ሴኔጋልን ለዋንጫ ያበቃው 'የአፍሪካ እግር ኳስ አምባሳደር' ሳዲዮ ማኔ

ሳዲዮ ማኔ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሳዲዮ ማኔ ሴኔጋልን በድጋሚ ለአፍሪካ ዋንጫ አብቅቷል። የቀድሞው የሊቨርፑል እና የባየር ሙኒክ ተጫዋች ማኔ 'የሴኔጋል ጀግና' ተብሎ እየተሞካሸ ነው።

በእሁዱ የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ሞሮኮ በ98ኛው ደቂቃ ቅጣት ምት ሲሰጣት የሴኔጋል አሠልጣን ፔፔ ቲያው ቡድናቸውን ከሜዳው አስወጥተዋል።

ማኔ እና ግብ ጠባቂው ኤዱዋርድ ሜንዲ የሴኔጋል ተጫዋቾችን ወደ ሜዳው መልሰዋል። ዲያዝ ፔናንካ ቅጣት ምቱን ሲመታ ግብ ጠባቂው በቀላሉ ነበር ኳሱን ያዳነው። ሴኔጋል እና ሞሮኮ ባዶ ለባዶ ሆነው ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።

ሴኔጋል በተጨማሪ ሰዓት ሞሮኮን አንድ ለባዶ ረትታለች።

ማኔ ይህ የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻው እንደሚሆን ተናግሯል። የቡድኑ መሪ ማኔ "እግር ኳስ ልዩ ነገር ነው። ዓለም እየተመለከተን ነበር። የዓለም ሕዝብ እግር ኳስ ይወዳል። እግር ኳስ የደስታ ምንጭ ስለሆነ ጥሩ ገጽታ ልናላብሰው ይገባል" ብሏል።

ሳዲዮ ማኔ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዋንጫ ፍልሚያው በድራማ የተሞላ ነበር። በስተመጨረሻም ማኔ ዋንጫውን ከቡድኑ ጋር ከፍ አድርጎ ታይቷል።

"ዳኛው ቅጣት ምት ስለሰጠ ብቻ ጨዋታውን ማቋረጥ እብደት ነው። እና ጨዋታውን ጥለን እንወጣለን? በተለይ በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ይሄ ተገቢ አይደለም። እግር ኳሳችን ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር ከማይ መሸነፍን እመርጣለሁ" ብሏል ማኔ።

የናይጄሪያው ተጫዋች ዳንኤል አሞካቺ "ማኔ ረዥም ርቀት ተጉዞ ቡድኑን ወደ ሜዳው መመለሱ ትልቅ ውጤት አስገኝቷል" ብሏል።

ማኔ በበኩሉ "ለአሥር ደቂቃም ቢሆን እግር ኳስ መቋረጥ የለበትም" ብሏል።

"አቋርጠን ብንወጣም ተመልሰናል። ጨዋታውን ቀጥለንም የሆነው ሆኗል" ሲልም ሴኔጋል ባለ ድል በመሆኗ የተሰማን ገልጿል።

የቡድን አጋሩ ዳንዴል ማኔን "አስደናቂ የእግር ኳስ አምባሳደር ነው" ብሎታል። "ከሜዳ ውጭ ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ እናውቃለን። እግር ኳስ ምን ማለት እንደሆነ ያውቃል" ሲለም ለቢቢሲ ተናግሯል።

ሳዲዮ ማኔ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቀድሞው የሞሮኮ ተጫዋች ሐሰን ካቹል "የአፍሪካ እግር ኳስም የዓለም እግር ኳስም ሊወድቁ ተቃርበው ሳለ ማኔ አድኗቸዋል" ብሏል።

"ከማንም በላይ ከሴኔጋል ቡድን የምወደው ሳዲዮ ማኔን ነው። ታላቅ ሰው መሆኑን አሳይቷል። መልበሻ ክፍል ተመልሶ ቡድኑን ወደ ሜዳው መልሷል" ሲልም አክሏል።

ማኔ እግር ኳስ የጀመረው በደቡብ ምዕራብ ሴኔጋል፣ ባምባሊ ውስጥ ነው። አሸዋማ መሬት ላይ በ13 ዓመቱ ኳስ ከመጫወት ተነስቶ ዓለምን እስከማስደመም ደርሷል።

በ2005 ሊቨርፑል ኤሲ ሚላንን በቻምፒየንስ ሊግ ማጠቃለያ ሲያሸንፍ ተመልክቷል።

ከዚያ በኋላም ከሊቨርፑል ጋር የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ሆኗል። 'ታራንጋ ላየንስ' (የታራንጋ አንበሶች) በሚለው ቅጽል ስሙ ከሚታወቀው የሴኔጋል ቡድን ጋር ሁለት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አንስቷል።

ሳዲዮ ማኔ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በ2021 ሴኔጋል ግብፅን አሸንፋ የአፍሪካ ዋንጫን ያነሳችበትን ግብ ያስቆጠረው ማኔ ነበር።

ያንን ቀን "በሕይወቴ እጅግ ደስተኛ የሆንኩበት እና የሕይወቴን ታላቁ ዋንጫ ያገኘሁበት" ሲል ነው የሚገልጸው።

ከትውልድ ቀዬው በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው ሳድሀዩ ውስጥ በስሙ ስቴድየም ተሰይሟል።

የ33 ዓመቱ ማኔ የአፍሪካ ዋንጫ ታሪኩን በድል አጠናቋል።

የሴኔጋል አሠልጣኝ በበኩላቸው ማኔ በቀጣዩ የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ እንዲሳተፍ ማሳመን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ በኬንያ፣ በታንዛንያ እና በኡጋንዳ ይካሄዳል።

"አብሮን ቢቆይ ደስ ይለናል። እየተጫወተ መቀጠል ይችላል" ሲል አንድ የማኔ አድናቂ ተናግሯል።

ማኔ አሁን ለሳዑዲ አረቢያው አል-ናስር እየተጫወተ ነው። በትውልድ ቀዬው ሆስፒታል እና ትምህርት ቤት ለመገንባት ቃል ገብቷል።

ለመስጊድ ግንባታ ገንዘብ ከመለገሱ ባሻገር በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅትም ከፍተኛ ድጋፍ አድርጓል።

በ2018 የቻምፒዮንስ ሊግ የመጨረሻ ፍልሚያ ሪል ማድሪድን 3 ለ 1 ካሸነፈ በኋላ 300 የሊቨርፑል ማልያዎች ለትውልድ ቀዬው ልኳል።

ማኔ ወደ ትውልድ ቀዬው ሲመለስ "ልክ እንደማንኛውም ሰው ይሆናል። ትሁት ነው" ሲሉ የአካባቢው እግር ኳስ ክለብ ፕሬዝዳንት ፎዴ ባካር ተናግረዋል።

"ጎልቶ መታየት አይፈልግም። የመንደሩ ነዋሪም ምን ያህል እንደሚወደው ያሳየዋል" ሲሉም ገልጸውታል።

ቤተሰቦቹ "ለሁሉም ሰው ሲል የሚታትር፤ ጥሩ ሙስሊም" ሲሉ ነው ማኔን የሚገልጹት።

ሊቨርፑል ካሸነፈ በኋላ የአንድ መስጊድ መጸዳጃን ማጽዳቱ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆናል።

ሳዲዮ ማኔ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአል ራሐም መስጊድ ኢማም አቡ ኡስማህ አል-ታሒብ "ማጽዳቱን በምሥጢር መያዝ ነው የፈለገው። በአደባባይ አላደረገውም። ታይታ አይፈልግም። ትዕቢተኛ አይደለም" ብለዋል።

የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ሙሳ ኒካቴ "ድንቅ ሰው ነው። ሳዲዮ በአፍሪካ እግር ኳስ ያለውን ሚና ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል። በተለይ ለሴኔጋል ሕዝብ ታላቅ ነው" ብሏል።

ማኔ በዓለም ዋንጫ የመጫወት ዕቅድ ይዟል።

በተለይም በአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ ዙር ጨዋታዎች ማኔ ትኩረት ስቦ ቆይቷል።

አሠልጣኙ "እስከቻልነው ጊዜ ድረስ አብሮን እንዲቆይ እንፈልጋለን" የሚሉትም ያለ ምክንያት አይደለም።