የአፍሪካ ዋንጫ በየአራት ዓመት እንዲካሄድ ተወሰነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች ዋንጫ (አፍኮን) ከአውሮፓውያኑ 2028 ጀምሮ በየአራት ዓመቱ እንደሚካሄድ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ኃላፊ ፓትሪስ ሞትሴፔ አስታወቁ።
የአፍሪካ ዋንጫ ከ1968 ጀምሮ በየሁለት ዓመቱ ነበር ሲካሄድ የነበረው። በወቅቱ ዋንጫውን ያዘጋጀችው ኢትዮጵያ እንደነበረች ይታወሳል።
በአውሮፓውያኑ 2012 እና 2013 ዋንጫው በአንድ ዓመት ልዩነት ተዘጋጅቷል።
ነገር ግን ከ2028 በኋላ አፍኮን በአራት ዓመት ልዩነት እንዲካሄድ ተወስኗል።
ሞትሴፔ እንዳስታወቁት ከ2029 ጀምሮ የአፍሪካ ኔሽንስ ሊግ የተባለ ውድድር በየዓመቱ ይካሄዳል።
"ለአፍሪካ እግር ኳስ አዲስ እና አስደሳች አሰራር ይዘን መጥተናል" ብለዋል ፕሬዝደንቱ።
"እኔ የማደርገው አፍሪካ የምትፈልገውን ነው። ዓለም አቀፉ መርሐ ግብር የተጣጣመ እና የተዋሀደ መሆን አለበት።"
በተጨማሪም ካፍ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ሀገር የምታገኘው ገንዘብ መጠን ከ7 ሚሊዮን ዶላር ወደ 10 ሚሊዮን ከፍ እንዲል ወስኗል።
የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ እሑድ በራባት ከመጀመሩ አስቀድሞ ነው የካፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቲ በሞሮኮ ባደረገው ስብሰባ አዳዲስ ውሳኔዎችን ያስተላለፈው።
በየሁለት ዓመት የሚካሄደው አፍኮን ከተቀረው ዓለም የእግር ኳስ መርሐ ግብር ይጋጫል የሚል ክስ ይቀርብበታል።
በተለይ በቅርቡ የተካሄዱ የአፍሪካ ዋንጫዎች የአውሮፓ እግር ኳስ በተደራረበበት ወቅት መከናወናቸው ቅሬታ አስነስቷል።
ነገር ግን ካፍ ዋንጫው በየሁለት ዓመቱ እንዲካሄድ ያደረገው ከውድድሩ የሚገኘውን ገቢ በአፍሪካ እግር ኳስ እድገት ላይ ለማፍሰስ እንደሆነ ይገልፃል።
በ2019 የአፍሪካ ዋንጫ በሰኔ እና ሐምሌ ወር እንዲካሄድ ቢወስንም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲሁም በመካከለኛው እና ምዕራብ አፍሪካ ያሉ ሀገራት የአየር ሁኔታ ይህ እንዲሆን አልፈቀዱም።
በ2021 እንዲሁም 2023 በካሜሩን እና አይቮሪ ኮስት የተካሄዱት ውድድሮች በጥር እና የካቲት ወር ነው የተዘጋጁት።
32 ሀገራት የሚሳተፉበት የዓለም ዋንጫ በሚቀጥለው ሰኔ እና ሐምሌ ይጠበቃል። በዚህ ምክንያት የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በወርሀ ጥር እንዲካሄድ ተወስኗል።
በ2027 ኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ የሚያዘጋጁት የአፍሪካ ዋንጫ በምን ወር እንደሚከናወን እስካሁን አልታወቀም።
ከ2027 ውድድር ከአንድ ዓመት በኋላ በ2028 ሌላ የአፍሪካ ዋንጫ የሚጠበቅ ሲሆን የዚህ ውድድር አዘጋጅ ሀገርም ይፋ አልተደረገችም።
ቢሆንም ከ2028 በኋላ አፍኮን በአራት ዓመት ልዩነት የሚከናወን ይሆናል። ይህም ማለት ውድድሩ ከአውሮፓ ዋንጫ ጋር በተመሳሳይ ወቅት ይደረጋል።
ሞትሴፔ እንዳሉት አዲሱ የአፍሪካ ዋንጫ መርሐ ግብር ይፋ የተደረገው ከፊፋ ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ጋር በመመካከር ነው።
በሌላ በኩል ከ2029 በኋላ የሚጀመረው የአፍሪካ ኔሽንስ ሊግ በመስከረም፣ ጥቅምት እና ኅዳር ወራት ይደረጋል። በውድድሩ 54ቱም የአፍሪካ ሀገራት ይሳተፋሉ።















