም።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የቆንጽላ መኮንኖች ከእነዚህ አገራት ለሚመጡ ሰዎች የሚካሄዱ የስደተኛ ቪዛ ማመልከቻ ሂደቶችን እንዲያቋርጡ ትዕዛዝ መስጠቱን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል። ይህ እገዳ እንደ ጊዜያዊ ጎብኚዎች ወይም ለንግድ ሥራ የሚያጓዙ ሰዎች ያሉ ስደተኛ ያልሆኑ ቪዛ ጠያቂዎች ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ምክትል ቃል አቀባይ የሆኑት ቶሚ ፒጎት፤ "መሥሪያ ቤቱ፣ የአሜሪካ መንግሥት እርዳታ ፈላጊ ለሆኑ እና የአሜሪካን ሕዝብ ልግስናን ያለአግባብ ሊጠቀሙ የሚችሉ ስደተኞችን ብቁ አይደሉም ብሎ ለመመደብ ሥልጣኑን ይጠቀማል" ብለዋል።
"የመንግሥት ድጋፍ እና ጥቅማ ጥቅሞችን የሚወስዱ የውጭ አገር ዜጎች እንዳይገቡ ለመከላከል" ሲባል የተላለፈው ውሳኔ አሰራሩ እንደገና እስከሚገመግም ድረስ ለጊዜው ምክትል ቃል አቀባዩ አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስደተኞችን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ውሳኔዎችን እያስተላለፈ ያለው የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፤ ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ በአገሪቱ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተሰጥቶ የነበረውን ጊዜያዊ የሕግ ከላለ ማንሳቱ ይታወሳል።
የጥገኝነት መብት የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ከአሜሪካ እንዳይባረሩ እንዲሁም የመስራት ፈቃድ እንዲያገኙ አስችሎ የነበረው ይህ አሰራር የዘረጋው ከሶስት ዓመት በፊት በ2015 ዓ.ም. ነበር። የዚህ ህጋዊ ከለላ የቆይታ ጊዜ እንዲያበቃ መደረጉን ተከትሎም የዚህ ስርዓት ተጠቃሚ የነበሩ ኢትዮጵያውያን በ60 ቀናት ውስጥ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ታዝዘዋል።
በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለብሔራዊ ደህንነት ሥጋት ናቸው ተብለው በተፈረጁ እንደ ሩሲያ፣ ኢራን፣ አፍጋኒስታን እንዲሁም በርካታ የአፍሪካ አገራት ስደተኞች ላይ የተለያዩ ገደቦችን ሲጥሉ ቆይተዋል።
ሕዳር ላይ አንድ አፍጋኒስታናዊ ስደተኛ ሁለት አሜሪካ ብሔራዊ ዘብ ወታደሮች ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ኤርትራውያንን ጨምሮ የ19 አገራት ዜጎች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ ተከልክለዋል። በታህሳስ ላይ ተጨማሪ አምስት አገራት እና በፍልስጤም አስተዳደር የተሰጡ የጉዞ ሰነዶችን የሚጠቀሙ ሰዎች ክልከላው ውስጥ ተካትተዋል።
በዚህ እገዳ ውስጥ ከተካተቱ አገራት የመጡ ስደተኞች ያቀረቧቸው የጥገኝነት ጥያቄዎች፣ የዜግነት ሂደት እና የግሪን ካርድ ማመልከቻዎችም ታግደው እንደሚቆዩም ተገልጿል።















